Site icon ETHIO12.COM

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና በድርጊቱ የተሳተፉትን ለህግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና በድርጊቱ የተሳተፉ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገለጸ።

በፍልሰት ችግሮች እና ሁለንተናዊ መፍትሄዎች ላይ የመከረና የልምድ ልውውጥ የተካሄደበት አገርአቀፍ መድረክ ዛሬ በድሬዳዋ ተካሂዷል።

ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የአስተዳደሩ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት፣ እንደ አገር በተቋቋመው ብሔራዊ ምክር ቤት እና በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ተቋቋሞ ወደሥራ መገባቱ ጉዳዩ የተሻለ ትኩረት እንዲያገኝና ውጤት እንዲያመጣ አግዟል።

በተለይ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር ለተቋቋመው ጥምረት እና ምክር ቤት አዲስ አሠራር፣ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ተሟልቶ ወደሥራ በተቀናጀ መንገድ መግባቱ ድሬዳዋን ለፍልሰት እንደመሸጋገሪያ የማድረጉ ዝንባሌ እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል።

“ይበልጥኑ ከፍልሰት ወደቤታቸው ለተመለሱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መሰራቱ የተሻለ ውጤት ለማስገኘት አስችሏል” ብለዋል።

ለአብነትም ከተለያዩ የአረብ እና ጎረቤት አገራት ወደኢትዮጵያ የተመለሱ 120 ወጣቶች በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እና የፕላስቲክ ኮዳዎችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ሀርቢ ገለጻ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና በድርጊቱ የተሳተፉትን ለህግ ለማቅረብ የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት ይሰራል።

በመድረኩ ከፌደራልና ከክልሎች የሥራ አፈጻጸም የተሻሉትን ልምዶች በመቀመር በቀጣይ የተጀመሩትን ተግባራት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ቅንጅታዊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሌላው ውይይቱን የመሩት የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው፣ እንደ አገር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት መዋቀሩን አስታውሰዋል።

“ብሔራዊ ምክር ቤቱ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ጉዳዩ የመንግስት ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ለመፍትሄው የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

በአካል፣ በስነ ልቡና፣ በህይወት እንዲሁም በምጣኔሃብት እና በማህበራዊ መሠረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለው በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ከ10 ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዋንኛው መሆኑንም አቶ አብርሀም ጠቁመዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ከማቋቋም ባለፈ በየክልሉ ተመሳሳይ አደረጃጀቶች ወደተግባር ገብተዋል።

“በእነዚህም በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት ቢሰራም ከችግሩ ስፋት አንፃር በዙ ይቀራል” ብለዋል።

“በተለይ በዚህ ወንጀል የተሰማሩ ደላሎች፣ መልማዮች እና አዘዋዋሪዎች በሦስት የድንበር መሻገሪያ አቅጣጫዎች ከአዲስ አበባ እስከ ደቡብ አፍሪካ እና አረብ አገራት የዘረጉትን የትብብር ጥምረት በተቀናጀ እና በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመበጣጠስና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ይሰራል” ብለዋል።

እንደአቶ አብርሀም ገለፃ በብሔራዊ እና በክልሎች ደረጃ የተዋቀረው የፍልሰት ትብብር ጥምረት አደረጃጀቶች ህገ ወጥ ፍልሰትን ለማስቀረትና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት ፍሬያማ ለማድረግ ህጋዊ የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ማመቻቸት ወሳኝ ነው።

በቅርቡም መንግስት ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑት የአገራችን ወጣቶች በሳዑዲ አረቢያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ማመቻቸቱ እና በሌሎችም አገሮች ተመሳሳይ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑ የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር የፓለቲካ አመራሮች ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት እያሳዩ ያሉት ቁርጠኝነት እና በፍልሰት ተመላሾች ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት እንደ አገር በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውንም አቶ አብርሀም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የብሔራዊ፣ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተሞች የፍልሰት ትብብር ጥምረት አመራሮች ተሳትፈዋል።

አመራሮቹ በድሬዳዋ አስተዳደር ከተለያዩ አረብ እና ጎረቤት አገራት ከፍልሰት ለተመለሱ ወጣቶች አስተዳደሩ ከአክሽን ፎር ዲቨሎፕመንት ከተባለ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ወጣቶች ሥራ ፈጥረው ህይወታቸውን እንዲመሩ ያከናወናቸውን ሥራዎችን ተመልክተዋል።

ተወያዮቹ በነገ ዕለትም በአወዳይ ከተማ የፍልሰት ተመላሾችን የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፍራው ተገኝተው ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version