Site icon ETHIO12.COM

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ግዴታውን እንዲወጣ አብን ጠየቀ

ሰኔ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ሰኔ 11/2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን አማራዎች ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ መጨፍጨፋቸውን አውግዟል፡፡

አብን ጭፍጨፋውን አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸም የኖረው እና እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ እንደተፈጥሯዊ እና መደበኛ ክስተት እየተወሰደ መኾኑን “አሳዛኝ” ሲል ገልጾታል፡፡

መንግሥት የጸጥታ መዋቅሩ በሰው ኃይልም ኾነ በቁሳቁስ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አቅም መገንባቱን በተደጋጋሚ መግለጫዎች እና ትዕይንቶችን በሚያከናውንበት በዚህ ወቅት ይህ ዓይነቱ ጭፍጨፋ ተባብሶ መቀጠሉ እና ጥቃቱን ማስቆም አለመቻሉ ጉዳዩ የአቅም ማጣት ሳይኾን የፈቃደኝነት እና የዝግጁነት ማጣት መኾኑን እንደሚያመላክት አብን ገልጿል፡፡

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ግዴታው መኾኑን ተረድቶ ያለምንም ሰበብ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ንቅናቄው ጠይቋል፡፡ በዚህ ጭፍጨፋ ውስጥ የተሳተፉ ታጣቂዎችን እና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ተባባሪዎቻቸውንም ለሕግ ያቅርብ ብሏል፡፡

አብን በመግለጫው ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በሕይወት የተረፉ ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሶ አፋጣኝ ሕይወት አድን ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ለተጎጅዎች እና ቤተሰቦቻቸው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው ነው የጠየቀው፡፡

የፌዴራሉ እና የክልል መንግሥታት ለጥቃት ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች በቂ የስጋት ትንተና እንዲሠሩ እና ቀጣይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉም ሲል ንቅናቄው አሳስቧል፡፡

መንግሥት ለጥቃት ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች ነዋሪ የኾኑ ዜጎችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ከመሰል ጥቃቶች ራሳቸውን የሚከላከሉበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትም ገልጿል፡፡

ችግሩ መዋቅራዊ እና ሥርዐት ሠራሽ ገጽታ ያለው መኾኑን መረዳት እንደሚገባም ነው አብን ያመላከተው፡፡

መንግሥት እና መላ ኢትዮጵያውያን ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መዋቅራዊ እና ሥርዐት ሠራሽ ሽግግር እንዲደረግ እና ለኹሉም ኢትዮጵያውያን ዋስትና የሚሰጥ ሥርዐት እና ሀገር ለመገንባት እንዲረባረቡም ንቅናቄው ጥሪ አቅርቧል፡፡

አብን በመግለጫው “በተፈጸመው ጭፍጨፋ ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችን ነብሳቸው እንዲማር፤ ለጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች ፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን” ብሏል፡፡

Exit mobile version