የፌደራል መንግስት የአማራ፣ ትግራይና አፋር ህዝብን ማህበራዊ ዕረፍት የሚነሱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌለው መንግስት አስጠነቀቀ።
የይገባኛል ጥያቄ በሚነሣባቸው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ሁሉም ወገኖች ለፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲገዙና ከተንኳሽ ተግባራት እንዲቆጠቡ የፌደራሉ መንግሥት ያሳሰበው ሰሞኑንን በራያ አላማታ አካባቢ እየወጡ ያሉ መረጃዎችን ተከትሎ ነው።
የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምንት አስመልክቶ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ፣ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ውይይት እየተካሄደ መሆኑንን አስታውቀዋል። በውይይቶቹም ላይ የህዝብ ውሳኔና ፍላጎት እንደሚከበር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በይገባኛልና በማንነት ጥያቄ ዙሪያ ሲንከባለሉ የኖሩ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በህግና በህዝብ ውሳኔ ዕልባት ለመስጠት እየተሰራ ባለበትና መንግስትም ለተግባራዊነቱ ጫፍ በደረሰበት ወቅት፣ የህዝብን ማህበራዊ ዕረፍት የሚያናጋ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ከትገባራቸው እንዲቆጠቡ፣ ካለፈው ስህተትና ጥፋት በመማር ለፕሪቶሪያው ስምምነት መገዛት እንደሚገባ አቶ ፋራህ አስታውቀዋል።