ትግራይ እንደ ቢያፍራ (Biafra)?

የኢትዮጵያ-ትግራይ( ወያኔ) ጦርነት እስካሁን ባለው ሁኔታ ብቻ እንኳን ብንመለከተው፤ ያስከተለውና እያስከተለው ያለው ሁለንተናዊ ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ጦርነቱ የቀጠለ በመሆኑ ይህ ውድመት ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በኔ ግምት ውድመቱን ለመቀነስ ያለን ብቸኛ መፍትሄ አንድ ነው፡፡ ይሄውም ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት፡፡ ጦርነቱ የግድ በጦርነት ብቻ ይቋጭ ማለትም አይደለም፡፡ በተለይም ወያኔ ካሁን በኋላ የሚፈይደው አንዳች ነገር እንደሌለ አምኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ቢሰጥ፤ አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም የትራይ ህዝብ ከቀጣይ ከባድ ውድመት መዳን ይችላሉ፡፡

Chuchu Alebachew opinion

ተመሳስሎሽ እና ልዩነት!

1. ፈር መያዥያ

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በአንዳንድ የትግራይ ኢሊቶች/አክቲቪስቶች እና አንዳንድ ወገኖች፤ ትግራይ እንደ ቢያፍራ(Biafra) ወይም ስሪላንካ ( Sri Lanka) አይደለችም አይነት ነገር ሲነገሩ ተስምተዋል፡፡ ከነዚህ ወገኖች ምኞት የምንረዳው ነገር ቢኖር፤ ምንም እንኳን በናይጀሪያም ይሁን በስሪላንካ በፌደራል መንግስታቶቹና በአማፂያኑ መካከል በተካሄደው ስቪል ዋር ፤ ጦርነቱ በተገንጣይ ወገኖች ተሸናፊነት የተደመደመ ቢሆንም፤ ከኢትዮጵያ አንጻር ግን የፌደራሉ መንግስትና የትግራይ አማፂ (ተገንጣይ) ሀይሎች የገበቡበት ጦርነት ግን በተገንጣዮ ቡድን(ወያኔ) ተሸናፊነት ሊደመደም የሚችል ጦርነት አይሆንም ማለታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ በታሪክ የቢያፍራ ጦርነት የሚባለው ምንድን ነው ? የስሪላንካ የርስበርስ ጦርነትስ?

በታሪክ የቢያፍራ ጦርነት (Biafra war) እየተባለ የሚጠራው እ.ኤ.አ ከ1967 እስከ 1970 ዓ.ም የዘለቀውና the Nigerian Civil War በመባል የሚታወቀው ጦርነት ነው፡፡ የስሪላንካ የርሰ በርስ ጦርነት (Sri Lankan Civil War) በመባል የሚጠራው ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1983 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ስሪላንካ ውስጥ የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት ነው፡፡ በነዚህ ሁለት አገራት የተካሄዱት የርስበርስ ጦርነቶች አነሳስና ፍጻሜ የራሳቸው የሆነ የተለየ ባህሪ ቢኖራቸውም፤ ተመሳሳይነትም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለቱም አገራት የተካሄዱት ጦርነሮች የቅኝ ግዛት ሌጋሲ የሚንጸባረቅባቸው ሲሆን፤ አማጺያኑ የመገንጠል አላማ ያነገቡ ነበሩ፡፡ ሌለው ተመሳስሎሽ ደግሞ በሁለቱም አገራት በተካሄደው ጦርነት መንግስታቱ በአሸናፊነት የወጡ ሲሆን አማጽያኑ ደግሞ ተሸንፈዋል፡፡ በአንጻሩ በርካታ የሚያለዩባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በአገራቱ የቆየው የጦርነት እርዝማኔ እና በጦርነቶቹ የደረሱ ውድመቶች አንዱ የልዩነት ማሳያ ተድርገው ሊወሰዱ ይችላል፡፡

በዚህ መጣጥፍ የፀሀፊው ትኩረት በቢያፍራ ጦርነት ላይ ይሆናል፡፡ የጽሁፉ ዓላማም የዚህን ጦርነት መነሻና አላማ፤ እንዲሁም ፍጻሜ ከትግራይ ጦርት ጋር በማነጻጸር መመሳሰልና ልነቶቻቸውን ማሳየት ይሆናል፡፡

2. ቢያፍራ ማን ናት?

ናይጀሪያ ከታላቋ ብሪጣኒያ እ.ኤ.አ በ1960 ነጻነቷን ያገኘች አፍሪቃዊት አገር ናት፡፡ ናይጀሪያ ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪቃ አገራት ነፃነቷን በተቀናጀችበት ወቅት፤ አገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ሀይማኖቶች፤ ኢኮኖሚ ፤ ባህል፤ ህዝቦች/ብሄረሰቦች፤ ቋንቋዎችን የያዙና አንጻራዊ ነፃነት ያላቸው አካባበያዊ አስተዳሮች ነበሩ፡፡ ናይጀሪያ በኮሎኒያል አስተዳደር ወቅት በሦስት ክልላዊ አስተዳሮች የተዋቀረች አገር ነበረች፡፡ እነዚህ ክልላዊ አስተዳሮችም ሰሜን፤ምእራብና ምስራቅ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡እነዘህ ሶስት ክልላዊ አስተዳደሮችም በዋነኛነት የሦስት ዋና ዋና የተለያዩ ብሄሮች መኖርያዎች ናቸው፡፡ የሰሜኑ ክልል ነዋሪ ህዝብ በዋነኛነት ሀውሳ (Hausa) የሚባል ሲሆን ከሐይማኖት አንጻር በዋነኛነት የእስልምና እምት ተከታይ ነው፡፡ የምስራቃዊ ክልል ነዋሪ ማህበረሰብ ደግሞ በዋነኛነት ኢቦ(Igbo) የተባለ ማህበረሰብ የሚኖርበት ሲሆን ከሀይማት አንጻር ደግሞ በዋነኛነት የክርስትና እምነት ተከታይ ነው፡፡ ቢያፍራ በዋነኛነት Igbo የተሰኘው ህብረተሰብ የሚኖርበት የናይጀሪያ አንዱ ክልል ነው፡፡ .የምዕራቡ ክልል ነዋሪ ደግሞ በዋነኛነት ዩርባ(Yoruba) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ማህበረሰቡ ደግሞ የእስልምና እና ክርስተና እምነቶች ተከታይ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ- የትግራይን ሁኔታ ስንመለከተው ከናይጀሪያ-ቢያፍራ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስሪት አንጻር ብዙም ተመሰሳይነት አናገኝበትም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ በተለየ መልኩ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች አገር ናት፡፡ ከባህል፤ ኢኮኖሚ፤ከሀይማኖት ስብጥር አንጻር ሲመዘንም የትግራይ ክልል ከሌሎቹ የኢትዮጵያ 11/12 ክልሎች ጋር ሲነጻጸር የጎላ ልዩነት የሚታይበት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ የጎላ ልዩነት አለ ከተባለ ቋንቋ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

See also  አሁን ነገሮች ተቀያይረዋል - አዲስ አበባ የማይደረስባት መንግስት ሰማያት ሆናለች!!

3. የቢያፍራ ጦርነት መንስኤ ምንድን ነው ?

የተለያዩ ሊትሮቸሮች፤ለናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት መንስኤ ናቸው የሚሏቸውን የተለያዩ ምክንያቶች አስቀምጠዋል፡፡ ለምሳሌ Kirk-Greene(1975).የተባለ ፀሀፊ ለናይጀሪያ-ቢ ያፍራ ጦርነት መንስኤ (ምንጮች) ናቸው ያላቸውን የሚከተሉትን አምስት ምክንያቶች አስቀምጧል( Five sources of conflict): –

1. Politics as a source of conflict.

2. Economics as a source of conflict.

3. Society as a source of conflict.

4. Elites as a source of conflict.

5. History as a source of conflict.

ከላይ የተዘረዘሩትና ለናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት ምክንያት ነበሩ የተባሉትን ምክንያቶች በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትና በትግራዩ አማጺ ቡድን(ወያኔ) መካከል ለተቀሰቀሰውና ዛሬም ድረስ እየተካሄደ ካለው ጦርነት አንጻር መመልከት ይገባል፡፡ በእኔ እምነት ለናይጀሪያ- ቢያፍራ የርስ በርስ ጦርነት መቀስቀስ በምክንያትነት ከቀረቡት አምስት ምክንያቶች መካከል በዋነኛነት ሁለቱ ማለትም በተራ ቁጥር 1 እና 4 የተዘረዘሩት በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትና በወያኔ መካከል ለተቀሰቀሰውና ወደ የርስበርስ ጦርነት ላመራው ግጭት ምክንያቶች ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡ ሁላችንም እንደምናስተውሰው ጦርነቱ በግልጽ ከመጀመሩ በፊት በቀድሞዎቹ የኢህአዴግ ልጆች ማለትም፤ ብልጽግና መራሽ በሆነው የፌደራል መንግስትና የትግራይን ክልል ይመራ በነበረው ወያኔ መካከል ጥልቅ የሆነ የፖለቲካ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ እንደ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በዋና ዋነ እና ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ጭምር በኢሊት ደረጃ መግባበት አለመቻሉ አንዱ ችግሮችን ለመፍታት እንቅፋት ሁኖ ከርሟል፡፡ ይህ ሁኔታ በ2013 ዓ.ም ለተቀሰቀሰው የርስበርስ ጦርነት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡ ከነዚህ ሁለት ምክንያቶች ውጭ የተዘረዘሩትና ለናይጀሪያ -ዲያፍራ ጦርነት በመንስኤነት የተጠቀሱት ምክንያቶች ግን በኢትዮጽያ- ትግራይ( ወያኔ) መካከል ለተቀሰቀሰው የርስበርስ ጦርነት በምክንያትነት ሊወሰዱ የሚችሉ አይደሉም ባይ ነኝ፡፡

4. በቢያፍራ ጦርነት የተሰሙ ዋና ዋና ትርክቶች ምን ነበሩ?

ለ ሦስት ተከታተይ አመታት በዘለቀው የናይጀሪያ-ቢያፍራ የርስበርስ ጦርነት፤በሂደቱ የደረሰውን ውድመት በመመልከት አንዳንድ ወገኖች የተለያዩ ትርክቶችን ይዘው ብቅ ብለው ነበር፡፡ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ከሆኑት የጦርነቱ ትርክቶች መካከል በኢቦ (Igbo) ማህበረሰብ ላይ ”ጀኖሳይድ“ ተፈጽሟል፤ እንዲሁም የፌደራሉ መንግስት “ረሀብን እንደ ጦርነት ስልት” ተጠቅሞበታል የሚሉት ትርክቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በ ኢቦ ማህበረሰብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል የሚለው ክስ ከብዙ ውዝግብና ጥናት በኋላ ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ሳይሆን የርስበርስ ጦርነት ነው ተብሎ እልባት ተሰጠው፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ በወንጀሉ ዙሪያ አብሮ ስሙ ይነሳና ይታማ የነበረው የእንግሊዝ መንግስት ትልቁን ሚና እንደተጫዎተ ይነገራል (Heerten & Moses, 2014). አንዳንድ ወገኖች በናይጀሪያ-ዲያፍራ ጦርነት ወቅት የነበረውን የታላቋ ብሪጣኒያ ተሳትፎ እንዲህ ገልጸውታል “The most important third party to the conflict was the UK“.

የናይጀሪያ ፌደራላዊ መንግስት ረሀብን እንደጦር መሳሪያነት ተጠቅሞበታል ለሚለው ክስ በአንድ ወቅት አስገራሚ ምላሽ መስጠቱ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ አንድ የናይጀሪያ ተወካይ በ1968 ዓ.ም ንያሚ ላይ በተደረገ የሰላም ንግገር እንዲህ ሲል መናገሩ ይነገራል “Starvation is a legitimate weapon of war, and we have every intention of using it against the rebels.” (Ayida, 1968; as cited in Akresh, Bhalotra, Leone, & Osili, 2017). እንደ ባለስልጣኑ አባበል በዲያፍራ ጦርት ወቅት የናይጀሪያ መንስት አማፂያንን ነጥሎ በረሀብ መቅጣት አንዱና ተቀባይነት ያለው የጦርነት ስልት አድርጎ ተጠቅሞበታል ነው፡ ይሄም ሁኖ በዚህ ጦርነት በርካታ የዲያፍራ ስቪሊያን በረሀብ እዳለቁ ታሪክ መዝግቦት አልፏል፡፡

ይሄንን ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ – ትግራይ ( ወያኔ) ጦርነት እንመልሰው፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበትና እየቀጠለ ካለው ጦርነት አንጻር ስንመለከት፤ ከላይ በናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት ወቅት የተከሰቱት የጦርነት ትርክቶች በኢትዮጵያ-ትግራይ( ወያኔ) ጦርነትም በወያኔና የውጭ ደጋፊዎቻቸው አማካኝነት የተነሱና እየተነሱ ያሉ ትርክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ትርክቶች እስካሁን ባለው ሁኔታ ተቀባይነት ያገኙ ባይሆንም፤ ጦርነቱ ባለመቋጨቱ መጨረሻው ልክ እንደ ናይጀሪያው የታወቀ አይደለም፡፡ ይሄም ሆኖ ወያኔና የትግራይ ኢሊቶች አጀንዳውን ዛሬም ድረስ አጠንክረው እየገፉበት ያለ ሲሆን፤ ይሄንን አጀንዳ በማራገብ በኩል አንዳንድ ምዕራባዊያን አገሮችማ ሚዲያዎቻቸውም ገዝተውት ይታያል፡፡ በተለይም ዛሬም ሆነ ነገ ላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስትና በትግራዩ ወያኔ መካካል እየተካሄደ ባለው ጦርነት “The most important third party to the conflict is/was the USA“ ተብላ መጠቀስ ያለበት ይመስለኛል፡፡

See also  የጦርነት ናፍቆታችንን ለታዘበ ድሆች አንመስልም !

ያም ሆነ ይህ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት ሩብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል የሚለው አባባል ከሀቅ የራቀ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ወያኔ በሚፈጥራቸው አንዳንድ ሳንካዎች መጎላደፎች ያጋጠሙ ቢሆንም፤ የትግራይ ህዝብ በረሀብ እንዳይጎዳ የፌደራሉ መንግስት በየብስና አየር የምግብና መድሀኒት አቅርቦት በስፋት ወደ ትራይ እንዲገባ ፈቅዷል፡፡ በዚህም አይደለም ህዝቡ የወያኔ ሰራዊትም የዚህ ተጠቃሚ ሁኖ መንግስትን እየወጋ ያለበት ሁኔታ እንዳለ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳይቀር የታዘበው እውነታ ነው፡፡ እንዴውም እኔ እንደማምነው፤እስካሁን ባለው የአለም የጦርነት ታሪክ እያወቀ ጠላቱን እየመገበ ከጠላቱ ጋር የሚዋጋ በአለም ላይ ብቸኛው መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ከትግራይ ህዝብ አንጻርም ቢሆን እውነታው የሚያሳየው ተገላቢጢሽ ነው፡፡ ለምሳሌ ምን እንኳን የትራይ ህዝብ በዚህ ጦርነት ለችገር መዳረጉ አጠያያቂ ባይሆንም በሩብ እየተጎዳ ነው የሚለው ግን ውሀ አይቋጥርም፡፡ ለምሳሌ ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብ አምርቶ ከሚያገኘውም ይሁን መንግስት በእርዳታ ከሚያቀርብለት የምግብ እህልና ቁሳቁስ እየቀነሰ በፈቃደኝነት ለትግራይ አማፂ ሰራዊት ሲደግፍ ማየት የተለመደ ሁኗል፡፡ ይህ ተግባር ቢያንስ በረሀብ እያለቀ ካለ ህዝብ የሚጠበቅ ተግባር ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ያም ሆነ ይህ የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን እውነታውን ያውቃልና፤ ለነዚህ ክሶች፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ፤ የኢትዮጵያን መንግስ ከማስፈራት የዘለለ እርምጃና ውሳኔ ሲወስዱ አልታዩም፡፡ የመጨረሻው መዳረሻቸውም የናይጀሪያ-ቢያፍረው አይነት ድምዳሜ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

5. የቢያፍራ ጦርነት እንዴት ተጠናቀቀ?

የናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት የተጠናቀቀው ለ3 አመታ ያክል ከተካሄደ በኋላ፤ በፌደራሉ መንግስት አሸናፊነትና በተገንጣዩ የዲያፍራ አማፂያን ተሸናፊነት ነው፡፡ የቢያፍራ ጦርነት ኦፊሰላዊ በሆነ መንገድ ተጠናቀቀው የሚባለው ጥር 15/1970 ሲሆን ይሄም የሆነው በጦርነቱ ወቅት ተሰውሮ የነበረውና የቢያፍራ ጦር ኩማንደር የነበረው ግለሰብ ጥር 14/1970 እጁን ለመንግስት መስጠቱን ተከትሎ ነው፡፡ ይህ በድንገት የቆመ ጦርነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ለናይጀሪያዊያን ትልቅ እፎይታን የሰጠ ሆነ፡፡ ይሄን ሁኔታ ተከትሎ የወቅቱ የናይጀሪያ አስተዳር መሪ ጀኔራል ያኩቡ ጎውን( Yakubu Gowon) ሦስት በ “R” ፊደል የተወከሉ ሃሰቦችን ለአለም አቀፉና ለናይጀሪያ ህዝብ አስተዋወቀ፡፡ His government introduced the popular three R;s ; which stood for Reconciliation, Rehabilitation, and Reconstruction.

ኢትዮጵያ- ከትግራይ (ወያኔ) ጋር የገባችበት ጦርነት ገና በሂደት ላይ ስለሆነ ከወዲሁ መቶ ፕረሰንት አሸናፊው እከሌ ነው ለማለት አይቻል ይሆናል፡፡ ይሄም ሁኖ በብዙ መስፈርቶች ይህ ጦርነት በፌደራሉ መንግስት አሸናፊነትና በወያኔ ተሸናፊነት እንደሚደመደም የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ይህ እምነትና ፍላጎት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎትና እምነት ጭምር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን በደረስንበት የጦርነት ደረጃ ወያኔ እንኳን የፌደራሉን መንግስት አሸንፌ መንግስት እሆናለሁ የሚለውን ህልሙንና ምኞቱን ከሞላ ጎደል የተወው ይመስላል፡፡ አሁን መገመት እንደሚቻለው፤ ከወያ አንፃር ይህ ጦርነት እንዲጠናቀቅ የሚፈልገው በአቻነት ነው፤ ይሄም ማለት ወያኔ በድርድር “NO VICTOR, NO VANQUISHED“ በሚል የጦርት መርህ መሰረት ጦርነቱ እንዲቋጭ ይፈልጋል፡፡ ወያኔ ከተሳካት ይህ ሁኔታ/መርህ በናይጀሪያ-ዲያፍራ ጦርነት ወቅት የጦር መኮንን በኋላም የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት በነበሩት የተከበሩ ኦሊሴጎ-ኦባሳንጆ በሚመሩት የሰላም ድርድር ላይ ስምምነት እንዲደረስበት የሚፈልግ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ አስቸጋሪው ነገር የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ይህ ጦርነት “NO VICTOR, NO VANQUISHED“ በሚል መርህ/ስምምነት መሰረት እንዲቋጭ ይፈቅዳሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የናይጀሪያ-ዲያፍራ ጦርነት የተጠናቀቀው በ3 አመታት ውስጥ ያውም ጥር ወር ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ-ትግራይ( ወያኔ) ጦርነት ከተጀመረ ስንት አመት ሆነው? ሁኔታው ፊት ለፊታችን ካለው ጥር ወር ጋር ይገጣጠም ይሆን ? ማን ያውቃል፡፡ ሁሉንም ለማየት የነገ ሰው ይበለን፡፡ ገራሚው ነገር የናይጀሪያ-ቢያፍራን ሆነ የኢትዮጵያ-ትግራይ (ወያኔ) አማፅያን መሪ የነበሩትና የሆኑት የመንግስ የጦር መኮንን የነበሩ ከዳተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው፡፡

See also  በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ - ክፍል 2

6. የቢያፍራ ጦርነት ያስከተለው ጥፋት

የናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት ያስከተለው ጥፋት እጅግ ከባድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንዳንድ ጸሀፍት እንደሚሉት በጦርነቱ ወቅቱ ተከስቶ የነበረው ረሀብ እጅግ ከባድ ነበር፤ “The levels of starvation in Biafra were three times higher than the starvation reported during World War II in Stalingrad and Holland ( Mustell,1977).” በዚህም መሰረት አጠቃለይ በጦርነቱ የጠፋው የሰው ሂዎት ከ1 እስከ 3 ሚሊየን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ አንዳንዶች ይሄንን ቁጥር እስከ 5 ሚሊዮን ያደርታል፡፡ ሁሉም የሚስማበት ነገር ቢኖር አብዛኛው እልቂት የተከሰተው በረሀብ ስለመሆኑ ነው፡፡ Akresh, Bhalotra, Leone, & Osili, (2017). የተባሉ ስኮላርስ እንዳሉት “It was the first African war to be televised, and millions around the globe witnessed the large-scale devastation that ensued in the war-torn region.”

የናይጀሪያ-ቢያፍራ ጦርነት ያስከተላቸው ውጤቶች (The Immediate Impact of the Biafra War) የሚከተሉት ነበሩ፡፡

1. የበርካታ ስደተኞችና ተጎጅዎች መከሰተ፤

2. ከባድ ረሀብ (Hunger)፤

3. የሰብአዊነት ድጋፍ ስራዎች መስተጓጎል፤

4. ማህበራዊ ቀውስ መፈጠር፤

5. የኢኮነሚ ድቀት(ድህነት) ናቸው፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያ- ትግራይ(ወያኔ) ጦርነት የሚያስከትለው የተጠቃለለ ውጤት ከጦርነቱ መጨረሻ በኃለ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከወዲሁ እታዩ ያሉ ሁለንተናዊ ወድመቶች ግን አስፈሪ ናቸው፡፡ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖችና በስቪላን ላይ እየደረሰ ያለው ሂዎት መጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በትግራይ፤አማራ እና አፋር ክልች እየተስተዋለ ያለው የተፈናቃዮችና ተጎጅዎች ብዛት የትየለሌ ነው፡፡ ወያኔ በሚፈጥረው ሳንካ ሰብኣዊ ድጋፍን በሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ጦርነቱ በደረሰባቸው ሁሉም አካባቢዎች ማህበራዊ ቀውስ እየተከሰተ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ውድመትና መቀዛቀዝ በስፋ በመታየቱ ድህነትም በዚሁ ልክ የመስፋት እድሉ እየጨመረ ነው፡፡

በአጠቃለይ የኢትዮ-ትግራይ (ወያኔ) ጦርት አሁንም ላይብ በመሆኑ አጠቃለይ ውድመቱን ከወዲሁ መናገር አይቻልም፡፡ ሁኖም ግን ከወዲሁ እየታዩ ያሉትን አጠቃላይ ውድመቶችና ጥፋቶች በማየት፤ ይህ ጦርነት እንደ አጠቃለይ በኢትዮጵያ ደረጃ በተለይም ደግሞ በአማራ፤ አፋርና ትግራይ ክልሎች አስትሎት የሚያልፈው ውድመት ቀላል እንደማይሆን ለመተንበይ አይከብድም፡፡ በተለይም ጦርነቱ የሚራዘም ከሆነ፡፡ ስለሆነም ዋነኛው መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ጦርነቱን በአጭር ጊዜ መቋጨት ሁኖ በሂደቱም ውድመቱን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰሩ መሄድ ይገባል፡፡

7 . ቀጣዩን ውድመት እንዴት መቀነስ ይቻላል ?

የኢትዮጵያ-ትግራይ( ወያኔ) ጦርነት እስካሁን ባለው ሁኔታ ብቻ እንኳን ብንመለከተው፤ ያስከተለውና እያስከተለው ያለው ሁለንተናዊ ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ጦርነቱ የቀጠለ በመሆኑ ይህ ውድመት ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በኔ ግምት ውድመቱን ለመቀነስ ያለን ብቸኛ መፍትሄ አንድ ነው፡፡ ይሄውም ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት፡፡ ጦርነቱ የግድ በጦርነት ብቻ ይቋጭ ማለትም አይደለም፡፡ በተለይም ወያኔ ካሁን በኋላ የሚፈይደው አንዳች ነገር እንደሌለ አምኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ቢሰጥ፤ አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም የትራይ ህዝብ ከቀጣይ ከባድ ውድመት መዳን ይችላሉ፡፡

ጦርነቱን በማሳጠር ቀጣይ ውድመቶችን እንከላከል !

ድል ለመከላከያ ሰራዊታችንና በሱ ስር ለሚመሩት ሁሉም የፀጥታ ኃይሎቻን !!

Leave a Reply