Site icon ETHIO12.COM

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ክልከላ በኢትዮጵያ

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው በህግና ይህን መብት ለመገደብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሲሆን ይህ መብት ከሚገደብባቸው ምክንያቶች መካከል የሌላን ሰው መብት ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሞራል (Public morals) ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት (Public order) ለመጠበቅ እንደሆነ በዚሁ ኮንቬንሽን ላይ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

መግቢያ

በአለም አቀፍም ሆነ በሀገር ደረጃ ማንኛውም ሰው በነጻነት የመናገርና የመሰለውን ሀሳብ የመግለጽ መብት አለው። ይህ በሀገራችን ህግ መንግስት እንዲሁም ሀገራችን ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች የህግ ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው፡፡ ሆኖም እነዚሁ የሰብአዊ መብት ሰነዶች መብቱ በጠባቡም ቢሆን ሊገደብ ስለሚችልበት ሁኔታ አመላክተዋል፡፡ በዚህ መነሻነትም በሀገራችን በ2012 ዓ.ም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012 እንዲወጣ ተደርጓል። በዚህ አጭር ጽሁፍ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለውን የህግ ጥበቃና የሚገደብበትን ሁኔታ እንዲሁም በሀገራችን የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በተመለከተ ያለውን ክልከላ እንመለከታለን። ትርጉም

የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከልከል የወጣው አዋጅ በአንቀጽ 2 ላይ መሰረታዊ የሆኑ ቃላትን ትርጉም የሰጠ ሲሆን የጥላቻ ንግግር ማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፤ ብሔረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆነ ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ መልእክት የማሰራጨት ተግባር ነው በማለት አስቀምጦታል፡፡

ሐሰተኛ መረጃ ማለት ደግሞ መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግርን በማናቸውም መንገዶች ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ ማድረግ ነው በሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የህግ ጥበቃና የሚገደብበት ሁኔታ

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃም እውቅና ተሰጥቶት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራትም ተስማምተው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1966 ዓ.ም አለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኮቨንሽን (ICCPR) እንዲወጣ ተደርገል። በዚህ ኮንቬንሽን ከተካተቱ ሰብአዊ መብቶች መካከል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት (freedom of expression) በአንቀጽ 19 ስር ተደንግጎ ይገኛል።

ማንም ሰው በፈለገው መንገድ ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለው ሁሉ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችልም በአለም አቀፍ ሰብአዊና ፖልቲካዊ መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 19(3) ስር ተደንግጓል። ይህ ኮንቬንሽን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንደሚገደብ በመግለጽ ብቻ አላለፈውም በምን ሁኔታና እንዴት እንደሚገደብ አስቀምጦት ይገኛል፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው በህግና ይህን መብት ለመገደብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሲሆን ይህ መብት ከሚገደብባቸው ምክንያቶች መካከል የሌላን ሰው መብት ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሞራል (Public morals) ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት (Public order) ለመጠበቅ እንደሆነ በዚሁ ኮንቬንሽን ላይ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል እንደመሆኗ የአለም አቀፍ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብት ኮንቬንሽንን (ICCPR) ፈርማ ያጸደቀች በመሆኑ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በህገመንግስቱ እንዲካተት ተድረጓል፡፡ በኢ.ፍ.ድ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 29 ስር እንደተደነገገው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በማንኛውም መንገድ እና ስልት ማከናወን የሚችል ሲሆን ይህ መብት በህግ የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሊገደብ እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው ህግ አላማ

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 በዋናነት ሆነ ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሃገራዊ አንድነት፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሀነትና ለእኩልነት ጠንቅ በመሆኑ በሶሰት አላማዎች ምክንያት አዋጁ ሊወጣ ችሏል፡፡ እነዚህ አላማዎችም

• ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሔርን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማድረግ፤
• መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበርና መግባባትን ማበረታታትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጎልበት፤
• የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃና መረጃዎችን ስርጭት መበራከትን ለመቆጣጠርና ለመግታት ነው በሚል ተቀጧል። የወንጀል ተጠያቂነት

የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከልከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 መሰረት የጥላቻ ንግግር ማድረግና ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት በወንጅል እንደሚያስጠይቅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት፤-

1ኛ ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን ማለትም በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፡ ብሔረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑ ተደንጓል። በመሆኑም ይህንን የጥላቻ ንግገር ያደረገ ማንኛውም ሰው እስከ 2 አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር አንድ መቶ ሺ ብር ያልበለጠ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን በተደረገው የጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ያስቀጣል።

2ኛ ማንኛውም ሰው የሐሰት መረጃን ማለትም መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግርን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ያሰራጨ እንደሆነ እስከ አንድ አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር ሃምሳ ሺ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡ በተፈጸመው ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ከሁለት እስከ አምስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።

በሌላ በኩል የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር አንድ መቶ ሺ ያልበለጠ መቀጮ የሚያስቀጣ ሲሆን በጥላቻ ንግግር ወይም በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል ለፍ/ቤቱ ስልጣን ሰጥቷል። በወንጀል የማያሰጠይቁ ሁኔታዎች

በዚህ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 6 መሰረት አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሐሰት መረጃ ተወስዶ ማሰራጨት የማይከለከለው ወይም የወንጀል ተጠያቂነትን የማያስከትለው-
 የትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር አካል እንደሆነ፤
 የዜና ዘገባ፤ ትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል እንደሆነ፤
 የኪነጥበበ ፣ ትወና ወይም መሰል የሥነጥበበ ውጤት ከሆነ፣
 የሃይማኖታዊ አስተምህሮት አካል እንደሆነ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ንግግር እንደ ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ተወስዶ የማይከለከለው ንግግሩን ያሰራጨው ወይም ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በሱ ሁኔታ ካለ ሰው ማለትም ከአንድ ምክንያታዊ ከሆነ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ወይም ንግግሩ የጥሬ ሐቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ የወንጀል ተጠያቂነትን አያስከትልም።

በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ማህበራዊ ሚዲያን ሲጠቀምም ሆነ በማንኛውም መንገድ ሃሳቡን ሲገልጽ የሚያደርገው ንግግረም ሆነ መረጃ ሲያሰራጭ የወንጀል ተጠያቂነትን እንዳያስከትልበት ከፍተኛ ጥንቃቄ የማድረግ፣ የማህበራዊ ሚድያ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች የሚያደርጉትን ንግግርም ሆነ መረጃ ስርጭታቸው እውነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ የመስጠት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በዚህ አዋጅ የተቀመጡ ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ሪፖርት የማዘጋጀት እና የሐሰት መረጃ ስርጭትና ጉዳትን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ የማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ የማድረግ ሀላፊነት የተጣለባቸው በመሆኑ ሁሉም የየራሱን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡ በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

Exit mobile version