Site icon ETHIO12.COM

“ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻልʺ

አንቺ የማትጠልቅ ጀንበር የወጣችብሽ፣ ከጀንበር የበለጠ ብርሃን ያለሽ፣ ስምሽ ከአጽናፍ ዓለም እስከ አጽናፍ ዓለም የሚጠራልሽ፣ የክብርሽ ነገር የሚነገርልሽ፣ አንቺ የዓለም ዓይኖች ሁሉ የሚፈልጉሽ፣ አንቺ እግሮች ሁሉ የሚከተሉሽ፣ ጀሮዎች ሁሉ ስለ አንቺ ለመስማት የሚያዘነብሉልሽ፣ ዓለማት ሁሉ የሚጠብቁሽ ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል።

ጠቢቡ ሰሎሞን ባጣሽ ጊዜ አብዝቶ ያለቀሰልሽ፣ አቤ ምልክ በያዘሽ ጊዜ አብዝቶ የተደሰተብሽ፣ ከሰሎሞን ቤተመቅደስ መውጣሽ በታወቀ ጊዜ የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያለቀሱልሽ፣ ንግሥተ አዜብ በክብር የተቀበለችሽ፣ የኢትዮጵያን ምድር የመረጠሽ፣ ለዓለማት ሁሉ ብርሃን የሆንሽ ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል። ሊቃውንቱ ስምሽን በሰርክ የሚጠሩሽ፣ በምድር ሕግና ስርዓት የሆንሽ፣ በየአድባራቱና በየገዳማቱ ስምሽ የሚወደሰው፣ በታላላቆቹና በታናናሾቹ የምትከበሪው ጽዮን ኾይ ተናፍቀሻል፡፡

አማልእክቱ ባዩሽ ጊዜ ተሰባብረው የወደቁልሽ፣ ሕዝብ ሁሉ የሚሰግድልሽ፣ የጌታ ትእዛዛት የተቀረፁብሽ፣ በልባቸው ክፋት ያለባቸው የማይቀርቡሽ፣ ክፉዎችን የሚቀስፍ ኃይል ያለሽ ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል። አንቺ የምድር እና የሰማይ እመቤት ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል።

ብዙዎች ወደ አንቺ ለመምጣት አሰቡ። ሳይሳካላቸው በቀረ ጊዜ አብዝተው አለቀሱ። አዘኑም። አንቺ የሰላም እናት፣ የፍቅር እመቤት ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል። አንቺ ሙሴ ጥበብንና ሕግን የተማረብሽ፣ ኢያሱ ጥበብን ያየብሽ፣ እስራኤላውያንን ከመከራ ያወጣሽ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ባየሽ ጊዜ የቆመልሽ፣ ለጠቢቡ ሰሎሞን ግርማና ሞገሱ የሆንሽ፣ መከራና ስቃይ የራቀብሽ፣ በረከትና ተድላ የመጣብሽ፣ ፈጣሪና ፍጡርን ያስተሳሰርሽ ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል።

ሙሴ የከበረብሽ፣ ሰሎሞን የተመካብሽ፣ አቤ ምልክ ሞገስን ያገኘብሽ፣ ንግሥተ ሳባ የተማረከችብሽ፣ በአየችሽም ጊዜ የተደሰተችብሽ፣ ለክብርሽ የእጅ መንሻ ያቀረበችልሽ፣ እጅም የነሳችሽ ፅዮን ኾይ ተናፍቀሻል፡፡ በአጸድሽ ሥር የሚሰባሰቡት ናፈቁሽ፣ በረከትን ያገኙ ዘንድ አውራጃዎችን አቆራርጠው የሚመጡብሽ ናፈቁሽ፣ ምንም ምንም ሳይለያቸው በአንድነት የሚከትሙብሽ፣ ለፍቅርና ለሰላም የሚጸልዩብሽ ናፈቁሽ፣ በአሻገር ኾነው አሰቡሽ፣ ይመጡ ዘንድም አብዝተው ጓጉልሽ፡፡
በተቀደሱ አፍላጋት የተከበበች፣ በበረከት የኖረች፣ ቅዱሳን የሚኖሩባት፣ ባሕታውያን የሚጠለሉባት፣ ዓለምን የናቁ በዱር በገደሉ በዋሻና በሰርጡ የሚመላለሱባት፣ በአምላክ የተወደደች፣ በስሙ የከበረች፣ በበረከቱ የተጠበቀች፣ ለምስክርነት የተቀመጠች፣ ለአደራ የተመረጠች ሀገረ ኢትዮጵያ ዓለም የሚቀናባትን፣ ሕዝብ ሁሉ የሚመካባትን ይዛለች፡፡

በቀደመው ዘመን ሕገ ልቡናን፣ በቀጠለው ዘመን ሕገ ኦሪትን ተቀበለች፣ ተቀብላም ሃይማኖትን አስተማረች፣ ሕዝብን ገሰጸች፣ በኋላም ሀዲስ ኪዳንን ተቀበለች፣ በምድሯም አስተማረች፣ በሃይማኖትም ጸናች፡፡ አበው አክሱም ፅዮን ኢትዮጵያዊነት ያየለባት፣ ሃይማኖት የተሰበከባት፣ የጸናባት፣ ጥበብ የፈሰሰባት፣ በረከት የመላባት፣ ታላቋ ስጦታ የተቀመጠችባት፣ ነገሥታቱ በአስፈሪ ዙፋናቸው ላይ የኖሩባት፣ በአጸዷ ዙሪያ የተመላለሱባት፣ ለፅዮን የእጅ መንሻ እየያዙ የተጓዙባት፣ ዘወዳቸውን አውልቀው እጅ የነሱባት፣ ሰይፋቸውን ጥለው ለክብሯ የተንበረከኩላት ናት ይሏታል፡፡

ታላቋ ንግሥት ንግሥተ አዜብ (ሳባ፣ ማክዳ) በኢትዮጵያ ነገሥላች፡፡ ይህች መልኳ ያመረ፣ ጥበቧ ከፍ ያለ ንግሥት ስሟ ከፍ ብሎ ይጠራል፡፡ በዚያም ዘመን ጥበብን ሁሉ የተቸረው ጠቢቡ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ነግሷል፡፡ በዘመኑ ታምሪን የተባለ ፀጋ የበዛለት፣ ሃብት የተትረፈረፈለት፣ በየብስና በባሕር እያቋረጠ የሚነግድ ብርቱ ነጋዴ ነበር፡፡ ይሄም ነጋዴ ከኢትዮጵያ እየተነሳ ቀይ ባሕርን እያቋረጠ፣ በረሃውን እየሰነጠቀ ይነግድ ነበር፡፡ ይህም ነጋዴ የሳባ ወዳጅና አገልጋይ ነበር፡፡

ጢቢቡ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ያሠራ ዘንድ ወድዷል፡፡ ቤተ መቅደስ የሚያሠራበት የተመረጠ ቁስ የሚያመጡለት ሃብታም ነጋዴዎችንም ያፈልግ ነበር፡፡ በዚያም ጊዜ ከባለጠጋው ታምሪን ጋር ተገናኙ፡፡ ንጉሡም ቀይ ወርቅ፣ ጥቁር የማይነቅዝ እንጨትና ሰንፌር የተባለውን እንዲያመጣለት አዘዘው፡፡ ታማኙ ነጋዴ ታምሪንም ያሻውን አደረገለት፡፡ ሰሎሞንም ደስ ተሰኘ፡፡ ስለ አደረገለት የሚከፈለውን ዋጋ ከፈለው፡፡ ብልሁ ነጋዴ ከሰሎሞን ጋር በተገናኘ ጊዜ የሰሎሞንን ጥበብ ተመለከተ፡፡ ባየውም ነገር አብዝቶ ተደነቀ፡፡
ወደ ሀገሩም በተመለሰ ጊዜ በጠቢቡ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት ያዬውን ጥበብ ለንግሥተ ሳባ ነገራት፡፡ በሰማችም ጊዜ አብዝታ ተደነቀች፡፡ በልቧ አሰበችው፣ የጥበቡ ነገር ልቧን ገዛው፣ ታዬውም ዘንድ ወደደች፡፡ ከፍቅሯም ብዛት የተነሳ ታለቅስ ነበር ይባላል፡፡ ታላቋ ንግሥትም በጀሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ታየው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ወደደች፡፡ ለመንገዷ የሚያስፈልጋትን፣ ለጠቢቡ ሰሎሞን የሚቀርበውን ስጦታ፣ ለመኳንንቱና ለመሳፍንቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅታ በታላቅ አጀብ ከሀገሯ ተነሳች፡፡ አስቸጋሪውን ጉዞም አልፋ በልቧ ከተመኘቻት፣ በአሻገር ኾና ከናፈቀቻት ከተማ ደረሰች፡፡ በደረሰችውም ጊዜ ጠቢቡ ሰሎሞን በታላቅ አጀብ ተቀበላት፡፡ ከታላቅ ሀገር የመጣች ታላቅ ንግሥት ናትና ለክብሯ የሚመጥነውን መስተንግዶ ሁሉ አደረገላት፡፡

ʺየሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፣ የማዕዱንም መብል፣ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፣ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፣ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም። ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።” አለች እንዳለ መጽሐፍ ሳባ በአየችው ሁሉ ተደነቀች፡፡
ሳባም በሰሎሞን ቤተ መንግሥት ቆዬች፡፡ በቆዬችም ጊዜ ከጠቢቡ ሰሎሞን ፀነሰች፡፡ የፀነሰችበትም መንገድ የረቀቀ ነበር፡፡ በታላቅ አጀብ እንደ ሄደች በታላቅ አጀብ ወደ ተቀደሰች ሀገሯ፣ ወደ ተከበረች ዙፋኗ ተመለሰች፡፡ ከኢየሩሳሌም በተነሳች ጊዜ ሰሎሞን ለሳባ የቃል ኪዳን ስጦታ ሰጣት፣ ተቀበለችውም፡፡ የሀገሯ ሕዝብ እልል እያለ ተቀበላት፣ ንግሥቷ መጥታለች እና ክብሯን የሚጥን አቀባበል ተደረገላት፡፡ ሳባም ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ስሙንም አቤምልክ (ምኒልክ) አለችው፡፡ ቀዳማይ ልጇም በክብርና በሞገስ በሳባ ቤተ መንግሥት አደገ፡፡ ባደገም ጊዜ እናቴ ኾይ አባቴን ንገሪኝ አላት፡፡ አባቱም ጥብብን ሁሉ የተቸረው፣ መልኩ ያመረ፣ ግርማ ሞገሱ የሚያስደነግጥ በእስራኤል ላይ የነገሠ፣ በአማረው በኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥት የሚኖረው ጠቢቡ ሰሎሞን እንደሆነ ነገረችው፡፡
ምኒልክም አባቱን ያይ ዘንድ እናቱን ተሰናብቶ፣ አጀቡን አስከትሎ፣ ከሳምሪን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ አባቱም ከሚወዳትና፣ በልቡ ውስጥ ከፍ አድርጎ ካስቀመጣት ንግሥት የተወለደው ልጅ መምጣቱን በሰማ ጊዜ አብዝቶ ደስ አለው፡፡ አሳምሮም ተቀበለው፡፡
ጢቢቡ ሰሎሞንም ለልጁ በራሱ ላይ ዘውድ ደፋለት፣ በእጣቱ ላይ ቀለበት አጠለቀለት፣ በእንቁ የተንቆጠቆጠ የክብር ልብስ ደረበለት፣ እርሱ ከሚቀመጥበት አጠገብ በክብር ዙፋን አስቀመጠው፡፡ የእርሱ አልጋ ወራሽ አድርጎ በእስራኤል ላይ ያነግሰው ዘንድ ወደደ፡፡ ምኒልክን እናቱ ሳባ ትጠብቀዋለች፣ የከበረ ቃል ኪዳንም ሰጥተዋለችና በኢሩሳሌም ይቀር ዘንድ አይቻለውም፡፡ አባቱም በኢየሩሳሌም ይነግስ ዘንድ በጠየቀው ጊዜ ምኒልክ በእናቱ ዙፋን መተካት፣ በኢትዮጵያም ላይ መንገሥ እንደሚፈልግ እንጂ በእስራኤል ላይስ አልነግሥም አለው፡፡

ምኒልክ እምቢ ባለ ጊዜ ሰሎሞን በቀኝና በግራው የሚቀመጡትን የከበሩ መኳንንትና መሳፍንቱን ሰበሰበ፡፡ በእስራኤል ይነግሥ ዘንድ ፈቃዴ ነበር እርሱ ግን እምብኝ አለኝ፡፡ ወዳጆቼ ኾይ ልጄ ንጉሥ ይኾናል እና የበኩር ልጆቻችሁን ስጡትና እናንተ በቀኝና በግራዬ እንደተቀመጣችሁት እነርሱም በእርሱ በቀኝና በግራ ይቀመጡለት አላቸው፡፡ እነርሱም ፈቀደሉት፡፡ የበኩር ልጆቻቸውን ለተወደደው ንጉሣቸው ልጅ ሰጡት፡፡
ምኒልክም በአባቱ በሰሎሞን ፊት ቅብዓ መንግሥት ተቀባ፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ ሕገ ኦሪትን፣ ሕገ መንግሥትን እና የእብራይስጥን ቋንቋ ተማረ፡፡ የመመለሻውም ጊዜ ደረሰ፡፡ ከንጉሡ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ የታዘዙ የእስራኤል የበኩር ልጆችም ተዘጋጁ፡፡ ከሀገራቸው እና ከወገናቸው ተለይቶ መሄድን ባሰቡ ጊዜ አዘኑ፡፡ ይባስ ብሎ ከታቦተ ፅዮን ተለይው መሄዳቸውን ባሰቡ ጊዜ አብዝተው አዘኑ፡፡

ከታቦተ ፅዮን እንደ ምን ተለይተን እንሄዳን ሲሉ መከሩ፡፡ የካህኑ የሳዶቅ ልጅ አዛሪያስም ማንም ሳያውቅብን ታቦተ ፅዮንን እንውሰዳት አለ፡፡ ሁሉም ተስማሙ፡፡ ያሰቡትንም በፈቃደ እግዚአብሔር ፈጸሙ፡፡ ምኒልክ ወደ ናፈቀችው ቤቱ ሊመጣ ተነሳ፡፡ ሰረገላዎቹ ተጫኑ፣ አለቆች ሁሉ ተነሱ፤ ነጋሪት ተመታ፣ ሀገሪቱም ጮኸች፣ ጎልማሶች ደነፉ፣ ግርማም ጋረዳት፣ ጸጋም ከበባት፣ የእስራኤል ጀግኖችና የመኳንንቱ ልጆች ስለተነሱ ሽማግሌዎች ዋይ ዋይ አሉ፣ ሕጻናት ጮኹ፣ ባልቴቶችና ደናግላንም አለቀሱ፡፡ በእነርሱ ምክንያት ግርማዋ ስለተወሰደባት ሀገር አለቀሱ፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም የሚሆነው ባየ ጊዜ አለቀሰ፡፡ ክብሬ አልፋለች፣ የመመኪያ ዘውድም ወድቃለች፣ ሆዴም ተቃጥላለች ወየውልኝ አለ፡፡ ከአሥራሁለቱ ነገደ እስራኤል የተውጣጣ ሕዝብ ምኒልክን ተከትሎ ጎዞ ወደ ኢትዮጵያ ኾነ፡፡

በመንገድ ላይም ሳሉ የእስራኤል ልጆች ለምኒልክ ምስጢር ትችል እንደሆነ እንገርህ አሉት፡፡ እርሱም ምስጢራቸውን እስከዕለተ ሞቱ ድረስ እንደሚጠብቅ ነገራቸው፡፡ ፀሐይ ከሰማይ ወረደች፣ በሲናም ለእስራኤል ተሰጠች፣ ለአዳም ዘር ሁሉ መድኃኒት ኾነች፣ እነኾ በእግዚአብሔር ፈቃድ በአንተ ዘንድ ናት፤ ይሄም በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተደረገ አይደለም፤ እኛ ፈቀድን እግዚአብሔር ፈጸመ፡፡ እኛ አሰብን እግዚአብሔር እውነት አደረገልን፣ አንተን መረጠ፣ ሀገርህንም ወደደ፣ የአምላክህን ትዕዛዝ ብትጠብቅ ለአንተም፣ ከአንተም በኃላ ለሚመጣው ለዘርህ መሪ ትሆናለች፣ አንተ ብትሻ እሷን መመለስ አትችልም፡፡ አባትህ ቢፈልግም ሊወስዳት አይቻለውም፣ እርሷ ወደ ወደደችው ትሄዳለችና፣ እርሷ ካልፈቀደች ከመንበሯ አትነሳም አሉት፡፡

ታቦተ ፅዮንን ባሳዩት ጊዜ ደነገጠ፡፡ ለፈጣሪውም ምስጋና አቀረበ፡፡ ታቦተ ፅዮን ከእነርሱ ጋር መሆኗን ያወቁ ሁሉ ደስ አላቸው፡፡ ብርሃኗ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ እስራኤል ስታዝን ኢትዮጵያ ደስ ተሰኘች፡፡ ለምን ታቦተ ፅዮን ኢትዮጵያን መርጣለችና፡፡ ንግሥተ ሳባ የልጇን መምጣት በሰማች ጊዜ አብዝታ ተደሰተች፡፡ ከልጇም ጋር ታቦተ ፅዮን እንደመጣች በሰማች ጊዜ ደስታዋ እጥፍ ድርብ ኾነ፡፡ ለልጇም ከፍ ያለ አቀባበል አደረገች፡፡ ከመኳንንቱና ከመሳፍንቱ ጋር መክራ ልጇን አነገሰችው፡፡ ታቦተ ፅዮን በምኩራብ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ በታቦተ ፅዮን ኢትዮጵያውያን እና እስራኤላውያን አንድ ኾነው በአጸዷ ሥር እየተሰባሰቡ ምስጋና አቀረቡ፡፡

ዘመን ዘመን እተካ ሄደ፡፡ ዓመተ ዓለም አልፎ ዓመተ ምህረት መጣ፡፡ ወንድማማቾቹ አብርሃ ወ አጽብሃ የነገሡበት ዘመንም ደረሰ፡፡ በአክሱምም ያማረውን ቤተ መቅደስ አሠሩ፡፡ ታቦተ ጽዮንም ከመቅደሰ ኦሪት ወደ አዲሱ ቤተመቅደስ አስገቡ፡፡ በገባችም ጊዜ የበዙ ኢትዮጵያውያን ተገናኝተው በዓሉን በደስታ አከበሩ፣ ያማረው ቤተ መቅደስም በዮዲት ዘመን ጠፋ፡፡ ዘመንም አልፎ የንጉሥ አምበሳ አውድም ዘመን ደረሰ፡፡ በንጉሡ አምበሳ አውድም በወርቅና በእንቁ የተለበጠ ቤተ መቅደስ ተሠራ፡፡ ይሄም ቤተ መቅደስም በጠላቶች ጠፋ፡፡

የአፄ ፋሲስ ዘመንም ደረሰ፡፡ አጼ ፋሲልም ታላቋ እመቤት ተከብራ የምትኖርበት ቤተ መቅደስ ያሠራ ዘንድ ወደደ፡፡ የጎንደርን ኪነ ሕንጻዎች የሚመስል ቤተ መቅደስ አሠራ፡፡ ይህም ቤተ መቅደስ ዛሬም ድረስ በአክሱም አብቦ አለ፡፡ ዘመናት እየገፉ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ደረሰ፡፡ እሳቸውም በአክሱም ያማረውን ቤተ መቅደስ አሠሩ፡፡ እቴጌ መነንም ለጽላቴ ሙሴና ለእንቁ ስጦታዎች ማረፊያ ይሆን ዘንድ ቤተ መቅደስ አሠርተዋል፡፡

ታቦተ ፅዮን በአክሱም፣ በመላው ኢትዮጵያ ስትከበር ትኖራለች፡፡ በወረኃ ኅዳር በ21ኛው ቀንም ከወትሮው በተለዬ ክብር ትከብራለች፡፡ ሕዝብም ይሰባሰባል፡፡ ማነህ ከየት ነህ አይባባሉም፣ ከአራቱም ንፍቅ እየተነሱ በአጸዷ ሥር ይሰባሰባሉ፣ በጋራም ይጸልያሉ፣ ለኢትዮጵያ ለዓለምም ሰላምና ፍቅር ይሆን ዘንድ ይማጸናሉ፡፡ በአንድ መዓድ ይበላሉ፣ በአንድ ጽዋ በፍቅር ይጠጣሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉበት መልካሙ ጊዜ በጦርነት መክንያት ቀርቶባቸው ቆይቷልና ፅዮንን ናፍቀዋታል፣ ከአራቱም አቅጣጫ ተጠራርተው የሚሰባሰቡባት፣ ኢትዮጵያን እያነሱ፣ ፅዮንን እያወሱ የሚያመሰግኑባት ናትና ናፈቋት፡፡

አሁን የሰላም ምልክት አይተዋልና አብረው እንደሚሰባሰቡ፣ ተገናኝተው በአንድ ጽዋ እንደሚጠጡ፣ በአንድ መዓድ እንደሚበሉ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ ተስፋቸውንም በፅዮን ላይ ጥለዋል፡፡ ፅዮን የመረጠችሽ፣ በክብሯም ያከበረችሽ ኢትዮጵያ ኾይ ለዘላለም ኑሪ፡፡

በታርቆ ክንዴ (አሚኮ)

Exit mobile version