Site icon ETHIO12.COM

‹‹ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ወይስ ‘የማደናገርና የማበጣበጥ’ መብት… ›› አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

ማንኛውም ዜጋ ወይም ቡድን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው ማለት የአንድን ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብ፣ መንግሥት ወይም የሀገርን ክብርና ዝና በማጉደፍ ለግጭትና ለብጥብጥ የሚያጋልጥ ሀሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨት መብት አለው ማለት አይደለም፡፡

ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ምንም አይነት የፖለቲካ ፍላጎት ይኑረውም አይኑረውም በማንኛውንም አይነት የመገናኛ ዘዴ ተጠቅሞ በሚያሰራጫቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ሳቢያ በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ ዋነኛ ሰለባዎቹ ንጹሐን ዜጎች ናቸው፡፡

ስለሆነም ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ዜጎችን ማታለል፣ ማደናገርና ለጉዳት ማጋለጥ፣ የህብረተሰቡን የአንድነት፣ የወንድማማችነትና የመቻቻል ባህልን ማዳከም፣ የብሔርና የሃይማኖት ግጭቶች እንዲፈጠሩ ፅንፈኛ አጀንዳዎችን ማቀንቀን ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እንጂ በየትኛውም መመዘኛ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተደርጎ ሊታሰብ አይችልም፡፡

ሀሰተኛ መረጃ ደጋግሞ በመንዛት ሕዝብን እርስበርስ ማጋጨት ወይም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመግባባትን መቀስቀስ ሀገር የማፍረስ ፍላጎትን እንጂ ሀገር ወዳድነትን ወይም ለህዝብ ጥቅም መስራትን በፍፁም አይገልጽም፡፡ ለየትኛውም የኅብረተሰብ ችግርም የጥፋት እንጅ የመፍትሄ መንገድ አይሆንም።

በመሆኑም ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የማድረግ ጉዳይ በሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የመከላከልና ሀገርን የመታደግ ጉዳይ ከመሆኑ ባሻገር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ መንግሥታዊ ግዴታና ተግባር ነው፡፡

መንግሥት ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ በተጠና፣ የሕዝብን ፍላጎት እና ተጠቃሚነት በሚያስጠብቅ፣ ህጋዊነትን ማዕከል ባደረገ እና ጥፋተኞችን ሊያስተምር በሚችል አግባብ በክልላችን ህግና ሥርዓትን ለማስከበር እያደረገ የሚገኘውን ጥረት በመደገፍ ለሰላምና ለህግ የበላይነት ሌት ተቀን የሚተጉ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ያሉ ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው የመንግሥትን ህግና ስርዓት የማስከበር እንቅስቃሴ ለማኮላሸት አልመው የሚሠሩ አንዳንድ ሚዲያዎች በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶችና ግለሰቦች የመንግሥት የጸጥታ መዋቅርን እና አመራሮችን ስም የሚያጠለሹ በአጠቃላይ የህግ ማስከበር ሂደቱን በሚያደናቀፍ መንገድ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝብን የማደናገርና የማበጣበጥ ወንጀል የሙሉ ጊዜ ተግባራቸው አድርገው የሚሠሩ አሉ።

እነዚህ ኃይሎች የማኅበራዊ ሚዲያ የመገናኛ ዘዴን እንደ ምሽግ በመጠቀም በሀሰተኛና በተዛቡ መረጃዎች አማካኝነት ሥርዓት አልበኝነት እንዲንሰራፋ፣ በሁከትና ብጥብጥ ሕዝብና ሀገርን የሚያደሙ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ሲወተውቱ ይታያሉ፡፡ መቀመጫቸውን ከሀገር ውጭና በሀገር ውስጥ ያደረጉ ግለሰቦች፣ በቡድንና በግል የሚሠሩ ዩቱዩበሮችና የፌስቡክ ጸሐፊዎች እንዲሁም አንዳንድ የግል ሚዲያዎች ከእውነት ሸሽተውና ለገንዘብ አድረው ከሕዝባችን ፍላጎት በተቃራኒ ተሰልፈው አገራችንን የሚያምሱ በመሆናቸው ከዚህ ህገ ወጥ ተግባራቸው ለህዝብ ጥቅምና ለሀገር አንድነት ሲሉ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

መላው ሕዝባችን ከእነዚህና እነሱን ከመሰሉ የውሸት እና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም ከመረጃዎቹ ጀርባ ሆነው በአጀንዳ አቃባይነትና ሰጭነት የሸመቁ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ማንነት እንደሚገነዘበው እናምናለን፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት ከሀገር ውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቢጤዎቻቸው ጋር ሆነው በክልላችን ሕግና ሥርዓት እንዳይከበርና ክልላችንና ሀገራችን የብጥብጥ ማእከል ለማድረግ የሄዱበትን ርቀት በመገንዘብ መላው ሕዝብ ከሚነዙት ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች ሰለባነት ራሱን ሊጠብቅና የወሬዎቻቸውን ስውር ዓላማ አውቆ ሊያወግዛቸውና ሊታገላቸው ይገባል፡፡

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሽፋን አድርገው ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሕዝብን የሚያደናግሩና የጠላትን ዓላማ ለማሳካት ላይ ታች የሚሉ ሀሰተኞችን አደብ ለማስያዝ እንደ ሕዝብ ውሸትን ያለማዳመጥ መብታችንን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም ሀሳብን በነጻነት መግለጽ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት እና እንደ መንግሥትም ዋጋ የከፈልንለትና ወደፊትም የምንከፍልለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሽፋን በማድረግ የዜጎችን ክብር የሚነካ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለግጭት የሚያነሳሳና የሕዝብን ፍላጎቶችና ህግን የሚጻረር ሁሉ ከዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ሊቆጠብ ይገባል።

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ – የአማራ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ

Exit mobile version