Site icon ETHIO12.COM

ወጣቱ ለሰባት ዓመታት እንቅልፍ ባለመተኛት ሪከርድ ያዘ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ “አራት አመት ተኩል ዕንቅልፍ ያልተኛው ኢትዮጵያዊ የዓለምን ክብረወሰን ለመስበር አቅዷል” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ መስራቱ ይታወሳል።

ወጣት ቁምላቸው አሰፋ፤ አሁን ላይ በአፍሪካ ድንቃ ድንቆች መዝገብ ላይ ለ7 ዓመታት እንቅልፍ ባለመተኛት ሪከርድ ይዟል።

የአፍሪካ ድንቃ ድንቆች መዝገብ ለወጣቱ በሰጠው የምስክር ወረቀት አቶ ቁምላቸው አሰፋ ተጠንቶ ባልታወቀ ምክንያት ለ7 ዓመታት ያክል እንቅልፍ ባለመተኛቱ የክብር ሰርተፍኬት እንደሰጠው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ስለወጣት ቁምላቸው ይህን ብሎ ነበር

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት ቁምላቸው አሰፋ ለአዲስ ዘመን እንደገለጸው፤ ከሚያዚያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረ አጋጣሚ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም።

የእንቅልፍ እጦት ቢኖርበትም በምሽት መኝታው ላይ አረፍ ለማለት ሲፈልግ ግን የሰውነት ሙቀቱ እንደሚጨምርና ጎኑን ውጋት ይሰማዋል። እንግዳ ጉዳዩ ችግር እየፈጠረበት ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ያለእንቅልፍ የመቆየት የአለም ክብረወሰን ለመስበር አቅዷል።

አብዛኛውን ምሽት የእጅ ስልኩን በመነካካትና ቴሌቪዥን በማየት እንዲሁም የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸም እንደሚያሳልፍ የተናገረው ወጣት ቁምላቸው፤ እንቅልፍ ባያገኝም የዕለት ተዕለት ስራውን በሰላም ከመከወን እንዳላገደው ገልጿል።

አቶ ቁምላቸው በ2008 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ በተዘጋጀ የባህል ፌስቲቫል ላይ የባህል ቡድን በመምራት አሸናፊ እንደነበረ ገልፆ፤ በጊዜው የባህል ቡድኑ አባላት መኝታ ክፍል ሲይዙ እርሱም አንድ ክፍል ውስጥ እንቅልፍ መተኛቱን አስታውሷል።

በጊዜው ግን አንድ ወጣት አልጋ ባለማግኘቱ የአካባቢው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወደእርሱ ደውሎ አልጋ ያላገኘ ወጣት መኖሩን ገልጾ አብሮት እንዲያድር እንዲተባበረው ይጠይቀዋል።
እሺታውን የገለጸው አቶ ቁምላቸውም ወጣቱን ተቀብሎ አብሮ ቢተኛም እንቅልፍ ግን ሊወስደው አልቻለም።

በዚያን ቀን ከሰው ጋር በመተኛቱ እንቅልፍ ሊወስደው እንዳልቻለ ያሰበው አቶ ቁምላቸው፤ በሌሎች ቀናት በቤቱም ብቻውን ለመተኛት ቢሞክርም እንቅልፍ ሊወስደው እንዳልቻለ አስረድቷል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተርጫ ካምፓስ የጤና ሳይንስ መምህር አቶ ውብሸት ጌታቸው፤ የወጣቱን የእንቅልፍ ችግር ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት የእንቅልፍ መድሃኒት እንዲወስድ ቢደረግም እንቅልፍ ሊይዘው እንዳለቻለ ገልጸው ነበር።

በጌትነት ተስፋማርያም (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version