Site icon ETHIO12.COM

የ2.5 ኪ.ሜ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት…

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢጣልያ መንግስት ባገኘው ድጋፍ የሚያሰራው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የማስጀመርያ ስነሰርዓት ተከናወነ፡፡

በፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡

ፕሮክቱን በይፋ ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአራት አመታት በፊት በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማን ወንዞችና ዳርቻቸውን የማጽዳትና የማስዋብ አካል የሆነው ይህ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ለከተማዋ መዋብ የላቀ አስተዋጽዖ የሚያበረክት መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቶች በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 2.5 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን ወንዙንና ዳርቻውን የማጽዳት እና የማስዋብ እንዲሁም መሸጋገሪያ ድልድይ ግንባታዎችን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል፡፡

አቶ ጀማሉ ጀንበር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሀላፊ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማን ወንዞች በማጽዳትና በማስዋብ ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር እየተሰራ ያለው ስራ አካል የሆነው ይህ ፕሮጀክት የአካባቢውን ነዋሪ ችግር መቅርፍ የሚስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከጣሊያን መንግስት በተገኘ አምስት ሚሊዮን ዩሮ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በ23 ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለህዝብ አገልግሎት የሚውል ይሆናል::

Addis Ababa administration

Exit mobile version