ETHIO12.COM

በሌለበት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ግለሰብ ከዓመታት በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ

በ2012 ዓ.ም በፈፀመው የማታለል ወንጀል ሲፈለግ ተሰውሮ የቆየውና በሌለበት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ግለሰብ ከዓመታት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ወንጀለኛው በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ለማታለያ የሚጠቀምባቸውን ሰነዶች ተገኝተዋል።

ተከሳሽ ታምራት አበራ የማታለል ወንጀሉን የፈፀመው ታህሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ሲኒማ ራስ ቶታል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ግለሰቡ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አስመጪ እና ነጋዴ ነኝ ብሎ የማታለያ ዘዴ በመፍጠር ከውጭ ሃገር ያስመጣኋቸው ቴሌቪዥኖች ጉምሩክ ስለተያዙብኝ በ5 ቀናቶች ውስጥ ካላወጣሁ መንግስት ይወርስብኛል፤ ስለዚህ ለቀረጥ የምከፍለው ገንዘብ ከሰጠኸኝ ቴሌቪዥኖቹን በቅናሽ እሸጥልሃለሁ ብሎ ነበር ከግል ተበዳይ በተለያዩ ቀናቶች 812 ሺህ ብር የተቀበለው፡፡

ተከሳሽ ታምራት አበራ በፖሊስ ክትትል ተይዞ ጉዳዩን በፍርድ ቤት ሲከታተል ከቆየ እና ፍርድ ቤቱም ዋስትና ፈቅዶለት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በቀጠሮ ሳይቀርብ ተሰውሮ ቆይቷል፡፡

የተከሳሹን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎትም ግለሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ በቀጠሮ መቅረብ ባለመቻሉ ነሃሴ 30/2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት በሌለበት በ3 አመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በመወሰን ፖሊስ ታምራት አበራን አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክትትልና የኢንተለጀንስ ቡድን በማቋቋም አስፈላጊውን ተግባር ሲያከናውን ቆይቶ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሽ ታምራት አበራ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ፍርድ ቤት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-B81460 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የተከናወነው የክትትል ተግባር ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ማምለጥ እንደማይችል ማሳያ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ ተከሳሽ ታምራት አበራ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ለወንጀል መፈፀሚያ የሚጠቀምባቸውን 1 ቱርክ ሰራሽ ህገ-ወጥ ሽጉጥ ፣ በርካታ የብሄራዊ ሎተሪ ወረቀቶች፣ የተለያዩ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች እና 58 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ በፍተሻ ወቅት መያዙን ፖሊስ ገልጿል።

ከዚህ ቀደምም የቅሚያና የማታለል ወንጀሎችን ሲፈፅም ስለመቆየቱ ከፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ በተገኘ የጣት አሻራ ሪከርድ ተረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የትዊተር ገጽ ይከተሉ‼️

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version