Site icon ETHIO12.COM

ደረሰኝ ሳይዙ ሸቀጦችን ጭነው በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

ደረሰኝ ሳይዙ ሸቀጦችን ጭነው በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ መሆኑን በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበርና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ አስታውቀዋል፡፡

የታክስ ሕጉ ማንኛውም ነጋዴ ወይም አገልግሎት ሰጪ ግብይት ካከናወነ በኋላ ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቢያስገድድም ደረሰኝ የማይሰጡ እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

አንድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ሽያጭ በሚከናወንበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ታክስን 15 በመቶ ጨምሮ ከገዢው ወይም ከተጠቃሚው ለመንግስት ግብር እንዲሰበስብ በሕጉ ውክልና መሰጠቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ይሁንና በሀገራችን አገልግሎት ሰጪም ሆኑ በየደረጃው ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ የታክስ ሕጉን ተከትለው እንደሚሠሩ ሁሉ ደረሰኝ የማይሰጡ መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ሸቀጦች እና ንብረቶች የሚያጓጉዙ እና ጫኝ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሸቀጥ ከመጫናቸው በፊት ሕጋዊ ሰነድ መኖርና አለመኖሩን እያረጋገጡ መሄድ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ይህንኑ ተቋሙ ወደ እርምጃ ከመግባቱ በፊት በማስታወቂያ እና በሌሎች የማስተማሪያ መንገዶች የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ሁሉም ክልሎች በዚህ ላይ በትኩረት እንዲሠሩ አቅጣጫ ለመስጠት መታሰቡን ጠቁመው÷ በየትኛውም ደረጃ ያሉ የሕግ አስከባሪ አካላት ጭነቶች በሚጓጓዙበት ጊዜ ህጋዊ ሰነድ መያዛቸውን እንዲያረጋግጡ እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡

በታክስ ሕጉ መሰረት አንድ ጭነት ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖረው ሲንቀሳቀስ ከተያዘ በዋናነት የጭነቱ ባለቤት ሸቀጡን ከየት እንዳመጣ ማስረጃ መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ይህ ሳይሆን ሲቀር ወደ ኋላ በመሄድ ሸቀጡን ያለደረሰኝ የሸጠው አካል ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እና የሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልበት መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Via . OBN

Exit mobile version