Site icon ETHIO12.COM

አማራ ክልል ደስታውን ገለጸ፤ ቤተክርስቲያኗ የሄደችበትን መንገድ አደነቀ

“የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ይህንን ፈተና በትኩረት ሲከታተለው ቆይቷል” ይላል ዛሬ ውይይቱ ከተደረገና የስምምነት ዜና ከተሰማ በሁዋላ አማራ ክልል ያወጣው መግለጫ። ስምምነት በመደረሱ የተሰማውን ደስታ በማስታወቅ የተቋጨው መግለጫ፣ ሁሉም ክልሎች ሃይማኖትን ተገን አድረገው የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማራመድ በተነሱ የተደራጁ ሃይሎች ላይ ያሰሙትን ቅሬታ ዓይነት አሳብ አላካተተም።

ክልሉ በመግለጫው ቤተክርስቲያኗን የሚመሯት አካላት ላሳዩት ጥበብ የተሞላበት አካሄድ አድናቆቱን፣ ተግባራቸውም ለሌሎች መማሪያ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል። ቤተክርስቲያኗ ላይ ፈተና መደረሱንና ይህንኑ ፈተና በጥሞና ሲከታተል እንደነበር ያወሳው መግለጫው በቤተክርስቲያኗ ላይ በደልና መከራ ያደረሱትን ክፍሎች ግን አላስታወቀም።

” ለረጅም ዘመናት ጸንታ የቆየችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ መንበር፣ አንድ ሲኖዶስ እና አንድ ፓትሪያርክ የሚለውን የቤተ ክርስቲያኗን ሕግና ቀኖና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ሁልጊዜም ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስገነዝባል” ያለው መግለጫው ሙሉ ቃሉ ከታች ቀርቧል።

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

በረዥሙ የሀገረ መንግሥትነት ታሪካችን ውስጥ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ወሳኝ የታሪክ አንጓዎችና ውጣውረዶች ብዙ ናቸው። ቢሆንም ግን በታሪካችን ሂደት በገጠሙን ፈተናዎች ወድቀን ሳንቀር ፈተናዎችን በአኩሪ ገድል እየተሻገርን አኩሪ ሀገራዊ የጋራ እሴቶችን አፍርተን ከዚህ ደርሰናል።

ስለሆነም ይኸኛው ትውልድ የተረከባቸው በከፍተኛ ውጣውረዶች መካከል ተፈትነው ያለፉ፣ የነጠሩና በጋርዮሽ መስተጋብሮቻችን የተሳለጡ እጅግ የምንኮራባቸው የባሕል፣ የትውፊትና የታሪክ ሀብቶቻችን ዘርፈ ብዙ ናቸው።

በውልና በገሃድ እንደሚታወቀው በዘመናችን ሁሉ ላካበትናቸው ሀገራዊ እሴቶች እንደ ሌሎች ቀደምት ሃይማኖቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በታሪክ ሂደታችን ውስጥ እያጋጠሙን ከምናልፋቸው እንደ አንዱ የሚቆጠር ችግር ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጥሯል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ይህንን ፈተና በትኩረት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ የተፈጠረውን ችግር በቤተ ክርሰቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት መሰረት መፈታት አለበት የሚል እምነት በመያዝ ጉዳዩን ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ቀኖናው በሚፈቅደው የአሠራር ስርዓት እንዲፈታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጅ የተፈጠረው ችግር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግጋት መሰረት መፈታት ሲገባው ባለመፈታቱ ምክንያት ችግሮች በመባባሳቸው በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ለሰው ልጆች ሕይወት መጥፋት፤ አካል ጉዳት እና የምዕመናን እንግልት መድረስ የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን እረፍተ ነፍስ እንዲሰጥልን ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውንም ፈጣሪ መጽናናትን እንዲያድልልን እንመኛለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት እና አደጋውን በመገንዘብ እጅግ በበሰለ መንገድ በመጓዝ ታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ ጸንቶ እና ተጠብቆ እንዲቀጥል እና የተፈጠረው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከውይይቱ የሚያፈነግጥ አካል ካለ በሀገሪቱ ሕግ እና ስርዓት መሰረት እንዲፈታ ቤተ ክርስቲያኗ አቅጣጫ አስቀምጣ ሲሠራ የነበረበትን መንገድ እና የተሄደበት ርቀት የሰከነ እና ጥበብ የተሞላበት ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ይገነዘባል፡፡

ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ የተሄደበትን ርቀት እያደነቀ በዛሬው እለት በፌዴራል መንግሥት እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በተካሄደው ውይይት መግባባት ላይ በመደረሱ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል፡፡

በቀጣይም ለረጅም ዘመናት ጸንታ የቆየችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ መንበር፣ አንድ ሲኖዶስ እና አንድ ፓትሪያርክ የሚለውን የቤተ ክርስቲያኗን ሕግና ቀኖና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ሁልጊዜም ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

የሃይማኖት አባቶችም ችግሩ ካጋጠመበት ጊዜ ጀምሮ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ ጉዳዩ በሕግ እና ስርዓት እንዲፈታ ያሳዩት ትእግስት እና አስተውሎት የተሞላበት ተግባር ትምህርት የሚወሰድበት እና በቀጣይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች አርዓያ የሚሆን ነው፡፡

መላው የክልላችን ሕዝብ እና የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናንም ችግሩን ከሰማንበት ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ በሚፈቅደው እና ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሰረት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በጾም፣ በጸሎት እና ምህላ ላበረከታችሁት ፍጹም ሰላማዊ፣ የሰከነ እና በአስተምህሮት የጸና አካሄድ መንግሥት ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Exit mobile version