Site icon ETHIO12.COM

ተመልሶ ተንቤን? የትህነግ ስትራቴጂ

የመከላከያ ሰራዊት የሚመራው ጥምር ጦር እልቂት እንዳይኖር ከመስጋት አንጻር ፍጥነቱን ካልቀነሰ በስተቀር መቀለ እንዳይገባ ሊያግደው የሚችል ሃይል የለም። ነገሩ ለጊዜው አብቅቷል። በሁሉም በኩል ተቆልፎ በአንድ መተንፈሻ ሽሽት ብቻ ሆኗል። ህዝቡም ሰራዊቱ ገብቶ በተገላገልን የሚል ስሜት ይታይበታል። የሚሻለው እሱ ነው። “ተመልሶ ወደ ተንቤን” አለና ከላይ ያለውን መረጃ ያካፍለኝ የዛው አካባቢ ወዳጄ ስልኩን በብስጭት ዘጋው። “ይህቺን ጥያቄማ ይመልሷታል” ሲሉ የጽሁፍ አሳብ ላከልኝ። በዛው ይህችን አጭር አሳብ ጫርኩ።

ነገሮች ተገለባብጠዋል። ትህነግ ሲል የነበረው ሁሉ ምን ያህሉ ተግባር ላይ ታየ የሚለው ወደፊት የሚሰላና የሚጠና የመጪው ትውልድ መማሪያ ይሆናል። ምንም ሆነ ምን፣ ያለቀው አልቆ፣ የወድመው ወድሞ፣ የተፈናቀለው ተፈናቅሎ፣ የተሰደደው ተሰዶ፣ የራበው ሁሉ ተርቦ፣ የተዘረፈው ተዘርፎ፣ ምን ያልሆነ ነገር አለ? ምድር ላይ ያለ መከራ ሁሉ ምስኪኑ ህዝብ ላይ ሆነ። ከተራ የጎሰኝነት እሳቤ ለአፍታም ቢሆን ፈቀቅ በማለት “ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ማን አጥጋቢ መልስ ይሰጣል?

አንድ የደህንነት ሹም ጌታቸው አሰፋን “አላስረክብም” ብሎ ወደ መቀለ ጠቅልሎ የገባው የትህነግ አመራር ያንንም አድርጎ ልክ እንደ ማንኛውም ክልል ለመኖር እንዴት ተሳነው? ለምስ ተሳነው? ይህ ሁሉ ሲሆን በጭፍን ከመመራት ቆም ብሎ የሚመረመር፣ አርቆ የሚያይ፣ የነገውን የሚተነብይ እንዴት ጠፋ? ይህ አድሮም ቢሆን የሚጠየቅ ጥያቄ ነው። ጥያቄው ደግሞ “ለምን ሞትን” የሚለው የነገር ጭቦ ሲቀጣተል ይሆናል።

የዛሬ ሰላሳ ዓመት በአስር ሺህ የሚቆተሩ የትግራይ ልጆች ሞቱ ተባለ። ውጤቱ መንግስት መሆን በመቻሉ ሟቾች ” ጀግኖች” ተባሉና ቤተሰብን ” የጀግና አባት/ እናት” የሚል ስያሜ ባለቤት አደረገ ተባለ። በዚሁ ወኔና ስብከት ” ጦርነት ባህልህ” እየተባለ ሲነገረው ህዝቡም ደረቱን የሚነፋ ሆኖ አርፈው። ለጦርነት በልዩ ትዕዛዝ የተሰሩ ሆነው የሚሰማቸው ትውልዶችንም አፈሩበት። በሄዱበት በጥይት የሚጫወቱ ህጻናትን በአደባባይ አሳዩን።

ዛሬስ? ዛሬ እንደሚሰማውና ወደፊት ጊዜ ይገልጠዋል እንደሚባለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በሚሊዮን የሜገመት ወይም በበዙ መቶ ሺዎች የሚሰላ የሰው ልጅ አልቋል። ከየትኛው ወገን ብዙ ረገፈ የሚለውና አሃዙን ለጊዜው ቤትና የናት አንጀት ይቁጠረው። ወልዳ እንዳለ እምሽክ ያሉባት እናት እሮሮ ይየው። ግን ይህ ሁሉ የሆነው ለምን ይሆን?

አሁን እንደሚሰማው ነገ የሰላም አማራጭ ንግግርሩ እንደሚደረግ ነው። ማረጋገጫውን አሜሪካ ሰጥታለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቲውተር አውዳቸው የደቡድ አፍሪካንና የኬንያን ፕሬዚዳንቶች ከደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ስለ ድርድሩ ስኬታማነት መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

ይህ ሁሉ ሕጻን …

እንግዲህ ከላይ ያሉት ጥያቄዎች ከንግግሩ በፊት ቢቀርቡ የትህነግ አመራሮች ምን ያላሉ? አንድ የትግራይ እናት ከንግግሩ መጀመር በፊት ” ልጆቼ የሞቱት እዚህ መጥታችሁ ለመወያየትና ለመጨባበጥ ነው? ለምን አገር ቤት እናቶች እያለቀሱ ሲለምኗችሁ እምቢ አላችሁ…” ቢሉ ምን ምላሽ ያገኙ ይሆን? አንድ የአማራ ገበሬ ወይም የአፋር ሽማግሌ “መንደራችን ድረስ መጥታችሁ ስለምን ገደላችሁን? ምን በደልናችሁ?” ቢል የጌታቸው አንደበት መልስ አለው? ዛሬም ያነበንባል?

ይህን ጽሁፍ ስጽፍ ትህነጎች በአንድ ጎን፣ እነ አቶ ደምቀና ሬድዋን በሌላ ጎን ሆነው ጉሮሯቸውን እየጠራረጉ ሲነጋገሩ በአይነ ህሊናዬ እየሳልኳቸው ነው። የጀነራል ጻድቃን መመሳደቅም የታወሰኝ የዛኔ ነው። እነ አቶ ሬድዋን ይህን ቪዲዮ እንዲከፈት ጠይቀው የትህነግ ሰዎች ለአፍታ ቢያዩት ስልም አስቤ ነበር።

ሌላው ይህን ጽሁፍ ስጽፍ የመከላከያ ሰራዊት ወደ መቀለ መዳረሱን ስምቼ ነው። እንግዲህ የትህነግ ወኪሎች መቀለ በር ላይ /ሲያድርና ሲነጋ የሚሆነው አይታወቅም/ ቆሞ እየጠበቀ ያለን ሰራዊ እዚህ ደረጃ ደርሶ ምን ጉዳይ ቢነሳ “አይሆንም፣ አናደርገውም” ሊሉ ይችላሉ? ጻድቃን በዚህች ያያዝኳት ቪዲዮ ላይ ያሉትን አቶ ደመቀ ገልብጠው ቃል በቃል ቢደግሙላቸውስ? ምን ይላሉ? ምን ያመጣሉ? የትግራይ ህዝብ የወደፊት ጥያቄ መሰረቱን የሚተክለው እዚህ ላይ ይመስለኛል።

ይህ ሁሉ እልቂት፣ መከራና ረሃብ ተመልሶ ተንቤን በረሃ ለመግባት? እንጥፍጣፊ አቅም እንኳን ሳይኖር ተንፍሶ ለንግግር ብሎ መቀለን ለቆ ለመውጣት? ወይስ ምን ይሉታል? መንግስት ቢተው ህዝብ የማይተወው ጉዳይ እምብርቱ ይህ ነው።

በአራት ዙሩ ውጊያ ስንት የትግራይ ወጣት አለቀ? ስንቱ ተስፋ ቆረጠ፣ የስንቱ አካል ጎደለ? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሚቻለው አካላ ትህነግ ውስጥም ሆነ አጫፋሪዎቹ መካከል አይኖርም። እናም ጥያቄው እሳት ሆኖ ከመንግስት የተረፉትን እንደሚበላ ጥርጥር የለም። ተወደደም ተጠላም ትግራይ ኢትዮጵያ ጉያ ውስጥ ሆና በወግኖቿና በአገሯ ድጋፍ ትጽናናለች። ትድናለች። ሃዘኗንም ፍትህ አንግሳ ተረሳለች። ትግራይ እንደገና ዙሪያዋን ወዳጆቿ ከበዋት ፈገግ ትላለች። የትግራይ ህዝብ ከአማራና አፋር እንዲሁም ኤርትራ ህዝብ ጋር ገንፎ ይጎራረሳል። ማታድ ይዋዋሳል። እንጎቻ ያነጉታል። ዘርቶ ይቅማል። እሸት “ቅመሱልኝ” ብሎ ይልካል።

በቀጣይ ከመንግስት ወገን ሳለው የምለው ይኖረኛል። በደፈናው ግን ነገ ከንግግሩ ብዙም አዲስ ነገር ባልጠብቅም፣ ሁሉም ቀድሞ ስለተባለ ነው፣ መንግስት እንደ መንግስት ሆደ ሰፊ፣ መሃሪና ታጋሽ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ከገባበት ሰው ሰራሽ ጫካ እንዲወጣ ሁሉንም በቀናነት አድርጉ አላለሁ። ትህነግና ሕዝብ የሚለይበትን ወንፊት ግን በቅጡ መርመሩት። በሽንቁር ወንፊት ሲነፋ እብቁ አብሮ ይወራዳልና የትግራይ መከራ እንዲያበቃ፣ የጎረቤቶቿም ሰላም እንዲከበር ጭንቁር ያለበት ወንፊት እንዳያሲዟችሁ ተአተንቀቁ።

ሰናይት አገኘሁ

Exit mobile version