Site icon ETHIO12.COM

በሱዳኑ ግጭት ስምንት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተሰማ

በኃያላኑ የሱዳን የጦር መሪዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ ስምንት ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ።

12ኛ ቀኑን ባስቆጠረው ግጭት ከሟቾች በተጨማሪ አራት ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው በኤምባሲው የዲያስፖራ ክፍል የዜጎች ጉዳይ ክትትል ባልደረባ የሆኑት ነጂብ አብደላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ነጂብ ገለጸ ኢትዮጵያውያኑ ሞት እና ጉዳት የደረሰባቸው በተባራሪ ጥይት ወይም በፍንዳታ ምክንያት በሚፈጠር ፍንጣሪዎች መሆኑን ተናግረዋል።

“ለምሳሌ ከተገደሉት መካከል አንዷ የሆነችው ሴት ኢትዮጵያዊት በፍንዳታ ፍንጣሪ ተመትታ ነው ሕይወቷ ያለፈው። እሁድ ዕለት ደግሞ የአየር መቃወሚያ ተተኩሶ መኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ ሁለት ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ደረጃ ቆስለዋል” ሲሉ ዲፕሎማቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ነጂብ በሱዳን ያለው ግጭት የፀጥታ ስጋት በመፍጠሩ ምክንያት ከአገሪቱ መውጣት የሚፈልጉ ዜጎች መኖራቸውን እንዲሁም ቀድመው ከአገር የወጡ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ገልጸዋል።

በሱዳን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ከሱዳን መውጣት የሚፈልጉ ዜጎችን ከሱዳን ለማውጣት ምዝገባ መጀመሩን አቶ ነጂብ ጭምረው ተናግረዋል።

ኤምባሲው አቅም ያላቸው ከሱዳን መውጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክር እየሰጠ መሆኑን እና አቅም የሌላቸውን ደግሞ በአውቶብስ እስከ የኢትዮጵያ ድንበር ለመውሰድ ምዝገባ መጀመሩን አመልክተዋል።

“ችግር ውስጥ ነን እያሉን ያሉት በርካቱም ያሉት ብቻ ናቸው። በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ምንም ችግር አልደረሰባቸውም። ከዚህ ቀደም ባሉበት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት” ብለዋል።

ካርቱም ውስጥ በውጊያው ምክንያት ከፍተኛ ችግር እንዳለ የሚያስረዱት አቶ ነጂብ ፤ መደብሮች ዝግ በመሆናቸው መሠረታዊ ሸቀጦችን መግዛት እንደማይቻል፤ ሱቆች ክፍት ቢሆንም ምንም የመግዛት አቅም የሌላቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ተናግረዋል።

“በእድሜ የገፉ ምንም መሥራት የማይችሉ አዛውንቶች አሉ። ባል የሌላቸው እናቶች ከልጆቻቸው ጋር መሄጃ አጥተው ተቀምጠዋል። ህሙማንም አሉ። እነዚህን ዜጎች ነው ወደ አገራቸው ለመመለስ እየመዘገብን ያለነው።”

በኤምባሲው የሚመዘገቡት ኢትዮጵያውያኑ ከካርቱም ተነስተው – መደኒን – ገዳርፍ – ገለባት ተብለው በሚጠሩ ከተሞችን አቆራርጠው መተማ ለመድረስ 550 ኪሎ ሜትር በአውቶብስ መጓዝ እንደሚኖርባቸው ዲፕሎማቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሱዱን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ነጂብ ፣ ከሱዳን መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ ዜጎችን ከሱዳን የማስወጣቱ ሥራ ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል።

በካርቱም እየተካሄደ ባለው ውጊያ ምክንያት የኤምባሲው ሠራተኞች ወደ ገዳሪፍ ተዘዋውረ መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን የገለጹት አቶ ነጂብ ፣ በግጭቱ መጀመሪያ ቀናት ላይ በካርቱም በሚገኘው ኤምባሲ ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበረም አስታውሰዋል።

አቶ ነጂብ እንዳሉት ኤምባሲው ላይ ጉዳት የደረሰው ሆን ተብሎ ዒላማ ተደርጎ ሳይሆን፣ በተኩስ ልውውጥ መካከል የሕንጻው ግድግዳ መመታቱን ተናግረዋል።

“ኤምባሲው ዒላማ ተደርጎ አይደለም። ኤምባሲው ያለበት ቦታ የግጭት ቀጠና ነው። በወታደሮች ተከቦ ነው የሚገኘው” ብለዋል።

ኤምባሲው ከቀናት በፌስቡክ ገጹ በሱዳን ስላለው ሁኔታ ዜጎች መረጃ ‘መለዋወጥ እና ምክር’ ካሻቸው +249911646547 መደወል እንደሚችሉ ገልጾ ነበር።

የአገሪቱ ጦር ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ የሆኑት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሔሜቲ መካከል ሱዳንን ለመቆጣጠር በተፈጠረው ፉክክር አገሪቱ ወደ ግጭት ገብታለች።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል ባለፉት ቀናት በተደረጉ ወታደራዊ ግጭቶች በካርቱም እና በሌሎች የሱዳን ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ከ400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በርካታ አገራትም ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን ከሱዳን እያስወጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በተፋላሚ ወገኖቹ መካከል ተደርሷል።

ግጭቱን ተከትሎ ምግብ፣ መድኃኒት እና የሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት በካርቱም እና በሌሎች አካባቢዎች በመከሰቱ ነዋሪዎች ችግር ላይ ይገኛሉ።

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነትም እነዚህን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማቅረብ እና አገሪቱን ለቀው ለመውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።

source BBC Amharic

Exit mobile version