Site icon ETHIO12.COM

ኧረ የሕግና የሕሊና ያለህ ?!

“ውኋ ሲወስድ አሳስቆ!!! ይላል የሀገሬ ሰው
(ሙሼ ሰሙ)

ካርቴል (Cartel) ማለት በአንድ ዓይነት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ የንግድና የአገልግሎት ሰጭዎች ወይም አምራቾች በጋራ በመሰረቱት ማህበር አማካኝነት እርስ በርስ በመመሳጠርና በማሴር ገበያው ውስጥ ውድድርን አጥፍተው ወጥ የሆነ አንድ ዓይነት ዋጋ በመሐላ የሚተምኑበት የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ነው።

“ካርቴል” (Cartel) የሞኖፖሊ አካል ስለሆነ በየትኛውም ሀገር ሕገ ወጥ ተግባር ነው። በወንጀልም ያስጠይቃል። ዛሬ ወደ ገጠመኝ ጉዳይ መንደርደሪያ መሆኑ ነው።

ዛሬ የአጠቃላይ ኢንሹራንስ ሽፋን ፍለጋ አንዱ የኢንሹራንስ ድርጅት ጎራ አልኩ። መስተንግዷቸው እንደተለመደው አስደሳች ነበር። ደንበኛ ብሆንም አስተናጋጁን ስለማላውቀው፣ የአጠቃላይ ኢንሹራንስ እድሳት አረቦን ቅናሽ “እንዲሰጠኝ” የኢንሹራንስ ተመክሮዬን ዘረዘርኩ።

ከዚህ ቀደም ገጭቼም ሆነ ተገጭቼ ወይም አደጋ አድርሼ እንደማላውቅ አብራራሁለት። የእድሜዬን ግማሽ ያህል ታማኝ የኢንሹራንስ ደንበኛቸውም መሆኔን አከልኩለት።

በጥሞና ሲያዳምጠኝ የነበረው አስተናጋጅ “አይ ጋሼ!! ድሮ ቀረ፤ አሁን ታማኝ ደንበኛ በመሆን ከአደጋ ንጹህ በመሆን ቅናሽ ማግኘቱ ተጋዷል፣ በቅናሽ ወድድርም ቀርቷል” አለኝ።

ለምን ለማለት ቃጣኝና እድሜ ለነጻ ውድድር ገበያ ለጠንቃቃ ሹፌርና ለታማኝ ደንበኛ ክብር ያለው ኣንሹራንስ ስለማይጠፋ ዋጋውን አይቼ አማራጬን እፈልጋለሁ በማለት፣ “የአረቦኑን ዋጋ ንገረኝ” አልኩት።

ከዚህ ቀደም ከከፈልኩት 12,500 ወደ 42 ሺህ ብር ማደጉን ነገረኝ። እድገቱ ከ240 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው። ጠላታችሁ ደንግጥ ይበል፣ ክው ነበር ያልኩት !!!

የስሌት ችግር እንዳይሆን ብዬ ምንተፍረቴን “እርግጠኛ ነህ ?” አልኩት።

“አዎ ጋሼ !! ለሁላችንም አንድ አይነት ተመን ነው የተሰጠን!! የተሽሸርካሪውን ዋጋ በተሰጠን ተመን ማባዛት ብቻ ነው” አለኝ።

“አመሰግናለሁ፣ ተገቢ ዋጋ አይደለም። ሌላ ተመጣጣኝ ዋጋ የሚያስከፍል ኢንሹራን ጋር እሄዳለሁ አልኩት።” የምለው ጠፍቶኝ፤

“ጋሼ አይድከሙ ሁሉም ቦታ ተመኑ አንድ ነው። በኢንሹራንስ ማህበር አማካኝነት ውድድር እንዳይኖር ተስማምተው በወሰኑት መሰረት ነው እየሰራን ያለነው ” አለኝ።

የሰራተኛው የግንዛቤ እጥረት ቢሆን እንጂ “ኢንሹራንስን” ያህ የተደራጀ ተቋምን የሚመሩ ሰዎች በዚህ ደረጃ አይሳሳቱም በማለት የማውቀው አንድ ጉምቱ የኢንሹራንስ ባለሟል ጋር ደወልኩ። እውነት መሆኑን አረጋገጠልኝ።

እሺ ዋጋ ለመጨመሩ የዋጋ ጭማሪው አሰቃቂ ቢሆንም፣ ግሽበቱም ሆነ የእቃ ዋጋ ንረቱ ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ ። ወድድርን በሴራና በመቧደን መጨፍለቅና በአዲስ መንገድ የመስራትን የማሰብን መብት መገደብ ግን ለምን ያስፈልጋል። ጥያቄዬ ይህ ነበር ?!

በማህበር ተደራጅተው ውድድር እንዳይኖር በመመሳጠርና በአመጽ ወይም በደቦ ዋጋ መወሰን፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን ገለጽኩለት። ከቁም ነገር አልቆጠረውም። ምን ይገርማል ሁሉም የሚሰራበት ነው አለኝ። በድጋሚ “ኩም” ነው ያልኩት !!!

እንዴት ነው ነገሩ? ወዴትስ እየሄድን ነው ? በየሸጡና በየጉራንጉሩ የሚካሄደው ዘረፋ ከሕግም፣ ከስርአትም፣ ከሞራልም በላይ የተለያየ ሽፋን በተሰጣቸውና ከሕግና ሞራል በተሰወሩ የለየላቸው ጃዊሳ ወንበዴዎች የሚፈጸምብን ዘረፋና ንጥቂያ ኑሮ እየፈተነንና እየተማረርንም፣ ቢሆን ፈተናውንና ገፈቱን ተሸክመን እየኖርን ነው።

እንዴት በገሀዱ ዓለም ፈቃድ አውጥተውና በዘርፍ ተደራጅተው በመመሳጠርና በማሴር ወድድርን አጥፍተው በሚያደቡ ጉምቱ ተቋማት በጠራራ ጸሃይ እንዘረፍ። ገበያ በወጣን ቁጥር ስንቱ ቀልባችንን ይግፈፍ፤ ስንቱ ያሸማቀን !!!

እረ የመንግስት ያለህ ?!
ኧረ የሕግና የሕሊና ያለህ ?

Exit mobile version