Site icon ETHIO12.COM

ባለፉት 11 ወራት ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ተያዘ

ባለፉት 11 ወራት ከኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበር ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

የጸረ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያስችል የውይይት መድረክ በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው እለት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች፣ የንግድ እና ቀጠናዊ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገ/መስቀል ጫላ፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ፣ የፍትህ ሚኒስትር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን በመካላከል እና በመቆጣጠር የተገኙ ውጤቶች እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በሚመለከት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ የመነሻ ጹሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከባለድርሻ አካላት እና ከሌሎች ተሳታፊዎች ተጨማሪ የማደበሪያ ሀሳቦች ተነስተው ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ ባቀረቡት የመነሻ ጹሁፍ፣ ኮሚሽኑ የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተው ባለፉት 11 ወራት ብቻ 604 ሚሊዮን ብር የወጭ እና 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የገቢ በድምሩ ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባለፉት 11 ወራት በሰራው የህግ ማስከበር ስራ በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ሀገር ልታጣው የነበረውን ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ማደን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ አክለውም፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ህገወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ʽʽችግሩ የሀገር ደህንነት እና ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል” ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው፣ ሀገራችን ከለውጡ በኋላ በዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተፈተነች መሆኑን ጠቁመው በተለይም ህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ የአካባቢውን ሰላም እና የህዝብን ደህነነት አደጋ ላይ እየጣሉ በመሆኑ የጸረ ኮንትሮባንድ ግብረኃይል ተቋቁሞ ጠንካራ የህግ ማስከበር ዘመቻ በተደራጀ መንገድ እያተሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የህገወጥ ንግድ እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የንግድ ስርዓቱን በማዛባት ፍትሀዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ገ/ጫላ፣ በተለይም የጠረፍ ንግድን ስምምነትን ተገን በማድረግ የሚካሄዱ ህገወጥ የንግድ ልውውጦችን መልክ ለማስያዝ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከጊዜ ወደጊዜ በአፈጻጸም ስልቱ እና በዓይነቱ እየጨመረ የመጣውን ህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን ለመቀነስ ማህበረሰብን መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መደረክ ማዘጋጀት ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የጸጥታ እና የፍትህ ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version