Site icon ETHIO12.COM

በብ.ጀኔራል ተፈራ ማሞ ክስ ፍርድ ቤት ተጨማሪ 10 ቀን ፈቀደ

የአማራ ክልላዊ ብሄራዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ግንቦት 22/2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት የብርጋዴል ጀኔራል ተፈራ ማሞን ጉዳይ አይቷል። የመርማሪ ቡድኑ ምርመራ ስላልጨረሰ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በምክንያት ሲያስረዳም የተለያዩ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ በቂ ጊዜ ስላልነበረው መሆኑንን አመልክቷል። ከባንክ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከኢሳትና ከሌሎች ተቋማት የሚንሰበስባቸው መረጃዎች ስላሉ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰተው ምክንያቱን ዘርዝሮ በችሎት አቅርቧል።

የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው “መረጃዎቹ የሚሰበሰብባቸው ተቋማት የመንግስት ስለሆኑ ያን ያህል ጊዜ አይወስድም። ተከሳሽ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ በዋስትና እንዲለቀቁ ይገባል” ሲል ተከራክሯል። አስፈላጊ ናቸው የተባሉ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የተጠየቀው ጊዜ መርዘሙንም አመልክቷል።

የምርመራ ቡድኑ የጠበቃውን “በዋስትና ይለቀቁልኝ” ክርክር በመቃዎም “ተከሳሹ ከእስር ቢለቀቁ የተለያዩ ማስረጃዎችን ያጠፉብናል በዚህ ምክንያት በእስር ሊቆዩና የጠየቅነው የጊዜ ቀጠሮ ሊፈቀድልን ይገባል” በሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን ስላመነበት የምርመራ ቡድኑ ከጠየቀው የ14 ቀን ውስጥ 10 ቀናት ብቻ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለሰኔ 2/2014 ዓ/ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

የዜናው መነሻ የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

Exit mobile version