የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሚከተሉት ናቸው፦

1. ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

2. አቶ አደም ፋራህ

3. አቶ ደመቀ መኮንን

4. አቶ ደስታ ሌዳሞ

5. ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

6. አቶ አብርሃም ማርሻሎ

7. አቶ አሻድሊ ሀሰን

8. አቶ ጌታሁን አብዲሳ

9. አቶ ኡሙድ ኡጁሉ

10. አቶ ተንኳይ ጆክ

11. አቶ ኦርዲን በድሪ

12. አቶ አሪፍ መሃመድ

13. ዶ/ር አብርሃም በላይ

14. ዶ/ር ሊያ ታደሰ

15. ሀጂ አወል አርባ

16. ሀጅሊሴ አደም

17. አቶ ኤሌማ አቡበከር

18. ወ/ሮ ሀሊማ ሀሰን

19. አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

20. አቶ አህመድ ሽዴ

21. ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ

22. አቶ ፀጋዬ ማሞ

23. ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

24. አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

25. አቶ ርስቱ ይርዳው

26. አቶ ተስፋዬ ይገዙ

27. አቶ ሞገስ ባልቻ

28. አቶ ጥላሁን ከበደ

29. አቶ መለሰ ዓለሙ

30. አቶ ሽመልስ አብዲሳ

31. አቶ ፍቃዱ ተሰማ

32. ዶ/ር አለሙ ስሜ

33. ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

34. አቶ አወሉ አብዲ

35. አቶ ሳዳት ነሻ

36. ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

37. ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ

38. ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ

39. ዶ/ር ይልቃል ከፍያለ

40. ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

41. አቶ ተመስገን ጥሩነህ

42. አቶ መላኩ አለበል

43. ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ

44. ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ

45. አቶ ግርማ የሺጥላ ናቸው።

 

የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ የአቋም መግለጫ

ፈተናዎችን ተሻግረን የኢትዮጵያን ልዕልና ማብሰር እንደምንችል በመተማመን ቅድመ ጉባኤ ጥልቀት ያለው ውይይት በአዳማ አደርገናል፡፡ ከየካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ሲከናወን የቆየው የመጀመርያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በስኬት ተጀምሮ በስኬት መጠናቀቁ ወትሮም ቢሆን ገና ከጅምሩ አቅዶ መፈጸም ጀምሮ መጨረስ ቋሚ ባህል አድርጎ ለተነሳው ፓርቲያችን ስኬታማ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አራተኛ አመቱን የያዘ ቢሆንም ባለፉት አመታት በርካታ የሆኑ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች ተስተናግደዋል፡፡ እንቅፋትን እንደድልድይ ተጠቅሞ ወደዘላቂ ብልጽግና ለመንደርደር የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ከሞላ ጎደል ተሳክተዋል፤ ወደፊትም የተለያዩ ተሞክሮዎች እየታከሉባቸው ለታላቅ ስኬት መንደርደርያ ይሆናሉ የሚል እምነት ተይዟል፡፡

ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ጀምሮም በርካታ የምንኮራባቸው ድሎች ያስመዘገብን ቢሆንም በተመሳሳይ ጉድለቶቻችንና ተግዳሮቶቻችንም ቢሆኑ በቀላሉ የምናያቸው አይደሉም፡፡በመጀመርያው ጉባኤያችን ሰፊ ጊዜ ሰጥተን ለማየት የሞከርነውም ባለፉት አራት አመታት የነበሩንን መልካም ተሞክሮዎች እንዴት እናስቀጥል፣ ጉድለቶቻችንስ በምን መልኩ እንቅረፍ፣ ተግዳሮቶቻችንን በመቋቋም እንዴት እንሻገር ስንል ሰፊ ውይይት እና ምክክር አድርገናል፡፡

በአዳማው ውይይታችን ያሳለፍናቸውን ጊዚያት ካስቀመጥናቸው ትልሞች እና ግቦች በመነሳት በሰፊው የገመገምን ሲሆን በተለይም የአገረ መንግስት ግንባታ ጉዟችንን በጥልቀት ፈትሸናል፡፡ አገር የማጽናት ከትውልድ ወደትውልድ የማሻገር ትልማችን ሊሳካ የሚችለው ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በጽኑ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ በመትከል እንደሆነ አምነን ከዚህ በመነሳት የምንገኝበትን ሁኔታ በቂ ጊዜ ወስደን ለማየት ሞክረናል፡፡

ምንም እንኳን ከሰላም እና ጸጥታ መደፍረስ ከዜጎች መፈናቀል እና ሞት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙን ጉድለቶች ቀላል ተደርገው የሚወሰዱ ባይሆንም በአንጻሩ አገር ወዳድ ዜጎች በመፍጠር ለዜጎች ሁለንተናዊ ክብር እና ዘላቂ ሰላም የሚተጋ መንግስታዊ መዋቅር እና ተቋማዊ ሪፎርም ለማረጋገጥ የሰራነው ስራ ከፍ ያለ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡

ከፈተና ወደልዕልና በሚል መሪ ቃል በጥብቅ ዲሲፕሊን የተመራው የአዳማው ውይይት ለመጀመርያው ጉባኤያችን በስኬት መጠናቀቅ የማይተካ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከአሁን ቀደም ከተለመደው የውይይት አካሄድ ወጣ በማለት ለጉባኤው አጀንዳዎች በቂ ጊዜ በመመደብ ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነትን በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረት የተደረገ ሲሆን በጉባኤው አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክሮ ወደተቀራራቢ አመለካከት ለመምጣት አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የብልጽግና ምስረታ፣የተቋማት ግንባታ፣ ስኬታማ ምርጫ በማካሄድ በህዝብ ዘንድ ቅቡልት ያለው መንግስት መመስረት መቻላችን፣ አረንጓዴ አሻራችንን መሬት ለማስነካት የሄድንበት ርቀት፣ ለብዝሀ ኢኮኖሚ ልማት የሰጠነው የተለየ ትኩረት፣በከተማ እና በገጠር ልናከናውናቸው የሚገቡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎቻችን፣የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትና የቀጠናው ትብብር፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አፈጻጸምና የተገኘው ስኬት፣የውስጠ ፓርቲ ስራችን አጠቃላይ ሂደት እና ውጤቱን በስፋት በመዳሰስ ጥልቀት ያለው ውይይት የተደረገ ሲሆን በጉባኤው ተሳታፊዎች በኩል ተጨማሪ ግብአት የተገኘበትና ትምህርት የተወሰደበት ነበር፡፡

የጉባኤው ሂደት እና ነጥረው የወጡ ዋና ዋና ጉዳዮች

ስኬቶቻችን በርካታ እና ስፋት ያላቸው ቢሆኑም ያጋጠሙን ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶችም በእጅጉ የተወሳሰቡ እና ረዥም እና አድካሚ ተገዳዳሪ ሁኔታ የፈጠሩብንም እንደነበሩ አመላክተናል፡፡ ከውስጣዊ ፈተናዎቻችን ስንነሳ አልጠግብ ባዩ ጁንታ በሁሉም አቅጣጫ የፈጠረብን እንቅፋት የህዝባችንን አኗኗር በእጅጉ ያወሳሰበው ከመሆኑም በላይ በአገረ መንግስቱ ቀጣይነት ላይ የህልውና ስጋት እስከመሆን የደረሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህዝባችንን ዋነኛ አቅም አድርገን በመጠቀም የተቃጣብንን የህልውና አደጋ በብቃት መመከት ችለናል፡፡

ጽንፈኝነት የወለደው አገራዊ ፈተናም ቢሆን ፖለቲካው እንዳይሰክን በማድረግ በኩል አሉታዊ ሚና ነበረው አለውም፡፡ አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን ተከትሎ የተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እና የተፈጥሮ አደጋ በተለይም ኮሮና አንበጣ እና ድርቅ የፈጠሩት አሉታዊ ጫና በማህበረሰቡ አኗኗር ላይ ቀጥተኛ እና የወዲያው ተጽዕኖ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት እና የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ አለመፈጠር በብልጽግና ጉዟችን ሁነኛ እንቅፋት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡

ባሳለፍናቸው አመታት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እና የአንደኛና እና የሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌትን ተከትሎ እንዲሁም ከህልውና ትግላችን ጋር በተያያዘ የተፈጠረብን የውጭ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ የተፈተንበት ጉዳይ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነቱ የፈጠረብን ጫና በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ እንደፈጠረ በውይይታችን ላይ ተመልክተናል፡፡

ከተፈጠረብን ጫና ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት የጋራ እርብርብ በምሳሌነቱ ለአለም የሚተርፍ ታሪካዊ ድል የተቀዳጀንበት እንደነበረም እስታውሰናል፡፡

በውይይታችን ከተዳሰሱና የተለየ አጽንኦት ሊሰጣቸው ይገባል ብለን የተመለከትናቸው ነጥቦች ከህዝብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይም ከሌብነት እና ከስርቆት ጋር ህዝባችንን ያማረሩ ጉዳዮችን በስፋት የገመገምን ሲሆን በሁሉም አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችንም ለመመልከት ሞክረናል፡፡

በተለይም የህዝባችንን ኑሮ ከእለት ወደእለት አስቸጋሪ እና ውስብስብ እያደረገው የመጣውን እርስ በእርስ የመጠራጠር እና ያለመተማመን ችግር፣ መሰረታዊ የሆነ የገበያ ጉድለት እና የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀል እና ሞት የሚቆምበትን ሁኔታ በጥልቀት ገምግመን ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣበትን አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የውስጠ ፓርቲ ፖለቲካዊ ጤንነታችንን በቅጡ የተመለከትን ሲሆን አባላትን የማጥራት እና አመራር የማብቃት ስራችን የማያቋርጥ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተግባብተናል፡፡

ከጉባኤው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል ያለፉት አመታት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ቀርቦ በጥልቀት የታየ ሲሆን በተጨማሪ የፓርቲያችንን ፕሮግራምና ህገደንብም በጉባኤው ተሳታፊዎች ተፈትሾና ተመርምሮ ጥልቅ ውይይት ከተደረገ በኋላ በርካታ የማሻሻያ ነጥቦች ታክለውበት ጸድቋል፡፡

የመጀመርያው የፓርቲያችን ጉባኤ እነዚህን መሰረታዊ አጀንዳዎች መርምሮ በሰፊው ከተወያየና ካጸደቀ በኋላ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ለቀጣይ ሦሥት አመታት ፓርቲውን በበላይነት የሚመሩ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን፣ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትንና የስራ አስፈጻሚ አባላትን ግልጽ፣ ነጻ፣ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ችሏል፡፡

እኛ የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያ ጉባኤ ተሳታፊዎች በወሳኝ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይተን የአገራችንን መጻዒ እድል በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በጉባኤያችን የተደረሱ ማደማደሚያወችንና የተቀመጡ አውራ አቅጣጫዎችን በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት በመያዝ እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ እረፍት የለሽ አመራር የሚሰጡ የፓርቲውን የቀጣይ ዘመን መሪዎች መርጠናል፡፡ ስለሆነም የአገራችንንና የህዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንት እና ጥቅም አክብሮ ማስከበር ከላይ እስከታች የሚገኘው የፓርቲያችን መዋቅር ግዴታ መሆኑን እያሳሰብን የሚከተለውን አቅጣጫ እና የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1ኛ. የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማስፋት እና በማጽናት የህዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ የፓርቲያችን ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የውስጠ ፓርቲ ጤንነታችንን መጠበቅ ከሌብነትና ከተደራጀ ስርቆት አንጻራዊ ነጻነቱን የጠበቀ የአመራር ስምሪት ማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን የተላበሰ ጠንካራ የፓርቲ መስተጋብር ለመፍጠር ወስነናል፡፡

ያለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ እቅዶቻችንን ማሳካትም ሆነ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለማንችል ለዚህ ዘርፍ የተለየ ትኩረት የምንሰጥ መሆኑን እናረጋግጣለን፤ ለዚህም ቃል እንገባለን፡፡

2ኛ. የየአገራችንን አንድነት እና የህዝባችንን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ መድረኩ የሚጠይቀንን እና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፡፡ ስለሆነም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ለአገራዊ አንድነት ተጠናክሮ መውጣት፣ለዜጎች ክብር እና ነጻነት እንዲሁም በህይወት የመኖር መብት መረጋገጥ እና የአካል እና የንብረት ደህንነት መከበር በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡

ስለሆነም አገራዊ መግባባት ማምጣት የሚያስችል አካታች ብሄራዊ ምክክር በማድረግ በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚያስችል ፈጣንና መላውን ህዝብ ያሳተፈ ምክክር በማድረግ በህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ዘላቂ እና የማያዳግም እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም በተባበረ ጥረት ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በመገንባት፣በህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም መሰረት ላይ የታነጸ አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡

3. በተጨባጭ ውጤት የሚገለጽ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እውን እንዲሆን በጋራ መረባረብ አለብን፡፡የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም የበለጸገ አስተሳሰብ ውጤት እንጂ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ እርስ በእርስ አለመከባበር፣ መዘላለፍ፣ በአደባባይ ላይ ሳይቀር ጸያፍ ድርጊት መፈጸም፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና ለእህትማማችነት የማይመጥን ጸረ አንድነት የሆነ ከፋፋይ ድርጊት መፈጸም የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጸር እንደሆነ ጉባኤያችን ያምናል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሀነት አገር መሆኗ ግልጽ ሆኖ እያለ ከእኛ ይልቅ እኔብቻ በሚል ተነጣይ አስተሳሰብ መጠመድ፣ ሽማግሌዎችን እና የማህረሰቡን ጉልሀን መዝለፍ፣ የቡድን መብትን አለማክበር፣ ብዝሀነትን ማጣጣል፣ የመንግስት ሹመኞችን ከግብረገብነት ባፈነገጠ መልኩ ማንቋሸሽ ኢትዮጵያዊ ልማድ ካለመሆኑም በላይ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ ኋላ ቀር ድርጊት በመሆኑ ድርጊቱን የሆነ ቦታ መግታት ካልቻልን አገራችንን ብዙ አመት ወደኋላ የሚጎትት እና በውጥን የሚያስቀረን የብልጽግና ጉዟችን እንቅፋት ነው፡፡

እርስ በእርስ በመቻቻል እና በመከባበር፣ ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እምርታዊ ለውጥ በማምጣት አገራችንን ወደፊት ሊያስፈነጥር የሚችል የተግባቦት ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡የፍትህ አካላት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚኖራቸውን አበርክቶ አስፍተውና አልምተው መተግበር አለባቸው፡፡ ለዚህም በጋራ መታገል ይኖርብናል፡፡ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡

ሌብነትን የማይሸከም አሰራር እና ፖለቲካዊ ከባቢ መገንባት የሁላችንም ግዴታ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለሆነም ከመላው ህዝባችን ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት አገር በቀል እሴቶቻችንን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ እርስ በእርስ በመከባበርና በመቻቻል በጅምር ላይ የሚገኘውን የአገራችንን ዴሞክራሲ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ቃል እንገባለን፡፡

4ኛ. ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማቋቋምና የአስር አመት ዕቅድ ትግበራ ስራችን ላይ ፈርጀ ብዙ ስራ በመስራት የአገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ የህዝባችንን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ በአጠቃላይ የህዝባችንን ኑሮ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ ማሻሻል አለብን፡፡

አፋጣኝ መፍትሄ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ፈጣን እርምጃ መውሰድ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ምንም እንኳን የአለም አቀፍ ሁኔታው ለገበያ ጉድለት መፈጠር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ወቅታዊ የሆነውን የህዝባችንን የኑሮ ውድነት ችግር ለማሻሻል ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን እናምናለን፡፡

የመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ በገቢና በወጭ ምርት ላይ የሚታይ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት የሚፈታበትን ትልም ከወዲሁ ቀይሶ የህዝባችንን ሸክም ማቃለል እንዳለብን በጉባኤው ተመላክቷል፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ የብዝሀ ልማት ዘርፍን ማጠናከር፣ በግብርና ልማት ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ማምጣት፣ ቢያንስ ከውጭ ወደውስጥ የስንዴ ምርትን የማያስገባ የግብርና አቅም መገንባት፣ የማዕድን ሀብታችንን አሁን ካለበት ወደፊት እንዲስፈነጠር ማድረግ፣ የኢንዱስትሪንና የቱሪዝምን እድገት ሊያረጋግጡ የሚችሉ አማራጮችንና ዘዴዎችን መከተል እንዳለብን ጉባኤያችን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ መሳካት አለባቸው ብሎ ባስቀመጣቸው የልማት አጀንዳዎች ላይ ቀን ከሌት ተረባርቦ ተስፋ ሰጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለተግባር ስኬታችንም ቃል እንገባለን፡፡

5ኛ. የአገራችንን ሉአላዊነት እንደወትሮው ሁሉ ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን፡፡ ምንም እንኳን ከውስጥም ከውጭም የሚፈታተኑን ኃይሎች በርካታ ቢሆኑም ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም የሚችል የውስጥ አቅም ለመፍጠር እየተረባረብን እንገኛለን፡፡

በተለይም ጦርነትንና ግጭትን የሚያስቀር ጠንካራ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንዳለብን ጉባኤያችን በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡

የታላቁን ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ አንድ አገራዊ ወሳኝ ተልዕኳችን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ብዥታዎችን ያለማመንታት መቅረፍ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ለጎረቤት አገሮች የምንሰጠውን ልዩ ትኩረት አጠናክረን በመቀጠል የቀጠናውን ትብብር ማሻሻል እና የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት የበለጠ ማጽናት አለብን ብለን እናምናለን፡፡

ድህረ ጦርነት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የመላውን ህዝባችንን ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ሳንታክት እንሰራለን፡፡ ዜጎች በርሀብና በድርቅ እንዳይጎዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ ወንድማማችንትንና እህትማማችነትን ማጎልበት፣ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችንን ከፍ ማድረግ፣ አንዳችን ለሌላችን ያለንን ፈጥኖ ደራሽነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

ስለሆነም በጦርነትና በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በቅድመ ጥናት እና በጥንቃቄ ላይ ተመስርተን ወደየቀያቸው የሚመለሱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለህዝባችን ሰላማዊ አኗኗር ስረ ምክንያት የሆኑ የሽብር፣ የጽንፈኝነት እና የማን አለብኝነት ዝንባሌዎችን በእንጭጩ እየቀጨን የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንዳለብን እናምናለን፡፡

በሁሉም አካባቢ የወደሙና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት አለም አቀፍ ጫናን ተቋቁሞ ሉአላዊነትን የሚያጸና ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫዎችን ለመከተል አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

6ኛ. የሀገራችን ፖለቲካ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ባለው ፋይዳ ልክ መቃኘት አለበት፡፡ አገራዊ አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣አገር በቀል እሴቶቻችንን ለላቀ ጥቅም የሚያውል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን የሚያቀል እንዲሆን መስራት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ ጠንካራ የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ስራ መስራት አለብን፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንን በማጠናከር የአንደኛውን ህመም ሌላኛው የሚጋራበት፣ በሌላኛው ጫማ ላይ ቁሞ ቁስልን የሚረዳበት እርስ በእርስ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመቻቻል ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል መገንባት አለብን ብለንም እናምናለን፡፡

ዴሞክራሲን እየናፈቅን ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል የማንፈቅድ ከሆንን ዴሞክራሲ በዘፈቀደ አይገኝም፡፡

ብልጽግናን እና የህዝባችንን ኑሮ መሻሻል እየተመኘን ነገር ግን ሁሉ ነገራችን ፖለቲካ ብቻ ከሆነ ያሰብነው አይሳካም፡፡

ሰላምና ጸጥታን እየፈለግን ነገር ግን በየመንገዱ ለጸብ፣ ለክርክርና ለጥላቻ መሰረት የሚሆን ስድብ፣ ዘለፋ፣ ስም ማጥፋት እና አብሪተኝነትን የምናስቀምጥ ከሆነ ሰላም በምኞት ብቻ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስለሆነም በማህበራዊ ድረገጽ ትስስርም ሆነ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ዘወትር የምንናፍቀው የህዝባችን ሰላም እና የአገራችን አንድነት እንዲሳካ መረባረብ አለብን፡፡

በመጨረሻም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤያችን በመከረባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ለህዝባችን ሁለንተናዊ ሰላም ደህንነት እና ተጠቃሚነት መረጋገጥ በፍጹም ቁርጠኝነት የምንሰራ መሆኑን እያረጋገጥን ጉባኤያችን በታላቅ ስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን ለመላው ህዝባችን እናበስራለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለሁሉም የእምነት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ለአገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ ለምሁራን እና ለንግዱ ዘርፍ የማህበረሰብ አባላት፣ ለባለሀብቶች፣ ለወጣቶች እና ለሴቶች፣ አገራችሁን በተለያዩ መስኮች ለምታገለግሉ ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፌዴራል፣ በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋና በሁሉም ክልሎች የምትገኙ የፀጥታ አባላት፣ በውጭ አገር ለምትገኙ የዲያስፖራ አባላት ፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አገር የሚጸናው፣ የሚያድገው እና የሚበለጽገው በሁሉም ዜጋ የጋራ እርብርብ ነው በሎ ፓርቲያችን ብልጽግና ያምናል፡፡ ስለሆነም እናንተን ሳንይዝ የምናሳካው አንዳችም ነገር ስለሌለ በሁሉም መስክ የተለመደውን አገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በጋራ እንድንቆም የአደራ መልዕክታችንን ስናስተላለፍ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

ብዝሃነት ጌጣችን ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው !!!

መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ
Leave a Reply