Site icon ETHIO12.COM

ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ መዝብረዋል የተባሉ 49 ሰዎች ክስ ተመሰረተባቸው

ኮሚቴው ከሕዝቡና ከተቋማት ከደረሱት ጥቆማዎች ውስጥ በ78 ሚሊዮን ብር ምዝበራ የተጠረጠሩ 49 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፀረ ሙስና ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚቴው ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከሕዝቡና ከተለያዩ ተቋማት ከአንድ መቶ በላይ ጥቆማዎችን ተቀብሏል፡፡

ከመጡት ጥቆማዎች መካከል ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ምዝበራ በመፈፀም የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦች ላይ መዝገብ ተደራጅቶ ክስ ተመስርቷል ብለዋል፡፡

ኮሚቴው ለሙስና ይበልጥ ተጋላጭ ዘርፎችን በመለየት እና እቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን አንስተው፤ በእቅዱም ከዚህ በፊት በከባድ ሙስና ተጠርጥረው የነበሩ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሂደታቸው ያላለቁ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዲቻል ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችና ከየተቋማቱ የሚመጡ ጥቆማዎችን እየሰበሰቡ የሚያደራጁና የጥቆማዎችን ትክክለኛነት እየፈተሹ መረጃዎችን በመሰብሰብ የምርመራ ሥራውን የሚመሩ ንዑስ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም ሕዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ከተቋማት እና ግለሰቦች አዳዲስ የሙስና ጥቆማዎችን የመቀበል እና የማደራጀት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በተከናወነ የማጣራት ሥራም በሙስና የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦችን ያካተቱ አራት መዝገቦችን በማደራጀት ለፍርድ ቤት ማቅረብ ተችሏል ያሉት ኃላፊው፤ መረጃዎችን ከማደራጀትና ከማጥራት ጎን ለጎን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራም ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በቀሪ ግለሰቦች ላይ የቀረቡ ጥቆማዎችን በተቋቋሙት ንዑስ ኮሚቴዎች አማካኝነት የማደራጀትና የማጥራት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ግለሰቦችን ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን ምዝበራ የተፈፀመበትን ሀብት የማስመለስ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ሙስናን የመዋጋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ሰብሳቢው፤ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ጥቆማዎችን መስጠቱን መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሙስና ወንጀል ውስብስብ እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ጥቆማ ከመስጠት ባለፈ ወንጀለኞችን በማጋለጥና አሳልፎ በመስጠት ለሥራው መሳካት የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version