Site icon ETHIO12.COM

ዲጂታል ሚዲያዎች የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተከትለው መስራት ይጠበቅባቸዋል

 ዲጂታል ሚዲያዎች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሳይሆን የሀገርንና የሕዝብን ሰላም መሰረት ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ገለጸ። የሀሰት መረጃዎችን፣ ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ ምክር ቤቱ ትናንት ባዘጋጀው የበይነ መረብ ሥነ ምግባር ደንብ ሥልጠና መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ በዲጅታል ሚዲያው በሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች ፣ የጥላቻ እና ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የማስተላለፍ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ዲጂታል ሚዲያው ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ መስራት ካልቻለ በሀገር ደህንነትና በሕዝብ ሰላም ላይ ስጋት ስለሚፈጥር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትም ዲጂታል ሚዲያዎች የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው እንዲሰሩ የበይነ መረብ የሥነ ምግባር ደንብ አዘጋጅቷል።

ሀገራዊ ሰላምና ደህንነትን እንዲጠበቅ መስራት የሁሉም ሚዲያ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተው፤ ዲጂታል ሚዲያው የሀገርንና የሕዝብን ደህንነትና ሰላም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር በተከተለ መልኩ መስራት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ሚዲያ ተደራሽነት እየጨመረ ነው ያሉት አቶ አማረ፤ ዲጂታል ሚዲያዎች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሰላም መሰረት ባደረገ መልኩ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ባዘጋጀው የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንብ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር የተከተለ ዲጂታል ሚዲያ በሀገር ግንባታና ለሕዝቡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ በአንጻሩ ሥነ ምግባርን ያልተከተለ፣ ግጭት ቀስቃሽ፤ የሀሰት መረጃዎችንና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያስተላለፉ ዲጂታል ሚዲያዎች የሕዝብ ሰላምና የሀገር ስጋት መሆናቸውን አመልክተዋል።

 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ በዲጂታል ሚዲያዎች የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እውቅና የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመው፤ ዲጂታል ሚዲያዎች ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ረገድ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በተከተለ መልኩ መስራት አለባቸው ብለዋል። የዲጂታል ሚዲያዎች ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ መልዕክት ከማስተላለፍ ድርጊታቸው ተቆጥበው ሥነ ምግባርን አክብረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል

በበይነ መረብ ጋዜጠኝነት የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ሃይሉ በአብዛኛው በዲጂታል ሚዲያው እየተሳተፈ ያለው ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጪ መሆኑን ጠቁመው፤ የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡ የሚመለከተው በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ሆነው በዲጂታል ሚዲያ ተሳትፎ ያላቸውን ነው ብለዋል። በዲጂታል ሚዲያ የሀሰት መረጃ፣ የጥላቻና የግጭት ጉሰማ መልዕክት የሚያስተላልፉት በሙያው ዕውቀቱና ሥነ ምግባሩ የሌላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ለህብረተሰቡ ማሳወቅና ማስገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ዛሬ ግለሰቦች በዲጂታል ሚዲያዎች የታዋቂ ሰዎችና የፖለቲከኞችን ስም በመጠቀም የሀሰት መረጃና የጥላቻ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ ያሉት አቶ ታምራት፤ ስለ ዲጂታል ሚዲያዎች በትክክል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ጠብቀው ከሚሰሩ ሚዲያዎች ይጠበቃል ነው ያሉት።

ጌትነት ምህረቴ አዲስ ዘመን  መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version