ETHIO12.COM

ዝርፊያ ከትናንት እስከ ዛሬ የትህነግ ባህላዊ ጨዋታ

ከሰሞኑ የሽብር ቡድኑ ህወሐት በመቀሌ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የዓለም የምግብ ድርጅት መጋዘን በኃይል ሰብሮ በመግባት ነዳጅ እና ሌሎች ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን መዝረፉ ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳን ድርጊቱ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ቀልብ የሳበ እና ያሳዘነ ድርጊት ቢሆንም መሰል ድርጊቶች ግን ለህወሐት አዲስ እና እንግዳ አይደሉም፡፡

ወቅቱ 1970ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ የሰሜኑ ኢትዮጵያ በተለይም ትግራይ እና አዋሳኝ አካባቢዎች ትህነግን እና ድርቅ ጥሎባቸው የከፋ ርሃብ ተከስቷል፡፡ እናቶች የልጆቻቸውን የርሃብ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ትንቅንቅ መመልከት ተስኗቸው ቀድመው ወድቀዋል፡፡ ሕይወታቸው ያለፉ እናቶችን ጡት እንደነከሱ ተዘቅዝቀው ሞታቸውን የሚጠባበቁ፤ መናገር እና ማልቀስ የተሳናቸው ህጻናት ቁጥር ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ክስተቱን ለመስማት እና ለማየት እድል ያገኙ ሁሉ ልባቸው ተሰብሯል፡፡

ዓለም በወቅቱ ተደጋጋሚ ጦርነት እና ድርቅ ተባብረው በሰሜን ኢትዮጵያ በፈጠሩት የድርቅ እና የርሃብ አደጋ ልባቸው ክፉኛ ተነክቷል፡፡ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሁነቶችን እየፈጠሩ በርሃብ አደጋ ለተጠቁ ወገኖች ገቢ የሚያሰባስቡ በጎ አድራጊዎች ከዚህም ከዚያም ቢራወጡም የተፈለገው ድጋፍ ግን ለተባለለት ዓላማ በተገቢው መንገድ መድረስ አልቻለም፡፡

ለነፍስ አድን ርብርቡ ዋና እንቅፋት ደግሞ ህወሐት ነበር፡፡ መንገድ እየዘጋ፣ ለድጋፍ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችን እየዘረፈ እና እያጠቃ፤ እንደምንም የደረሰውን ድጋፍም በድብቅ እየከዘነ ለተቸገሩት እንዳይደርስ አደረገ፡፡ ትግራይ ውስጥ በርሃብ አለንጋ የሚቀጣው ሕዝብ በየጎዳናው ወድቆ የተላከ የእርዳታ ቁሳቁስ ግን ሱዳን ውስጥ በግልጽ ይቸበቸብ ነበር፡፡ ይህ አስነዋሪ እና አሳፋሪ ድርጊት በአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) እና መሰል ድርጅቶች ዘግይቶም ቢሆን ቢጋለጥም ቅሌት ለህወሐት ብርቁ አልነበረምና አልደነቀውም፡፡

ህወሐት በሱዳን ድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ሕቡዕ ተልዕኮ የተሰጠው እና ማሌሊት በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ቡድን ዋና ተግባራትም በርሃብ አለንጋ የሚቀጡ የትግራይ ዜጎችን ወደ ሱዳን ማስወጣት እና የሚሰጡትን እርዳታ ሽጦ መሳሪያ መግዛት ነበር፡፡ ህወሐት ከወታደራዊ መንግስት ደርግ ጋር በነበረው ጦርነት የመሳሪያ ችግር እንዳይኖርበት ካደረጉት መንገዶች አንዱ ይህው የእርዳታ ምግብን ሽጦ የጦር መሳሪያ መግዛት አስነዋሪ ስትራቴጂው ነበር፡፡ በጦርነቱ ሕይዎታቸውን ካጡት ትግራዊያን ባልተናነሰ መልኩ በህወሐት ሴራ በርሃብ ተቀጥተው ያለፉት ትግራዊያን በርካታ ነበሩ፡፡

በዚህ መልኩ ወደ ስልጣን የመጣው ህወሐት ሀገር የመምራት እድል አግኝቶም “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንዲሉ ኢትዮጵያዊያንን ከመስረቅ እና ከመልከስከስ የቦዘነበት ወቅት እንዳልነበር ለኢትዮጵያዊያን ድብቅ አይደለም፡፡ ህወሐት በዘመኑ ሀገር እየመራ መርከብ ሰርቋል፡፡ ሕዝብ እያሥተዳደረ ድንበር ዘርፏል፡፡ በእርዳታ እና በብድር ስም ከውጭ የሚመጣ ድጋፍ አየር ባየር ተመልሶ ማረፊያው ከአበዳሪዎቹ ኪስ እና ካዝና ውስጥ ነበር፡፡ በህወሐት ዘመን የምኒስተሮቹ ተቀዳሚ ተግባር ድለላ እና ኮሚሽን ማሰባሰብ ነው ብለው የሚተቹት በርካቶች ነበሩ፡፡

ታዲያ ከሰሞኑ መቀሌ ውስጥ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ሰብሮ በመግባት ነዳጅ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁሶችን መዝረፉ ዓለምን ስለምን እንደ አዲስ አነጋገረ ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋ ይሆናል፡፡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓዎር ትናንት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ህወሐት በመቀሌ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ድርጅት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ አሳፋሪ እና የሚወገዝ ነው ብለውታል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አገልግሎት የሚውል 150 ሺህ ጋሎን ነዳጅ መዝረፍ በትግራይ ንጹሃን ላይ በጭካኔ መፍረድ ነው ብለውታል፡፡ ምንም እንኳን ዳይሬክተሯ በህወሐት ዘረፋ ልቤ ተነክቷል ቢሉም ትግራዊያን ግን ይህንን ከተላመዱት ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ህወሐት የዘረፈውን ስለመመለሱ ቀርቶ ሌላ ስላለመዝረፉ እንኳን እርግጠኞች ባይሆኑም የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተሯ ህወሐት የዘረፈውን ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመልስ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞችን ከማንገላታት እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፤ ሰሚ ካለ፡፡

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ፣ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ድጋፍ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊዝ “ህወሐት በመቀሌ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን በኃይል ሰብሮ በመግባት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉን ስሰማ ደንግጫለሁ” ብለዋል፡፡ ምን አልባትም ኢትዮጵያዊያን የድርጅቱን ጥንተ ስሪት እና ባህሪ ስለሚያውቁ ላይደንቃቸው ቢችልም፡፡ 150 ጋሎን ነዳጅ መዝረፍ ማለት ትርጉሙ በሚሊየን በሚቆጠሩ ንጽሃን ላይ መፍረድ ነው ያሉት ሚስተር ግሪፊዝ ድርጊቱን አደገኛ ሲሉ ተችተውታል፡፡

ጉዳዩን ላለፉት ስድስት ወራት በጦርነት ውስጥ የምታሳልፈው ሩሲያም አሳፋሪ እና አደገኛ ስትል የህወሐትን ዘረፋ አውግዛዋለች፡፡ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢብጊኒ ተርኪኺን ዛሬ ህወሐት የዓለም ምግብ ድርጅት ነዳጅን ዘርፎ ነገ የሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ አልደረሰም ሲል ይወቅሳል ሲሉ ተችተውታል፡፡ ድርጊቱን ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እና ነውር ሲሉ ያጣጣሉት አምባሳደሩ በየትኛውም ሀገር የማይደገፍ ተግባር ነው ብለውታል፡፡

150 ሺህ ጋሎን ነዳጅ መቀሌ ውስጥ ተዘረፍኩ ሲል ስሞታውን ለዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ያሰማው የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ዘረፋውን አስነዋሪ እና ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ዳይሬክተሩ የተዘረፈው ነዳጅ ይመለስ ካልሆነ ግን ውጤቱ በንጹሃን ላይ የከፋ ነው ብለዋል በማስጠንቀቂያቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳን ህወሐት በመቀሌ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን መዝረፉን ዓለም ቢያወግዝም ህወሐትን “አበጀህ የእኛ ልጅ” የሚሉም ወፈፌዎችም አልታጡም፡፡ ግዙፉ የዓለም ጤና ድርጅት መርህ “ከጦርነት የጸዳች ዓለም” የሚል ቢሆንም፤ የወቅቱ የድርጅቱ መሪ ግን ከድርጅቱ መርሆው በተጻራሪ ቆመው “አትነሳም ወይ” ሲሉ መደመጣቸው የድርጅቱን መልካም ስም እና ዝና አደጋ ውስጥ ዘፍቆታል፡፡

ሰውየው በቲወተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “አንተ ለራስህ እስካልተነሳህ ድረስ፤ ሌላ ማንም አይነሳልህም” ሲሉም በገደምዳሜው ዘረፋው የነጻናት ትግል ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ያም አለ ይህም ግን ህወሐት የንጹሃን ሞት እና ርሃብ ጉዳዩ እንዳልሆነ ለዓለም ሕዝብ በተግባር በተደገፈ እርምጃ አሳይቷል፡፡ ትናንት የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አልቀረበልኝም የሚለው ወቀሳ እና ለቅሶ ዓለማው ምን እንደነበር ለአላቃሾቹ ሳይቀር ግልጽ የሆነላቸው ይመስላል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – (አሚኮ)

Exit mobile version