Site icon ETHIO12.COM

የሰው ተኮር ፕሮጀክት አፈጻጸም በ60/90 ቀናት

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተባባሪነት ባለፉት ጊዜያት ሲከናወኑ የቆዩ የ60/90 ቀናት ሰው ተኮር ሥራዎችን ለተለያዩ የሚዲያ አካላት አስጎብኝቷል።

በ60/90 ቀናት የሚተገበሩ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ኅብረተሰቡንና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቀናዒ የሆኑ የግሉን ሴክተር በማስተባበር እየተከናወኑ እንደሚገኙ በጉብኝቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ አዶኒያስ ወ/አረጋይ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የተጀመረው እና ተሞክሮ ተወስዶ ዘንድሮም ተጠናክሮ የቀጠለው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች አጠቃላይ በመልካም አስተዳደርን ጨምሮ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች በተደራጀ መንገድ እየተሠሩ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ከፊታችን ባሉ ቅርብ ቀናት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ይበቃሉ።

በክፍለ ከተማው የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ለማደናቀፍ በመጠናቀቅ ላይ ወደሚገኘው አዲሱ ሕንፃ ሰነዶች የተዘዋወሩ መስሏቸው አጥፊዎች ሕንፃውን በእሳት የማቃጠል ሙከራ ቢያደርጉም አስተዳደሩ እንደገና ሕንፃው ከበፊቱ የበለጠ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ በላይ ታደለ የለሚኩራ ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።

የሰው ተኮር ዕቅዶችን በፍጥነት መሬት ማውረድ እንዲቻል እና ለዜጎች በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ዒላማ በማድረግ በክፍለ ከተማው የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በክላስተር ተከፋፍለው እንዲተገበሩ እየተደረገ ይገኛልም ሲሉ ገልጸዋል።

ለ2 ሺህ 400 እናቶች አገልግሎት የሚሰጥ የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግም አቶ በላይ ጠቅሰዋል።

አንድ ሺህ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን መመገብ የሚችል ማዕከል በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ በንግግራቸው የጠቀሱ ሲሆን ከ30 ለሚበልጡ እናቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጨምረው ገልጠዋል።

የመሬት፣ የወሳኝ ኩነት እና የቤቶች አገልግሎትን የመሳሰሉ ተግባራትን በአጠቃላይ በቴክኖሎጂ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር በሚቀጥሉት ቅርብ ቀናት በክፍለ ከተማው ይፋ እንደሚደረግ ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል

EPA

Exit mobile version