Site icon ETHIO12.COM

በእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ክስ ለ5ተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው


በነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የክስ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች ያቀረቡት የሕገ መንግስታዊ ትርጉም ጥያቄዎች ከፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ መልስ ባለመቅረቡ ምክንያት ለ5ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

ተለዋጭ ቀጠሮውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ሕገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

በዛሬው ቀጠሮ በነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የክስ መዝገብ የተካተቱ፤ አምባሳደር ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ፣ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔን ጨምሮ አጠቃላይ 16 ተከሳሾች እና የ3 ድርጅቶች ጠበቃ ከታደለ ገ/መድህን ጋር በችሎት ቀርበዋል።

የካሌብ ኦይል ኢትዮጵያ ተወካይ (ጠበቃ) ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ችሎቱ በባለፈው በጥቅምት 22 ቀን በነበረ ቀጠሮ ሕገ መንግስታዊ ትርጉም የሚፈልጉ ጥያቄዎች ላይ የፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ የሚሰጠውን መልስ ለመጠባበቅ የተሰየመ ቢሆንም፤ መልሱ ግን ዛሬም ለ5ኛ ጊዜ ሳይቀርብ ቀርቷል።

በዚህም መነሻ ጠበቃ ታደለ ገ/መድህን፤ ”መልሱ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጠይቀን ከአጣሪ ጉባዬው መልስ አልተሰጠንም“ ያሉ ሲሆን፤ ”የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ ይዞት የሚመጣው ውጤት ስለማይታወቅ ውጤቱን መጠባበቅ ይሻላል ”ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በኩልም ”ውጤቱ ባልታወቀበት ኹኔታ ትዕዛዝ ሊሰጥበት የማይችል በመሆኑ ውጤቱን መጠባበቅ ይገባል ”ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

ከተከሳሾቹ መካከል 19ኛ ተከሳሾ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዬን የጠየቅነው ጥያቄ ወደ ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዬ መሄድ አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን እራሱ ፍርድ ቤቱ ቢወስንልን የሚል አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ በሌላኛው ተከሳሽ አንባሳደር ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ በኩል ግን፤ አጣሪ ጉባዬው የሚሰጠውን ውጤቱን መጠበቅ ይሻላል የሚል ሀሳብ ተሰንዝሯል።

ችሎቱ በበኩሉ ”የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄዎች በጉባዬው እየታየ ባለንበት ኹኔታ አልፈን ትዕዛዝ የምንሰጥበት የስልጣን የለንም” ሲል ዶ/ር ሰለሞን ባቀረቡት ጥያቄ ላይ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ጉባዬው የሚሰጠውን መልስ ለመጠባበቅ በድጋሚ ለ5ኛ ጊዜ ለታሕሳስ 14 ቀን 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ ያቀረበባቸው የሽብር ወንጀል ክስ በሚመለከት በጥር 30 ቀን 2014 በሽብር ወንጀል ልንከሰስ አይገባም የሚሉ ነጥቦች የተካተተባቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ እና የሕገ መንግስታዊ ትርጉም የሚፈልጉ ጥያቄዎችን አካተው 55 ገጽ ለችሎቱ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ ከ3 ወራት በፊት መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን በመገናኛ ብዙሃን የተዘገበ ሲሆን፤ ለፍርድ ቤት ግን እስካሁን አልደረሰም።
          (ታሪክ አዱኛ)

Exit mobile version