Site icon ETHIO12.COM

የአማራ ክልል 412 ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች አስረከበ

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ 412 ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች አስረከበ።

በሶስቱ ዙሮች እስካሁን ድረስ ከ1500 በላይ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ትራክተሮችን ለአርሶአደሩ ማሰራጨት ተችሏል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥቡ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ስራ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

አርሶአደሩም የተረከበውን ትራክተር በአግባቡና በጥንቃቄ በመጠቀም ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በኃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተወሰነው ውሳኔ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ፍይናንስን ወደ ገጠር እንዲሄድ በማድረግ ረገድ ለገጠር ፋይናንስ ጅማሮ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል።

ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ምርት ተሰብስቦ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ባለው ሂደት ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነትን መከላከል አስፈላጊ ነው በማለት ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ሉአላዊነትን በማስከበር ከተረጅነት በመላቀቅ የአድዋን ታሪክ በተግባር መድገም ይኖርብናል ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ኃ/ማሪያም ከፍያለው (ዶ/ር) በበኩላቸው ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ለየአካባቢው ሰነ-ምህዳር መሰረት አድርጎ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የአርሶአደሩን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት 20 በመቶ በመቆጠብ 80 በመቶውን ከባንክ ብድር በማመቻቸት አርሶአደሩ የትራክተር ባለቤት እንዲሆን የክልሉ ግብርና ቢሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።

ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችንና የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሉ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር ኃ/ማሪያም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝና ከሌሎች የእርሻ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለ3ኛ ጊዜ 412 ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ማስረከቡን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version