ETHIO12.COM

አጉል ሰርግና ምላሽ – ጣጣ እንዳያመጣ ጠንቀቅ!!

ራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ በሚል የተገንጣይ ስም ሰይሞ ግማሽ ምዕተ ዓመት ማስቆጠሩ መካካድ የማይቻልበት ሃቅ ነው። የዛሬ ሃምሳ ዓመትም፣ ዛሬም ትህነግ!! ነጻ አውጪ!! ጫካ ነጻ አውጪ፣ ከተማ ነጻ አውጪ፣ ቤተመንግስት ሲገባ ነጻ አውጪ፣ ኢትዮጵያን ሲገዛ ለሃያ ሰባት ዓመታት ነጻ አውጪ… ኢትዮጵያን ቆዳ ላይ ተጠቅልሎ አፍሪካን ሲመራ ነጻ አውጪ፣ በተባበሩት መንግስታትም ሲወከል የኢትዮጵያ ወኪል ግን ነጻ አውጪ … ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ አንዴ ክልል፣ አንዴ መንግስት፣ አንዴ ጎረቤት አገር፣ አንዴ ሃያል ነጻ አውጪ … በቃ ያልሆነው የለም ግን “ነጻ አውጪ” ማዕረጉና ኩራቱ የሆነ፣ “ነጻ ውጣ” ቢባል የማይሆንለት በቅዠትና በሴራ ያበጠ ድርጅት ነበር። ትህነግ። በትግርኛ ህወሃት። በእንግሊዝኛ TPLF።

– በትግራይ በረራ ተጀምሮ ቤተሰቦች ከሁለት ዓመት በሁዋላ ሲገናኙ፣ መሬት ሲስሙ አየን። ሲላቀሱ አየ። ያሳዝናል። ልብ ይነካል። ስልጣን የጠማቸው በለኮሱት ጣጣ ይህ ሁሉ መድረሱ አንገትን ያስደፋል።ማን ይህን ሁሉ እንዳደረገው ማሰብ አለመቻልና ይህንን ሁሉ ማህበራዊ ቀውስ ያደረሱት ዜናውን ተንተርሰው አስተያየት ሰጪዎች ሲሆኑ ማየት ይቀፋል። አስተያየታቸውን እንደወረደ በመቀበል ለነዚሁ የጥፋቱ አውራዎች የፖለቲካ ዳግም ውልደት አማማጭ የሚሆኑትን ማየት ደግሞ “መቼ ነው የምንነቃው” ያሰኛል

ከመተለቅ ይልቅ ትንሽነት ላይ ተችክሎ፣ ሌሎች እንዲያንሱ ሴራ ሲያመርት ኖሮ እንደምኞቱ መጨረሻ ላይ ተንደባሎ ራሱን አመድ ላይ ያገኘ ድርጅት ነው። ማን? ትህነግ። ጫካ ነበር። ከጫካ ወጣና መንግስት ሆነ። ተመልሶ ጫካ ገባ። ያው ዛሬ ህዝቡንም፣ ደጋፊዎቹንም ራሱንም ጨለማ ውስጥ ከቶ ” ሲስሟት ትታ ሲስቧት” እንዲሉ ሆኗል።

ትዕቢት ቀብትቶት እናቶች አልቅሰው ለሰላም ሲማጸኑት ” ወግዱ” ያለውና ኢትዮጵያን ሲኦልም ቢሆን ገብቶ እንደሚያፈራርሳት ሲዝት የነበረው ትህነግ፣ ዛሬ ራሱን ሲኦል ውስጥ ቀርቅሮ በላኪዎቹ ጩኸት ከቀብር ሊተርፍ ችሏል። በመከላከያ ሰራዊትና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ አፍረ በልቶ፣ አፈር ጠጥቶ፣ ተባይ በልቶት፣ መሳቂያና መሳለቂያ ሆኖ በጁንታ ማዕረግ እግር ልሷል።

ላለፉት አራት ዓመታት “ባዶ ቤት አገኘሁ” ብሎ አመድ ሊያደርገን እንደ ተምች ቢርመሰመስም ሳይሆንለት ቀቷል። የፈረሱ ክንዶች፣ የተበተኑ የመሰሉ ተቋሞች፣ የላሉ የመሰሉ መስተጋብሮች ተጋምደው ምሱን ሰጡትና ትህነግ እንዳይነሳ ተደቁሶ አግዳሚው ላይ ለመቅመጥ፣ ከጋምቤላ ክልል በላይ፣ ከቢኒሻንጉል የተሻልኩ፣ ከሲዳማ የማይል፣ ከአፋር የምልቅ እንዳይል ሆነ። የተመኘውን አገኘ።

እሱ ቀጥሯቸው ሲልከሰከሱ የነበሩ ሁሉ፣ ያ ሁሉ ፉከራ፣ ያ ሁሉ ቀረቶ፣ ያ ሁሉ ድንፋታ ” በጣም እናመሰግናለን” በሚል ተማጽኖ ሲቀየር ስታዩ ምን ተሰማችሁ? አሁንም ትልከሰከሱ ወይስ ቀሪ ዘመናችሁን በ”ሰው” ማዕረግ ለመኖር? ያ “ጦረነት ባህሌ፣ ጦርነት ተሰጥኦዬ” ሲል የነበረ ድርጅትና ተከታዮቹ ደቀው እጅ ሲሰጡ አሁንም በቅጥር ውልህ መሰረት ሰላማዊና ምስኪን አርሶ አደር መንደር እየተዛወርክ ትገላለህ? አቶቢስ እያስቆምክ ሰላማዊ ተጓዦችን ታጠቃለህ? ትዘርፋለህ? ታግታለህ? …

ይህን ሁሉ ያነሳሁት ወድጄ አይደለም። ከሰላም ስምምነቱ ጀመሮ የሚታየው ሰርግና ምላሽ ስላላማረኝ ነው። በበርካታ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ምክንያቶች ትህነግ ተወቅጦ ልሟል። ቀደም ሲል ሳይሆን አሁን ላይ የሚድያ አዋጊ የነበሩት ወዳጆቹ ” ተበታትኗል። ሊሰፋ በማይችል መልኩ ፈራርሷል” ሲሉ የመሰከሩለት ትህነግ የፖለቲካ ሞቱን ለመሻገር የሰላም ስምምነቱን ከሱ ጥንካሬ የተገኘና ለትግራይ ሕዝብ ሲል ያደርገው እንደሆነ እያሰፋ ነው።

ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ምንም ዋጋ በሌለው ጦርነት ማግዷል። አማራና አፋርን በተለይ የማይረሳ ቁስል አሳድሮባቸዋል። ትህነግ አማራና አፋር ክልልን ወሮ ምንም ያላደረጉትን አርሶ አደሮች ገሏል። ጨፍጭፏል። አርዷል። ንብረታቸውን ዘርፏል። ማጋዝ ያልቻለውን አውድሟል። ትምህርት ቤትና የጤና ተቅማትን መዝረፉ ሳያንስ አመድ አድርጓል። ሌማት ላይ የተጸዳዳ ነውረኛ ሲሆን፣ ክብረቢስነቱን ለማሳየት መነኩሴ ደፍሯል። ትህነግ የትግራይን ህዝብ ሃምሳ አመት ወደሁዋላ የመለሰ፣ ለልመናና ለውርደት ዳርጎ የዓለም መሳቂያ ያደረገ፣ ለፖለቲካ ቁማሩ ሲል በሚምልበት ህዝብ የነገደ ድርጅት ነው።

ይህ ድርጅት ሁሉንም ብንተወው እንኳ ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ፣ ስልጣን ላይ እያለ ከሁለት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሴፍቲ ኔት እንዲተዳደሩ አድርጎ በስማቸው ዱቄት የሚለምናባቸው፣ ዙሪያቸውን ጠላት ሸምቶ ጎረቤት አላባ በማድረግ በር ዘግቶ በእርዛት ያስመታ፣ በጨለማ ያኖረ፣ ያለመገናኛ የዘጋባቸው ነው። ሲሰክን ገና በደንብ የሚወራረድ የትግራይ ህጻናት ደም እጁ ላይ ያለበት ድርጅት ነው። ስልጣን በመልቀቁ አብዶ ትግራይን የጦር አውድማ ያደረገና ልጆቿን የበላ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ሁሉን ቧጦ፣ ኪሳራውን ሁሉ ተግቶ ሲያበቃ ዛሬ ከሰላም ዜናው ፊት ለፊት ቆሞ ከፖለቲካዊ ሞት እንዲያገግም መፍቀድ ነገ ዋጋ ያስከፍላል።

ኢትዮጵያ የታላቅ አገር ህዝብ አገር ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ምክንያት የሞቱም ሆነ አካላቸው የጎደለ፣ አርፈው በተቀመጡበት ንብረታቸው የተዘርፈና አመድ የሆነባቸው ፍትህ ይፈልጋሉ። ዕርቅ ደግ ነው። የትግራይ ህዝብ ምህረትን የወዳል። ምህረትንም ይሰጣል። ይቅርታን የኖረበት፣ ይቅርታ መጠየቅና ሰላም ለማስፈን ይመጥናል። ልክ እንደ አማራው፣ ጉራጌው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ሶማሌው ወዘተ ማለቴ ነው።

ነገር ግን በትግራይ ህዝብ ስም የተፈጸመን ወንጀል፣ ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ ማየት ግድ ነው። አገር ዱቄት አድርጎ፣ ነብሰገዳይ በማደራጀት ህዝብ አስጨርሶ፣ መከላከያን አሳርዶ መሙለጭለጭ አይቻልም። ሰላም የሚጸናው ፍትህ ሲኖርበት ነው። ፍትህ እገሌ እገሌ ሳይል፣ የፌደራል፣ የክልል ሳይል ሁሉ ላይ ከተበየነ፣ ነገ ላይ ህዝብ ለማሳረድም ሆነ ለማስጨረስ ለሚነሱ ሁሉ ትምህርት ይሆናል።

ስለሆነም በጀግኖቻችን አጥንትና ደም ተንፍሶ አመድ ለሆነ ድርጅት የፖለቲካ ትንሳኤ ሲባል “ሰርግና ምላሽ” መጫወት በንጹሃን ደም መጫወት ነው። ወልቃይት፣ ተገዴ፣ ሁመራ ፍትህ የሚጠብቁ ደማቸው እየጮኸ ነው። በጥቅል አፋር፣ አማራና ትግራይ ሳይቀር የተፈጸሙ ወንጀሎች ከወዲሁ ነጻና ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ሊጣራና በነብሰ ገዳዮች አለቆች ላይ ፍትህ ሊበይን ይገባል።

የሰላም ስምምነቱ እጅግ አስደሳች፣ የሚደገፍ፣ የሚወደስ ቢሆንም፣ ልብስ አጥሎ የሚስከንፍ አይደለም። የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ፍትህ ጠይቅ። እርዳታና አገልግሎት ዳግም የተጀመረልህ በትህነግ ጉብዝና ሳይሆን፣ በትህነግ ሽንፈት ላይ በተገነባ ክንድ ምክንያት መሆኑንን ተረድተህ ” ለምንድን ነበር ያስጨረስከን፣ ያሰቃየኸን፣ ጨለማ ውስጥ ያኖርከን?”በሉት? ” ልጄን” በሉና ጠይቁ። ትህነግ “በል” ሲል መማገድ፣ ” አመስግናለሁ” ብሎ እጅ ሲሰጥ ፈንዲሻ መርጫት እስከ መቼ። የፌደራል መንግስትም ጥሩ አድርገሃል። ግን ልባም ሁን። ሰርግና ምላሹ ላይ ጠንቀቅ!!

በመጨረሻም ይህቺን ትዕቢት ፊልሟን ክፈቱና ስሙልኝ። ይህ የተሟረተበት አየር መንገድ ነው እህል፣ መድሃኒት፣ ሰው ይዞ በመጓጓዝ ህይወት ያኖረው። ብዙ ተብሏል። እነዚህም ውጭ ሆነው ትግራይና ህዝቧን ሲያነዱ የነበሩ ተከፋዮች ናቸው።

አሉላ ብቻ ሳይሆን ጌታቸውም አለበት። ለዚህ ነው ሰርግና ምላሹ ፍትህን በሚጋርድ መልኩ መሆን የለበትም የምለው። ምክንያቱም በሁሉም መስክ ያላደረጉን የለማ።

ነጻ አስተያየት በአጌና ሰዋሰው

ኢትዮ 12ን በቲውተር በቴሌግራምበፌስቡክ ይከተሉ

Exit mobile version