Site icon ETHIO12.COM

ወደ ሲኦል – ተጋዙ፣ ከሲኦልም ሆነው ጮሁ፤ ሌቦቹን ማን ይንካቸው?

“ሰቆቃ” እየተባለ በየጊዜው የሚገለጸው የወገኖቻችን ስቃይ ልኩን አልፏል። እንደሸቀጥ ተቧድነው የቸረቸሯቸው ወገኖች ሲቃ ለወሬም፣ ለነጋሪውም ከባድ ነው። እንደ አሞሌ በገሃድ መንግስት ሽፋን አድርጎለት በየብስና በአየር የተቸበቸቡት ወገኖች ቢጋዙ ቢጋዙ የሚያልቁ አልሆነም። በተለይ ሳዑዲ እህትና ወንድሞቻችን እስር ቤት አጉራ እየቀቀለቻቸው ነው። ሌሎች አገራት የሄዱትም በየጉድባው ተደፍተው ተገኝተዋል። አሁን አሁን የሳኡዲ ሲኦል አፍኖ የያዛቸው ወገኖች ጉዳይ ግራ የሚጋባ ሆኗል። ግን ይህ ሁሉ ቢያግዙት የማያልቅ፣ እስር ቤቱ የማይጎድልበት የሰው ብዛት እንዴት ሳዑዲ ገባ? መልሱ “ሌቦቹን ማን ይነካቸዋል” ነው።

በአንድ ወቅት አሜሪካን ግቢ፣ ሃብተጎርጊስ ድልድያና ወደ አትክልት ተራ ግድም ያሉ ቢሮዎች ገንዘብ ያመርቱ ነበርና ድንገት በመካከላቸው በተነሳ የጥቅም ድብድብ ነገራቸው አደባባይ ዋለ። በጉዞ ወኪልነት የተከፈቱት ቢሮ መስለ ማጅራት መምቻ ስፍራዎች ድሆችን በኮታ ተካፍለው የሚቸበችቡበት ነበር። ዛሬ በዩቲዩብ ወሬ ሃያ አራት ሰዓት ስድብና ዘለፍ ሲለማመዱ የሚውሉ ቀፎዎች እንዲህ ያሉትን ቢሮዎች ሄደው በማፋጠጥ ለወገን ቢሰሩ ስል እየተመኘሁ ጎልጉል ” ሌቦቹን ማን ይነካቸዋል” ሲል ያተመውን መረጃና አምነስቲ ” ሰቆቃ” ያለውን ከ30 ሺህ የሚዘልቁ ዜጎች መከራ ከቢቢሲ እንዳለ ወስጄ አቅርቤዋለሁ።

አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የስራ እድል መመናመንና ወገን እየለየ የሚከናወነው የስራ እድል ተስፋ ያስቆረጣቸው እየበረከቱ በመሄዳቸው ኤጀንሲ ከፍቶ መስራት ታላቅ ቢዝነስ ሆነ። በዚህም የተነሳ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ሹመኞች ከሰው ንግድ ጀርባ ሆነው መጫወት ጀመሩ። በእንዲህ መልኩ የመንግስት ከፍተኛ ሰዎች ያሉበት ዝርፊያ ተከናወነ። ሌቦቹም፣ ህግ አስከባሪዎቹም ራሳቸው ስለሆኑ ለህዝብ በደል ጆሮ የሚሰጥ ጠፍቶ የድሆች እምባ ተደፋና ቀረ።

ኢህአዴግ ልዩ ምክንያት ከሌለው በስተቀር የውጪ ጠላት አያፈራም የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ምክንያት ካለው ግን ቅንድቧን አንደተላጨችው ነገረኛ ሴት ለመጋጨት ይፈጥናል። ከፊትለፊቱ ገንዘብ ካየ ደግሞ ኢህአዴግ ገደል ሜዳው ነው የሚሉም አሉ። ገንዘብ በሌለበት ቦታ ኢህአዴግ አይታይም በማለት ከበረሃው ኑሮ ጀምሮ የሚከሱት ጥቂቶች አይደሉም። በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ምድር በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚሰቃዩትን ወገኖች አስመልክቶ የያዘው አቋምም ከዚሁ መርሁ የተቀዳ እንደሆነ የሚከራከሩ በርካታ ናቸው። “ምን ያድርግ የኖረው የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ ተቆልለው እሱ ላይ ወደቁ” በማለት ኢህአዴግን ለኢትዮጵያ የተቀመጠ “የተቀባ” መፍትሔ አድርገው የሚያወድሱ አሉ።

ኳስ ሜዳ ያደገችው ኑሪያ መሐመድ አሁን የምትኖረው ኳታር ነው። ኑሮ እንዳሰበችው የተመቻቸ ባይሆንላትም ወደ አገርዋ ለመመለስ አትፈልግም። አታስበውም። “ኢትዮጵያ ምን አለ?” ከማለቷ በቀር ለምክንያቷ ብዙ ማብራሪያ መስጠት አትፈልግም። አገሯ እሷንና መሰል ወገኖቿን ለማኖር አልቻለችም። በኳታር ባይመቻትም የታናናሽ እህቶቿንና የምትወዳቸውን እናቷን ጉሮሮ መሸፈን የሚያስችላትን አቅም አግኝታለች። ይህ ለእርሷ ታላቅ በረከት ነውና ችግሯን በበረከቷ እያዋዛች ትኖራለች። በኳታር በረሃ!!

ኑሪያ ኳታር የሄደችው አሜሪካን ግቢ በሚገኝ አንድ የጉዞ ወኪል ቢሮ ውስጥ ሰዎችን ወደ አረብ አገራት የመላክ ህጋዊ ፈቃድ አለው በተባለ ሰው አማካይነት ነው። የላካትን ሰው በአካል አታውቀውም። ቢሮውንም የረገጠችው የመጓጓዣ ቲኬትና ሰነዶቿን ለመቀበል ብቻ ነው። በወቅቱ እዛው ቢሮ ወደ ሳዑዲ ለመሔድ በዝግጅት ላይ የነበረች እህት ተዋውቃለች። ልጅቷ ከደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የመጣች ነበረችና ቤቷ ወስዳ ጋብዛታለች። በዚያው በመሰረቱት ጓደኝነት ከያሉበት ሆነው ይጠያየቁ ነበር። እድሜ ለጊዜና ለስልጣኔ!!

ኑሪያ እንደምትለው ጓደኛዋ ወደ ጅዳ ለመሄድ እንደትችል ቤተሰቦቿ የሚያርሱባቸውን ሁለት በሬዎች ሸጠዋል። ገንዘብ በአራጣ ተበድረዋል። አሁን የተፈጠረው ትርምስ ከመከሰቱ ስድስት ወር በፊት በህጋዊ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ሄዳ የነበረችው ጓደኛዋ “ህገወጥ” ተብላ ተመልሳለች። ቅድሚያ እቅዷ ለቤተሰቦቿ ሁለት በሬዎች መግዛትና የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል ሲሆን፣ በየደረጃው ሌሎች እቅዶችም ነበሯት።



ሁሉም እንደታሰበው ሳይሆን ቀረና የኑሪያ ጓደኛ እዳ ተሸክማ ቤተሰቦቿ ዘንድ ገባች። በሬዎች የሉም፣ እዳ አልተከፈለም። አርሶ ለመብላትም አልተቻለም። ኑሪያ ስለ ጓደኛዋ ብዙ ተናግራለች። በኳታር ከምትኖር ሌላ ጓደኛዋ ጋር በመሆን የአቅሟን ለመርዳት ሞክራለች። ወደ ፊትም ከእህቶቿ ለይታ እንደማታያት ገልጻለች። መንገዱ ካለም “ከኢትዮጵያ የማይሻል ነገር የለምና እወስዳታለሁ” ብላለች።

የሚገርመው የኑሪያ ጓደኛ በህጋዊ መንገድ የላካት ድርጅት ዘንድ ስትሄድ የተሰጣት መልስ ነው። በስም የጠራችውና እሷን የላካት ሰው የለም። ድርጅቱ የጉዞ ወኪል ሆኖ ይሰራል። ሰውየው ግን የለም። ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ለተመሳሳይ ድርጅቶች ያቀርባሉ። ላኪዎቹ የውሃ ሽታ ሆነዋል። መልስ የለም … እንቆቅልሽ!!

ባለኮብራዎቹሰውነጋዴዎች

ባለ ኮብራዎቹ የጉዞ ወኪል ድርጅት ባለንብረቶች ናቸው። ለጸሎት ወደ ጅዳ የሚሄዱትን መንገደኞች በኮታ እየተከፋፈሉ የጉዞ ቲኬትና ማረፊያ በማዘጋጀት ብር ሲያመርቱ ኖረዋል። ከአንድ ሰው እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ ንጹህ ትርፍ ያተርፋሉ። ስለ ስራው የሚያውቁ “ዝርፊያ” የሚሉትን ስራ ህጋዊ ለማድረግ በማህበር ተደራጅተው ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ፣ እንዲሁም የኦዲት ኮሚቴ አቋቁመው ኢህአዴግ ህጋዊ እውቅና አጎናጽፏቸዋል።

ወደ ሳዑዲ ለጸሎት የሚደረገው ጉዞ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገላበጥበት በመሆኑ በማህበር የተደራጁት ነጋዴዎች ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ለጸሎት የሚሄዱ ምዕመናን የሚያድሩበትን፣ ስለ አጠቃላይ የጉዞ ኮታና ስለ ጉዞ መስፈርቶች ከመንግሥት አካላት ጋር ይነጋገራሉ፤ ያቅዳሉ። አንዳንዴም የመጅሊሱን ስራ ይሰሩለታል። የኢህአዴግንም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስራ ያከናውኑለታል። በዚህ ያልተገደበ የስልጣንና የስራ ደረጃቸው ባከማቹት ሃብት ተብለጭልጨዋል። የሚያሽከረክሩት ኮብራ ነው። አንዳንዶቹ ፊታቸው የሚፈርጥ ይመስላል። ኑሯቸው የተቀናጣ ሲሆን ከትምህርት ጋር ብዙም የሚዋደዱ አይመስሉም። የሃብታቸውን መጠን በልጆች ብዛት፣ በዘመናዊ መኪናና በሌሊት የዝግ ቤቶች በመመንዘር ከማሳየት የዘለለ የሚስብ ነገር የላቸውም። ሰውነታቸው ግዙፍና አብዝተው ጫት የሚጠቀሙ የሺሻ ወዳጆች ናቸው። ቢሯቸው ውስጥ ለእለት ጉርስ ሳይሆን “ሱስ” የሚሆኑ ቁሳቁሶች አሉ። በዚህ መካከል በድንገት በተደረገ የመጅሊስ ሹም ሽር መሰረታቸው ቆዳ ንግድ የሆነው ሃጂ ኤሊያስ ሬድዋን ወደ መጅሊስ ተመርጠው ገቡ።

ሃጂው ንግዱን ከውጪ ሆነው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት የመጅሊሱን ወንበር እንደተቀመጡበት አፍታም ሳይቆዩ ዘመቻ “የጉዞ ወኪል” ጀመሩ። ጉዞ ወደ ጅዳ አድርገው ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር መከሩ። አዲስ መስመር ዘርግተው መጡና ከማህበራዊ ጉዳይ ጋር ስትራቴጂ ነደፉ። ጎን ለጎን በዘመዶቻቸው ስም የጉዞ ወኪል ድርጅቶችን ከፈቱ።\

ዳግም ወደ ሳዑዲ በመሔድ ራሳቸው በዘመድ አዝማድ ስም ከፍተዋቸዋል ለተባሉት ስምንት የሚደርሱ የጉዞ አመቻች ድርጅቶችና ቁጥራቸው በጣም ውስን ከሆኑ ሌሎች የቀድሞ ድርጅቶች በስተቀር የተቀሩት ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በመጅሊሱ ሰም ከስምምነት ላይ ደረሱ። ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባካሄዱት የፊርማ ስምምነት የቀድሞዎቹን የንግዱ ፈጣሪዎች አራገፉዋቸው። ድርጊቱና ውሳኔው ድንጋጤ ፈጠረ።

በድንገት የገንዘብ ምንጫቸው የደረቀባቸው ባለኮብራዎቹ በግልና በድርጅት ተሯራጡ። ሃጂ ኤሊያስ ሙሉ የኢህአዴግ ድጋፍ ስለነበራቸው የሚነቀንቃቸው ጠፋ። አሸነፉ። ንግዱንም አስተዳደሩንም ተቆጣጠሩት። ያለ ከልካይ ብር ያመርቱ ጀመር። አምርተው የሚያቋድሱት የማይገፋ ሃይል ስላደራጁ እሳቸውን ለማሳጣት የሚደረጉ ሙከራዎች መዝናኛዎቻቸው ሆኑላቸው። በጉዳዩ ዙሪያ ሚዲያዎች ሲጠይቁዋቸው ያረገፉዋቸውን የቀድሞ ቱጃሮች አፈር ከመሬት እያስገቡ ከመናገር ውጪ አንዳችም ስጋት አልነበረባቸውም። መንግስት አሁን ቢያግዘው ቢያግዘው አላልቅ ያለው ወገን እንዲህ ነው የተከማቸው።

የቢቢሲ ዘገባ ከስር ያንብቡ።

በሳዑዲ አረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው የተባሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በተጨናነቁ እስር ቤቶች በሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ እና እየገጠማቸው ያለውን አሳሳቢ ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ቁጥራቸው ከ30 ሺህ እንደሚልቅ አመልክቷል።

ጨምሮም የሳዑዲ ባለሥልጣናት “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኢሰብአዊ እና ጭካኔ በተሞላበት አያያዝ ላልተገደበ ጊዜ በእስር ከቆዩ በኋላ በግድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል” ብሏል።

ኢትዮጵያውያኑ ለዚህ ስቃይ የሚዳረጉት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌላቸው ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ሳዑዲ ባላትና “ጨቋኝ” ነው በሚባለው ‘ካፋላ’ የሠራተኞች ቅጥር ሥርዓት ምክንያት የተባባሰ መሆኑን አመልክቷል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል የኢትዮጵያውያኑን ሁኔታ ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ ላይ እንዳለው፣ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች የሚገኙባቸው ስደተኞቹ በዘፈቀደ ተይዘው በእጅጉ የተጨናነቁ ናቸው ባላቸው አል-ኻራጅ እና አል-ሹማይሲ በተባሉ እስር ቤቶች ይገኛሉ።

የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አካባቢ ኃላፊ የሆኑት ሄባ ሞራዬፍ እንደተናገሩት ባለፉት አምስት ዓመታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ በማለፋቸው “በርካቶች ለከባድ እና ለዘላቂ አካላዊ እና አእምሯዊ ችግሮች ተዳርገዋል።”

“በአሁኑ ወቅትም ከ30,000 በላይ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው ተመሳሳይ ዕጣ እየተጋፈጡ ነው። አንድ ሰው ሕጋዊ ሰነድ የለውም ማለት ሰብአዊ መብቱ ይገፈፋል ማለት አይደለም” ብለዋል ሄባ።

በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ዓመታት በእስር ቤቶች በስደተኞቹ ላይ የተፈጸሙ ማሰቃየቶችን እንዲሁም ቢያንስ 10 ሞቶች ላይ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው በአገሪቱ ውስጥ ይገኛሉ ያሏቸውን ስደተኛ ሠራተኞችን በአሰሳ በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የማድረግ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

“ሳዑዲ ባላት ካፋላ በተባለው ጨቋኝ ሥርዓት” ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች የሆኑ ሠራተኞች ሕጋዊ እንዲሆኑ የሚያስችል ዕድል አይሰጥም። በተጨማሪም ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ስቃይ ከሚፈጽሙባቸው አሰሪዎች ያመለጡ ሠራተኞች ከሆኑም ሕጋዊነታቸውን ያጣሉ።

በሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ወቅት 10 ሚሊዮን የሚገመቱ ስደተኛ ሠራተኞች የሚገኙ መሆናቸውን ያመለከተው አምነስቲ፣ በተለይ ለስቃይ የተጋለጡ ናቸው ባላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ማተኮሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ መንግሥታት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ቢያንስ 100 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዕቅድ መያዛቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ሥራ እና ሕይወት ፍለጋ በአደገኛ መንገድ ከሚሰደዱባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ሳዑዲ አረቢያ አንዷ ስትሆን፣ ስደተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ከሚገጥሟቸው አደጋዎች ባሻገር በመድረሻቸውም ከባድ ሰቆቃ ይገጥማቸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በአደጋኛ ባሕር እና በረሃ አቆራርጠው በሕገወጥ መንገድ በሚጓዙበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩት ባሕር ውስጥ የመስመጥ፣ በአዘዋዋሪዎች እና ድንበር ጠባቂዎች የመገደልና በረሃብና በውሃ ጥም መንገድ ላይ መሞታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በሳዑዲ አረቢያ በመቶ ሺዎች ኢትዮጵያውን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት ሕገ ወጥ ናቸው ባሏቸው ስደተኞች ላይ እርምጃ በሚወስዱበት ኢላማ ከሚሆኑት መካከል አንዱ ናቸው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም ቢቢሲ በድምጽና በምስል ያገኛቸው መረጃዎችን መሠረት አድርጎ በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።   

Exit mobile version