Site icon ETHIO12.COM

ብልጽግናና የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

የብልጽግና ፓርቲ እና የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ። የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ እና በቅርቡ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሊዩ ጂያንቾኦ የዌብናር ውይይት አድርገዋል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያቸው የሆነውን የዌብናር ውይይት ያደረጉት ሊዩ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በአቶ አደም ፋራህ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። አቶ አደም ፋራህ በቻይና እየተመዘገበ ላለው ስኬት የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲን አመራር አድንቀዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲም ሀገር በቀል ፖሊሲዎችን በመተግበር ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሂደቱም ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ልምዶችን ሲቀስም መቆየቱንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

አሁን በምገኝበት ሀገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ አንድነትንና ትብብርን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት አቶ አደም፣ ሁለቱ እህት ፓርቲዎች ተግባር ተኮር የሆነ ግንኙነታቸዉን በማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባቸው አዉስተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክም የባለብዙ ትብብር ማዕቀፎችን በማጠናከር ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በዓለም እንዲሰፍን ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ሚስተር ሊዩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ዋናዋ ምሰሶ እንደሆነች ቻይና እንደምታምን እና የብልጽግና ፓርቲም በቀጠናዊ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች የሲፒሲ አጋር እንደሆነ አስታውቀዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በኩል ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን አንስተው፣ የሁለቱን ፓርቲዎች የወደፊት የትብብር መስኮች ጠቅሰዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተስማሙ ሲሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችንም በቅርቡ እንደሚጀምሩ ማስታወቃቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል

Exit mobile version