Site icon ETHIO12.COM

ኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

ባለስልጫኑ ለኢሳት በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ ላይ፤ ቴሌቪዥን ጣቢያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ በመረጃ ያልተደገፉ/ያልተረጋገጡ የህዝቦች መተማመንና አንድነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ1238/2013 የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣን አዋጅ 1185/2012 እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በመጣስ ላይ ይገኛል ብሏል።

ባለስልጣኑ ለአብነት ብሎ በቴሌቪዥን ጣቢያው የተፈጸሙ ግድፈቶችን የጠቀሰ ሲሆን፤ ጣቢያው የካቲት 23/2015ዓ.ም በዕለቱ የኦሮሚያ ክልል ኢአ ዙሪያ ሸገር ከተማ የዜጎችን ቤት በማፍረስ ግፍ መፈጸሙን ድምጻዊ መብሬ መንግስቴ ተናገረ፡ ድምጻዊው በዜጎች ላይ የተፈጸመው በደል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ገልጿል…..” የሚል ዜና የቀረበ ሲሆን በዘገባው የተጠቀሱ አካላት ሃሳብና አስተያየት ሳይካተት ድምዳሜ ላይ የደረሰ በመረጃ ያልተደገፈና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ አስተላልፏል ሲል አስታውቋል፡፡

በተጨማርም ኢሳት፤ መጋቢት 6/2015ዓ.ም “የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ከተማው የሚገቡ ዜጎችን አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭና የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚጥስ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ” የሚል መረጃ ያቀረበ ሲሆን፤ በዘገባው የጫካ ፕሮጀክት አንድ ሚሊየን የሚጠጋ በጣም አቅመ ደካሞች የሚባሉ ዜጎች አፈናቅሏል፤ የቤት ፈረሳውን የሚመራውን ግብረ ሀይል ቤቶቹን ከማፍረስ ባሻገር የንብረት ዘረፋ ውስጥ ተሰማርተዋል፤ የሚገድሉ፣ የሚዘርፉ እና የሚደበድቡ ሰዎች ናቸው እያስተዳደሩን ያለው” የሚሉ በሰነድ/በማስረጃ ያልተረጋገጡና የተቋማትን መልካም ስም የሚያጠፉ፤ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን አሰራጨቷል ሲል ነው ባለስልጣኑ የገለጸው።

መጋቢት 12/2015ዓ.ም ደግሞ፤ “በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ እድሜያቸው 18 አመት ያልሞላ ታዳጊዎች ለወታደራዊ ስልጠና እየተመለመሉ ነው ሲሉ ወላጆች ለኢሳት ገለጹ” በሚል አርዕስተ ዜና ስር በከተማዋ ከክልሉ ተወላጆች ውጪ ያለ አካል እንዳይኖር የማድረግ እቅድ አለ የሚል ዘገባ ቀርቧል ያለው ባለስልጣኑ፤ መረጃው ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ፤ የተዓማኒነት(የምንጭ) ችግር የተስተዋለበት ምንጮቻችን ነገሩን ከማለት ውጪ የድርጊቱን እውነትነት ሊያረጋግጡ በሚያስችሉ ማስረጃዎች ያልተመላከቱና በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ስጋትን ሊፈጥር የሚችል ጥንቃቄ የጎደለው ዘገባ ነው ሲል አስታውቋል።

መጋቢት 13/2015 ዓ.ም ጣቢያው አዲሱ የሽገር ከተማ አስተዳደር ምስረታን ምክንያት በማድረግ በተጠና እና ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ማንነት የሌላቸው ዜጎችን ቤት ለይቶ እያፈረሰ እንዲሁም ከክልሉ እያስወጣ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ዘገባ ቀርቧል ሲልም ነው ባለስልጣኑ የጠቀሰው። ዘገባው የተነሳውን ርዕሰ ጉዳይ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ጥረት ያላደረገና በህዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል የሚችል ነውም ሲል ገልጿል።

መጋቢት 22/2015ዓ.ም ደግሞ “ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የተመለመሉ የአማርኛ አስተማሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ተሰማ” በሚል ዘገባ ጣቢያው ትምህርት ቢሮን ሆነ ሌሎች ተገቢ አካላትን ሳያካትት በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታን ሊፈጥር የሚችል ኢ-ሚዛናዊ ዘገባ አቅርቧልም ነው የተባለው።

ቴሌቪዥን ጣቢያው ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ከጋዜጠኝት ስነምግባርና መርህ ጋር የሚጣረሱ ማህበራዊና ተቋማዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ክፍተት ያለባቸውን ዘገባዎች በማሰራጨት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/1(ሀ)እና (ለ) ፕሮግራሞች ወይም ዜናዎችን የተለያዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ አጠቃላይ ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ሚዛናዊ እና ከአድሎ የጸዱ አድርጎ ማቅረብ፤ የሚሰራጨው ፕሮግራም ወይም ዜና ይዘትና ምንጭን እውነተኛና ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሰራጩ ሪፖርቱ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሚል የተቀመጡ ህጎችን ያላከበረ መሆኑ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/2(መ)(ሠ) የወንጀል ድርጊት እንዲፈጸም እና ሰላም እና ጸጥታ እንዲደፈርስ የሚቀሰቅስ መሆን የለበትም ያለው የባለስልጣኑ ደብዳቤ፤ በብሮድካስት አገልግሎት ለስርጭት የሚቀርብ ማንኛውም ፕሮግራም ወይም ዜና የማንኛውም ሰው ዘር ቋንቋ እና ብሄርን መሰረት በማድረግ እንዲጠላ ወይም እንዲገለል የሚቀስቅስ መሆን የለበትምየሚሉትን ድንጋጌዎችን የጣሰ ስለመሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1185/2012 አንቀጽ5 ማንኛውም ሰው የሀሰት መረጃን በአደባባይ፣ ስብሰባዎች በብሮድካስት፤ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፤ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ተግባር እነደሆነ የጠቀሰው ደብዳቤው፤ የኢሳት ዘገባዎች እነዚህን ድንጋጌዎች የጣሱ መሆናቸው ተስተውለዋል ነው ያለው።

ጣቢያው ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ሀሰተኛ fገባዎችን በማሰራጨት በህዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑንም ባላስልጣኑ አስታውቋል።

ENA

Exit mobile version