ግምቱ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ እና የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል ባለፉት 6 ወራት መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ለትግራይ ክልል የሕክምና ግብዓት አቅርቦቶች ድጋፍን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው በመንግስት እና ከሰባት አለም አቀፍ ምግባረ ሠናይ ድርጅት ጋር በተፈጠረ ትብብር ከፈረንጆቹ ሐምሌ 2021 ጀምሮ 658 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የሕክምና አቅርቦቶች በ18 የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልሉ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡
መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምት ባወጀበት ወቅት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመድሃኒት እና የመድሃኒት አቅርቦቶች በመቐለ እና ሽሬ ሲደርሱ እንደነበር ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 3 ሺህ 565 ኪሎ ግራም የአደጋ ጊዜ መድሃኒት ማቅረቡን ያወሳው መግለጫው ዩኒሴፍ በአውሮፓ ህብረት ልገሳ 42 የተለያዩ መድሃኒቶችን የያዙ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና መስጫ ኪቶችን ወደ ቦታው ማድረሱንም ጠቅሷል።
በዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን እና በዓለም ጤና ድርጅቶች ትብብር ባለፈው ወር 850 ሺህ ዩኒት ክትባት ለትግራይ ክልል ሲደርስ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን በርካታ ሜትሪክ ቶን የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሶች፣ ማስክ እና ጓንቶች መድረሳቸውም ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 6 ወራት ግምቱ 1 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እና 128 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል መድረሱንም ውጭ ጉዳይን ጠቅሶ ኦ ቢ ኤን አመልክቷል