Site icon ETHIO12.COM

ደብረ ብርሃን-“ባራኪው ንጉሥ ተባራኪዋ ምድር”

“ባራኪው ንጉሥ ተባራኪዋ ምድር”

ሀገራቸውን የሚባርኩ፣ ከዘመናቸው በአሻገር ያለውን ረጅም ዘመን አስቀድመው የለኩ፣ ጥበብ የተቸራቸው፣ ብልሃት የበዛላቸው፣ ታሪክ ከፍ አድርጎ የጻፋቸው፣ ትውልድ የሚያከብራቸው፣ አባታችን ሲል የሚወዳቸው ታላቅ ንጉሥ፡፡ አስቀድመው ጥበብን መርምረዋል፣ በጥበብ መንገድም ተራምደዋል፡፡ ምስጢራትን ፈልገዋል፣ ምስጢራትን አመስጢረዋል፣ ደኃ እንዳይበደል፣ ፍርድ እንዳይጎደል፣ ፍትሕ በሀገራቸው እንዲሰፍን፣ ሕዝባቸው በፍትሕ እጦት እንዳያዝን ለፍተዋል፡፡

ንጉሡ ዳዊትና እግዚዕክብራ መልካም ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን ይማጸኑ ነበር፡፡ እናት አባቱን የሚያከብር፣ ሀገሩን የሚወድ፣ በሰውና በፈጣሪም የሚወደድ ልጅ እንዲሰጣቸው ጸሎትና ምኞታቸው ነበር፡፡ ፈጣሪም ልመናቸውን ሰማቸው፡፡ በተባረከች ሌሊት መልካም ልጅ አደላቸው፣ ስሙ ገናን የኾነ ልጅ ተሰጣቸው፡፡ ከአብራካቸው ታላቅ ልጅ ተፈጠሩ፡፡ የንጉሥ ልጅ ልዑል ነበሩና በልዕልና አደጉ፡፡ ፊደል ቆጠሩ፣ ዳዊት ደገሙ፣ መጻሕፍትን አመሰጤሩ፣ ተመራመሩ፡፡ ታዲያ እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ለስልጣን ተቀናነቃኝ ይኾናሉ ተብሎ ስለ ተሰጋ ወደ አምባ ግሸን ተወሰዱ፡፡ በአምባ ግሸንም እየተማሩና እየተመራመሩ አደጉ፡፡ እርሳቸው እና ሌሎች የነገሥታት፣ የመኳንንትና የመሳፍንት ልጆች በሚኖሩበት በዚያ በአምባ ግሸን መጻሕፍት ነበሩና መጻሕፍትን መረመሩ፡፡ የሚመጣውን ዘመን መተሩ፡፡

በገዳም በነበሩበት ዘመን ለአበው ይታዘዛሉ፣ ደግነትን ያደርጋሉ፣ ከአባቶች እግር ተቀምጠው እውቀት ይቀስማሉ፣ ጥበብን ኹሉ በብልሃት ይከተላሉ፣ አበው መረቋቸው፣ መልካሙን ኹሉ ተመኙላቸው፣ በልጅነት ዘመናቸው መኾን ያለባቸውንም ኾኑ፡፡ በገዳም እያሉ የፈጣሪያቸውን ስም እየጠሩ፣ ሳያቋርጡ ምሥጋና እያቀረቡ ይማጸኑም ነበር፡፡

እኒያ አስቀድመው ለቅብዓ መንግሥት የተመረጡት ሰው የመንገሻቸው ዘመን እስኪደርስ ድረስ በዚያው ቆዩ፡፡ በዚያ ሥፍራ በእውቀት ታንጸዋል፡፡ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ነገሥታት የስልጣን ዘመናቸው እያበቃ ሄደ፡፡ የእርሳቸው ቅብዓ መንግሥት መቀቢያ፣ በአስፈሪው ዙፋን ላይ መቀመጫ ዘመን እየቀረበ መጣ፡፡ አስቀድሞ ለንግሥና የተመረጠን ማን ያስቀረዋል? አስፈሪው ዙፋን ይጠብቃቸዋልና፡፡

ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ በየቦታው የሚነሱ ጠላቶች ፈተና አብዝተውባት ነበር፡፡ በዘመኑ የሚነሱት ነገሥታትም የሀገራቸውን ጠላት በማስታገስና በመቅጣት ታላቋን ሀገር በመጠበቅ ይጣደፋሉ፡፡ አንደኛው ንጉሥ አልፎ ሌላኛው ንጉሥ እየተተካ የታላቁ ንጉሥ ቅብዓ መንግሥት ዘመን ደረሰ፡፡ በታላቅ ግርማ ቅብዓ መንግሥቱን ተቀብተው፣ በዕውቀትና በብልሃት ነገሡ – ንጉሥ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፡፡ የዙፋን ስማቸውም ቆስጠንጢኒዎስ ተባለ፡፡ ቆስጠንጢኒዎስ በአስፈሪው ዙፋን ላይ ተቀመጡ፡፡

እውነተኛው መሪ በእውነተኛው መንገድ ይጓዙ ጀመር፡፡ የሕዝብ አሥተዳደራቸውም ብልሃት የተመላበት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱትን ጠላቶች ከጦርነት በፊት በፍቅር አደብ እንዲይዙ በብልሃት ሠሩ፡፡ ትዕግስትና ፍቅር ፍራቻ የመሰላቸውን ሞኞች ደግሞ በነበልባል ክንዳቸው ያነዷቸው ጀመር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ለጥል የሚነሳውን ቀጡት፣ አሳፍረው መለሱት፣ በሚወዷት፣ በሚመሯትና ነብሴ በሚሏት ሀገራቸው የከፋ ነገር ኹሉ ይጠፋ ዘንድ ያለ እረፍት ሠሩ፣ ደከሙ፡፡

ታላቁ ንጉሥ ሥልጣን በጠንካራ ማዕከላዊነት ተዋቅሮ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ እንዲያዝ፣ በመላ ሀገሪቱ የሚጸና አንድ የትዕዛዝና የደንቦች ሥርዐት እንዲዘረጋ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ወሰን ማስፋት፣ በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል አቋምን ማጠንከር ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡ በዘመኑ ከዓለማውያንና መንፈሳውያን የሚነሱባቸውን ችግሮች በጥበብ እየተሻገሩ፣ እያሸንፉ፣ በጠንካራ መንፈስ እያጸኑ፣ ያቀዱትን ተግባራዊ አደረጉ፡፡

አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮአና ማንቴል ኒችኮ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው “ያለ ጥርጥር እኒህ ንጉሥ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው፣ እጅግ አርቆ ተመልካች ከኾኑት ፖለቲከኞችና ስልተኝነትን ከተካኑ፣ ዲፕሎማቶች አንዱ ከመኾኑም በላይ እጅግ ብሩህ አስተሳሰብ፣ ካላቸውና በዕውቀት ከታነፁት ታዋቂ መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው በኋላ የመጡ አያሌ መሪዎች በቀጣዮቹ ምዕተ ዓመታት ውስጥ የእርሳቸውን የፖለቲካ አስተሳሰብ አርዓያቸው አድርገው ተከትለውታል” ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡

ብልህነታቸው፣ ጥበባቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸውና ራዕያቸው በእርሳቸው ዘመን የነበሩትን ብቻ ሳይኾን ከእርሳቸው በኋላም የመጡትን ትውልዶች አስደመመ፡፡ ጥበባቸው አስከበራቸው፣ ብልሃታቸው አባታችን አስባላቸው፡፡ ንጉሥ ኾይ ክብር ይገባዎታል፣ ንጉሥ ኾይ ታሪክ ያከብረዎታል፣ ድርሳናት ይናገርልዎታል ተባሉ፡፡

በታሪካዊና ሃይማኖታዊ ዕውቀት የታነፁት ዘርዓያዕቆብ የኢትዮጵያውያን ባሕልና ልምድ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር ይባላሉ፡፡ ስማቸው ዛሬም ገናና የኾኑት ታላቁ ንጉሥ በዘመናቸው አያሌ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ታላቅና እውነተኛ ንጉሣዊ ሥርዐት ለመገንባት ሲያስቡ የዕውቀት ምንጭ ከኾነቻቸው ቤተክርስቲያን ጋር ታላቅ ወዳጅነትን ፈጠሩ፡፡ እሳቸውም በቤተክርስቲያን ውስጥ ስላደጉ በውስጧ ያዩትን መልካም እሴት በሥርዐታቸው ሊጠቀሙበት ወደዱ፡፡ ተጠቀሙበትም፡፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ማጠናከር ትኩረት የሰጡት ንጉሡ ዘርዓያዕቆብ የባሕር በሩን ነጻ አድርጎ መጠበቅ ታላቁ ሥራቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ባሕሩን ተሻግሮ ከፍ እንዲል ነበረ ጥረታቸው፡፡ የቀይ ባሕርን በብልሃት መጠቀም ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው ያውቃሉና ከባሕር በሩ ላይ ትኩረት አደረጉ፡፡ ቀይ ባሕር ንግድና ሥልጣኔ የሚመላለስበት፣ ጻድቃን የሚመጡ የሚሄዱበት፣ ሙሴ በበትር የተሻገረበት፣ የዓለም ፖለቲካ የሚዘወተርበት የስበት ማእከል ነውና እርሱን በሚገባ ማሥተዳደር የሚፈልጓትን ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መኾኑን ተረድተዋል፡፡

ለመንግሥቱ መጽናትና ኃይልነት ታላቅ አጋዥ የነበረችውን ቤተክርስቲያንን በመደገፍ ታላቅ ነገር ያደርጉ ነበር፡፡ የጥንቆላ ሥራና ልማዳዊ እምነትም ተንቅሎ እንዲጠፋ ጥረት አደረጉ፡፡ በቤተ መንግሥቱና በቤተ ክህነቱ የጠለቀ ዕውቀት የነበራቸው ታላቁ ንጉሥ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ሕግጋትን አውጥተዋል፡፡ የዓለም መንግሥታት የሚፈልጉትን፣ በሀገራቸው እንዲቀመጥ የሚሹትን፣ እንዲባርካቸውና እንዲቀድሳቸው የሚመኙትን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበትን መስቀል በኢትዮጵያ ምድር እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡

ተክለጻዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ይኩኖአምላክ እስከ አጼ ልብነድንግል በሚለው መጽሐፋቸው አጼ ዘርዓያዕቆብ ስም መንግሥታቸው ቆስጠንጢኒዎስ በጠባያቸውና በዝንባሌያቸው እንደሌሎቹ ታላላቅ ንጉሠ ነገሥቶች እንደሞክሻቸው እንደ ቆስጠንጠኒዎስ መንፈሳዊነትንና ስጋዊነትን፣ ጭካኔንና ርህራሄን፣ ጀግንነትንና ጥንቃቄን አደባልቀው ሲሠሩ የኖሩ ትልቅ ንጉሠ ነገሥት ናቸው ብለዋቸዋል፡፡

ወጨጫ ተራራ የአባታቸው የአጼ ዳዊት መናገሻ ነበር ይባላል፡፡ በአባታቸው መናገሻ የነበሩት ታላቁ ንጉሥ ዘርዓያቆዕብ አንዲት ቀልባቸውን የምትስብ ሥፍራ ተመለከቱ፡፡ ለጤና የተስማማች፣ ለሠራዊታቸውና ለባለሟሎቻቸው ውብ የኾነች ሥፍራ፡፡ ንጉሡ አብዝተው ወደዷት፣ ወደዚያች ሥፍራም ይሄዱ ዘንድ ወደዱ፡፡ ድንኳናቸውን ከተራራው አውርድው ወደውቧ ሥፍራ አዛወሩ፡፡ ያቺም ሥፍራ ደብረኤባም ትባል ነበር ይባላል፡፡ ድንኳናቸውን በዚሕች ሥፍራ ያደረጉት ታላቁ ንጉሥ በዘመናቸው ከሠማይ የወረደ ብርሃን በመናገሻቸው ከተማ አናት ላይ ተመለከቱ፡፡ ብርሃኑም ግሩም ነበረ፡፡ በአዩት ብርሃንም ተደነቁ፡፡ የብርሃን አንባ አሉ፡፡ ስሟም ደብረ ብርሃን ተባለች፡፡ በዚህችም ከተማ ያማሩ ነገሮችን ሠሩ፡፡

የወርቅ ጉልላት ያለው የሥላሴ ቤተክርስቲያንን በመናገሻቸው ከተማ አሠሩ፡፡ አዲስ የቆረቆሯትን ከተማቸውን የትምህርት ማእከል አደረጓት፡፡ እርሳቸው የጥበብ ሥራዎችን የከተቡት በዚህችው በመናገሻዋ ከተማ ነበር፡፡ መጻሕፍትንም አስተረጎሙ፡፡ ቀን ቀን እየተካ የፍጻሜያቸው ዘመን ተቃረበ፡፡ በሀገራቸው አያሌ ሥራዎችን ያደረጉት ታላቁ ንጉሥ ዙፋኑን አስረክበው የማለፊያ ዘመናቸው ደረሰ፡፡ ከፍ ያለውን ታካሪካቸውን፣ የደመቀው ዐሻራቸውን አስቀምጠው አሸለቡ፡፡ ስማቸው ግን ከፍ ብሎ ይኖራል፣ ዝናቸው ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራል፡፡

ባራኪው ንጉሥ ምድሯን ይባርካሉ፡፡ በመሠረቷት ከተማ በቀኝ እጃቸው መስቀል አንስተው ለከተማዋ ውበት ኾነው በክብር ተቀምጠዋል፡፡ ንጉሡ የመሠረቷትን ከተማ ይባርኳታል፣ ታሪካቸው ምድሯን ያስውባታል፡፡ ባራኪው ንጉሥ የሚወዷትን መናገሻቸውን ከተማ ሲያከብሯት ይኖራሉ፡፡ በመናገሻቸው ከተማ የእሳቸው ስም ከፍ ብሎ ይጠራል፡፡ በተለይም ደግሞ በጥበብ የተሠራው ሐውልታቸው ለከተማዋ ውበት ኾኗል፡፡ ሐውልታቸውን የሚያየው ኹሉ ታላቁን ንጉሥ እያስታወሰ ይኖራል፡፡

ʺየዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል” እንዳለ መጽሐፍ የቀደሙትን አስተውል፣ ታሪኩንም አክብር፣ ጠብቅ፣ አዲስ ታሪክም ሥራ፡፡

ንጉሡ ዘርዓያዕቆብ የመሠረቷትን፣ የብርሃን አምባ ያሏት፣ ደጎች፣ ጀግኖች፣ ሀገር ወዳዶች የሚፈጠሩባት ደብረ ብርሃን ዘመናትን በተሻገረው ታሪኳ ደምቃ ትኖራለች፡፡ እነኾ በዚህ ዘመን ደግሞ በልማት መልካም ጉዞ ላይ ካሉት ከተሞች መካከል አንደኛዋ ናት፡፡ ተባራኪዋ ከተማ በባራኪው ንጉሥ አደባባይ ሰይማለች፡፡ በታላቁ ንጉሥ የተሰየመው አደባባይ የከተማዋ ውበት ነው፡፡ ንጉሡ ይባርኳታል፣ እርሷም ትባረካለች፣ በደስታም ትኖራለች፡፡ የብርሃን አምባ የነገሥታቱ መናኸሪያ፡፡

በታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)

Exit mobile version