Site icon ETHIO12.COM

ሰሞኑን እየታየ ያለው ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ ኮቪድ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው

ህብረተሰቡ የእጅ ንፅህናን መጠበቅን ጨምሮ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም እና ክትባት በመከተብ እንዲሁም ሰው ከተሰበሰበበት በመራቅ ራሱን ከወረርሽኙ መከላከል

ሰሞኑን በብዛት እየታየ ያለው ጉንፏን መሰል ወረርሽኝ በአብዛኛው የኮቪድ 19 ምልክት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሻምበል ሀቤቤ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልጸዋል።

ወረርሽኙ ኮቪድ 19ን ጨምሮ የብዙ መተንፈሻ አካላት በሽታዎች ምልክት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው ኮቪድ የመሆን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስተባባሪው አብራርተዋል።

በዚህ ወቅት ኮቪድ 19 የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 6 በመቶ እየጨመረ መምጣቱንም አቶ ሻምበል ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት ከተመረመሩ በርካታ ሰዎች መካከል ወደ 860 በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በመሆኑም እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ህጻናትን ጨምሮ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል አሁን እየቀረበ ባለው ፈጣን የ15 ደቂቃ የምርመራ ውጤት መሰረት በአቅራቢያው በሚገኝ ጤና ጣቢያ በመመርመር ውጤቱን አውቆ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ የእጅ ንፅህናን መጠበቅን ጨምሮ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም እና ክትባት በመከተብ እንዲሁም ሰው ከተሰበሰበበት በመራቅ ራሱን ከወረርሽኙ መከላከል እንዳለበት አቶ ሻምበል አሳስበዋል።
ዘገባው የኢቢሲ ነው።

Exit mobile version