ያዕቆብ ወልደ ማርያም – 57 ዓመታት ያገለገሉት አንጋፍው ጋዜጠኛ ስንብት ተፈጸመ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባልደረባ የነበሩትና የዘኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ስርዓተ ቀብር ዛሬ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። አቶ ያዕቆብ የ94 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ናቸው።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም የጋዜጠኝነቱን ዓለም የተቀላቀሉት በ1951 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በሚታተመው በዘኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ሲሆን፤ የዚህ ጋዜጣም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ እንደነበሩ ታሪካቸው ይናገራል።

ከዘኢትዮጵያን ሔራልድ በተጨማሪ በቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፤ በመነን፣ የካቲት፣ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፣ ሪፓርተር እንግሊዘኛው፣ አዲስ ትሪቡን መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነትና በአዘጋጅነት ከ57 አመታት በላይ አገራቸውን አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግስታት 50ኛ የምስረታ በዓሉን ሲያክብር ጋዜጠኛ ያዕቆብ ኒውዮርክ ሄደው ታድመዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሤን ንግግሮች በእንግሊዝኛ አየተረጎሙ ለውጪው ማህበረሰብ መልዕክቱ እንዲደርስ ያደርጉ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም በሚድያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት አሸናፊም ነበሩ።

የቀድሞው የኢፕድ ባልደረባ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም በተወለዱ 94 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸው ይታወሳል። የቀብር ሥነስርዓታቸው ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ነሀሴ17 ቀን 2015 ዓም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መፈጸሙን ኢፕድ ዘግቧል።

ሪፖርተር ጋዜጣ በባልደረቦቻቸው ይህን ጽፎላቸዋል።

አቶ ያዕቆብ በ94 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉት ነሐሴ 16 አጥቢያ ላይ መሆኑን ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ከአምስት አሠርታት በላይ ባስቆጠረው የጋዜጠኝነት ጉዟቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (ቅድመ 1967) ከሔራልድ ጋዜጣ በመቀጠል በአዲስ ሪፖርተርና መነን መጽሔቶች፣ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ሠርተዋል፡፡

በዘመነ ደርግ (1967 – 1983) በየካቲት መጽሔት ዋና አዘጋጅ የነበሩ ሲሆን፣ ጡረታ ሊወጡ መንፈቅ ሲቀራቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው ሠርተዋል፡፡

የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ በመጣው የግል ሚዲያው ዘርፍ በተለይ በሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር እየታተመ በሚወጣው ዘሪፖርተር ጋዜጣ በከፍተኛ አዘጋጅነትና አርታዒነት ከ15 ዓመታት በላይ የሠሩት አቶ ያዕቆብ፣ በተለይ ‹‹ዘ ስፔክታተር›› በተሰኘው ዓምዳቸው የሚያቀርቧቸው ሒሳዊ መጣጥፎች አድናቆትን ያተረፉ ናቸው፡፡

See also  ጎበዜ ሲሳይ ከጅቡቲ ተላልፎ መሰጠቱን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል አስታወቀ

በቀዳሚው የጋዜጠኝነት ሕይወታቸው በአዲስ ሪፖርተር መጽሔትም ከዋና አዘጋጅነታቸው ባሻገር ‹‹ዘ ቪው ፍሮም ፊንፊኔ›› ትኩረት ይስብ እንደነበር ይወሳል፡፡

አቶ ያዕቆብ ግለ ታሪካቸውንና የተመረጡ መጣጥፎቻቸውን የያዘ መጽሐፍ በ1995 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ አሳትመዋል፡፡

ከአባታቸው አቶ ወልደ ማርያም ሹባ ሌቃ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተ ሚካኤል ሰንበቶ ሰኔ 12 ቀን 1921 ዓ.ም.፣ በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ነቀምት ከተማ የተወለዱት አቶ ያዕቆብ፣ በነቀምት የተፈሪ መኰንን የአንደኛ ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማዕረግ አጠናቀዋል፡፡ ባገኙት ስኮላርሺፕ ወደ ለንደን በማቅናት ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ለሃምሳ ስድስት ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገሉት አቶ ያዕቆብ ቀዳሚው የሥራ ሕይወታቸው የጀመረው በአዲስ አበባ የአምሃ ደስታ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪ በመሆን ነው፡፡

ነፍስ ኄር አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም ባለትዳርና የሰባት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡

Leave a Reply