Site icon ETHIO12.COM

30 የኩላሊት እጥበት ማሽኖችን – ትልቅ እፎይታ

“የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግና በኩላሊት ህመም ለሚሰቃዮ ዜጎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነዉ” የተባለለት የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ተመርቋል።

በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአብ ሜዲካል ሴንተር ትብብር የተቋቋመ ነዉ።

የዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ታደሰ ሐብተየሗንስ ማዕከሉ “እኛጋ ያለዉን መገልገያ፤ ግንባታዉን የመሳሰሉትን እነሱ ደግሞ በኛ በኩል ፈተና ሲሆኑብን የነበሩትን የማሽን፤ የግብዓት አቅርቦት በመሸፈን ስራ ለመጀመር ዛሬ ለመመረቅ በቅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

ተቀመጭነቱ በአሜሪካ ያደረገዉ የአብ ሜዲካል ሴንተር 30 የኩላሊት እጥበት ማሽኖችን በማዕከሉ የገጠመ ሲሆን ይህም የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን በፊት ከነበረበት በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

ለአንድ የኩላሊት ታካሚ የእጥበት አገልግሎት የመስጠት ሂደት እስከ 4 ሰዓታት እንደሚፈጅ የተናገሩት ዶ/ር ታደሰ ታካሚዉ በሳምንት ሶስት ቀናትን አገልግሎቱን ማግኘት እንዳለበትም ነግረዉናል።

“የምናስተናግደዉ የሰዉ ቁጥር በቀን ሁለቴ ከሰጠን 120 ሰዉ፤ የማታዉን ጊዜም ከተጠቀምን ደግሞ በሳምንት ለ240 ሰዉ አገልግሎት መስጠት እንችላለን”

ማዕከሉ አሁን ከ30 እስከ 35 ለሚሆኑ ታካሚዎች አገልግሎቱን በመስጠት እንደሚጀምርና የተገልጋዮች ቁጥር በጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ ነግረዉናል።

“ታካሚዎች ዘመኑ የሚጠይቀዉን የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ነዉ የሚያገኙት” ያሉት ዶ/ር ታደሰ ሐብተየሗንስ የማዕከሉ መከፈት አገልግሎቱን በነጻ ለሚያገኙ ተገልጋዮች የገንዘብ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑንም ነግረዉናል።

ኢትዮጵያ ቼክ

Exit mobile version