Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሸተተ ስጋ ጋር ያቆራኘው [የኤርትራ/ዊው] እይታ

“ከታች የቀረበው ጽሑፍ ከትግርኛ የተመለሰ- የኤርትራ/ውያን ምልከታ ነው” ነው ይለናል ጽሁፉን ተርጉሞ ያስረጫው የማህበራዊ ገጽ አባል። ጽሁፉ አሽሙር አዘል ሆኖ አማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን አለምግባባት፣ ወይም ግጭት ወይም ስሙ በግጽ ያልለየ ንቅናቄ መጨረሻውን ይተነብያል። “ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል” ሲል ኤርትራን ሆኖ አቋሙን ይስቀምጣል።

“ጽሁፉ ፍርሃት የወለደው ነው። ከኢትዮጵያ ቀውስ ጀርባ ማን እንዳለ ህዝብ እንዲረዳ ስለሚጠቅም እባካችሁን አትሙት፣ ነገሩ ምስጥን ነቀዝ ሊበላው አይነት እሳቤና ድሃ መላምት ነው። ” ብለው አንባቢያችን በላኩልን መሰረት እንዳለ አትመነዋል.

ቀናት ያለፈበት ሥጋ ከመሽተት አይድንም

ሞኛሞኝ ሴት የራሷ ወጥ ይጣፍጣል ይሉት ተረት እንደዛሬ ሁነኛ ትርጉሙን አግኝቶ አያውቅም ።

ብልሆች ለአመታት ፤ ሞኞች ደግሞ የእለቱን ያስባሉ ።
ከባዱ የጨለማ ጊዜ ሲያልፍ አያ ገብስ ክረምቱን ባሳለፈ ጎመን ላይ ሲመፃደቅበት ማየት ንቡር ሆኖ በገሃድ በኢትይጵያ ሰማይ ስር አይተናል ።

በአሁናዊ የምስራቅ አፍሪካ ላይ ቆሞ መፃኢውን መተንበይ አስቸጋሪ መጠላለፍ የሞላበት መሆኑ ነጋሪ ሳያሻው ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኗል ። አንዳንዱ አቅም አጥቶ ፤ ማሰሪያ እንዳጣ ሰው ፍልጡን መሬት ላይ ዘርግፎ ይሰንዳል ፤ አንዳንዱ ቂጡን ገልቦ እንደ አዞ ይውጣል ፤ አሳህን ከሱዳን ጀምረህ ወደ ኢትዮጵያ ገብተህ ስትፈትሽ እየህነው ያለው ሁሉ ግርም ይላል ።

መቼም የኢትዮጵያ ፖለቲካን ልክ እንደ ሁለቱ ሰካራሞች ነው ፤ ፑል ሲጫወቱ አምሽተው በብር ይጣሉና በአረቄ የሚታረቁ አይነት ነው ፤ እግራቸው እስኪሽመደመድ ሲጋቱ አድረው ተደጋግፈው የሚሄዱ አይነት ነው ፤ ሰክረዋል ስትላቸው ፈትል ገትረው በፈትል የሚራመዱ ፤ ውሃ ጠጥተዋል ሲባሉ ደግም በተቃራኒው ዝርግት ብለው ሜዳ የሚንደባለሉ ፤ የት ናቸው ? ወዴት ነው አቅጣጫቸው ፍፁም የማይገባ ውንግርግር ያለ ሆኗል ነገሩ ሁሉ ።

በመንገዱ ላይ እየተመላለስክ ፤ በመንገዱ ላይ ሂያጅ ሴት ትፈልጋለህ !

አንድ አገር ነው አሉ ሁለት ሴቶች በአንድ ወንድ ተቀናኑና ፤ አገሬው ከቦ በትዝብት እያዬ እየተቧቀሱ ሲናጩ ማየት ይዟል ፤ አንዷ ድስት ስትወረውር አንዷ ፈርኔሎ ( የከሰል ምድጃ ) ትወረውራለች ፤ በአጠቃላይ ከተማው ሁካታ ነገሰበት ፤ ጎረቤቶች ተረበሹ ፤ ለአይን ያዝ ሲያደርግ ወደ ረብሻው እንዳይገቡ የአካባቢው መሰብሰብ ጀመረ ፤ በመጨረሻም አገሬው አቅሉን አሟጦ የነዚህ ረብሸኞች ጉዳይ ለፍርድ መቅረብ አለበት ወደሚል ውሳኔ ገቡ፤ በዚህም መሰረት ሴቶቹ ተከሰው ወደ ችሎት እንዲቀረቡ ተደረገ ።

ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎቹም በነዚህ ሁለት የተለከፉ ሴቶች ከጉዳያቸው እንዲቀሩ ሆነ ፤ ሁሉም ከዋርካ ዛፍ ጥላ ስር እንዲሰበሰቡ ግድ ሆነ ፤ ወንድም ጭራውን ሴቱም ነጠላውን አንጠልጥለው ወደ ችሎት ወረዱ ። የአገሬው ሹም የነዚህ ሴቶች ጉድ ለመስማት በሽበት የተሸፈወነውን ጆሮአቸውን እየኮረኮሩ ሲሰሙ ከቆዩ በኋላ እንዲህ የሚል ሃሳብ ሰጡ – –

“መቼስ ምቀኛ ጠላቱን ይተክላል ፤ ወዳጁን ደግሞ ይነቅላል አይደል የሚባለው ፣ እናንተ ደግሞ በጣም የምትቀራረቡ የልብ ወዳጆች እንደነበራችሁ ነው አገሬው የሚያውቀው ፤ ይሁንና በአንድ ወንድ ምክንያት አንባጓሮ ውስጥ ነው የቆያችሁት ፤ አሁን አገር ስለታወከ ጉዳያችሁን እናያለን

በማለት ጉዳያቸው እልባት እንደሚበጅለት አወጁ ።

በዚህ ጫጫታ በበዛበት ሙግት ” እሽሽሽ እሽሽሽ እስኪ ዝግ በሉ ” በማለት አፋቸው አስያዙአቸውና ፤ ወደ ጠቡ ያስገባቸውን ወንድ ጠሩና
” አንተ እሳ ማንኛዋን በመረጥክ ነበር ?”
በማለት ጠየቁት ። በአጎቶቹ መሀል ተቀምጦ ሙግቱን ሲሰማ የነበረው ወንዱ ሰው

” አይ – ክቡር ሆይ ፤ ከነቀዝ እና ከምስጥ ማንን ይመርጣሉ ቢባሉ ማንን ይመርጡ ነበር “
በማለት ጥያቄው በጥያቄ ለአገሬው ሹም መለሰላቸው ። ሹሙ ጥያቄው ግራ ገባቸው እና እኔ እንጂ ሲሉ መለሱለት ፤ በመልሳቸው የልብ ልብ የተሰማው ወንዱ ሰው ” ሁለቱም የእህል ቀበኞች ናቸው ፤ ምን በረከት አላቸው ” በማለት ሊድን በማይችል ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለማምጣት በከንቱ ሲደክሙ እንደቆዩ ለአገሬው መርዶውን አሰማ ።

ዓይናችን አድማ እያደረገ እንጂ የምናየው ነገርስ ….

ወያኔ (ትህነግ )— የኢትዮጵያ መንግስት በምዕራባውን ሃገራት ጫና አጀንዳዎቹ አደጋ ላይ የወደቀ ከመሆኑ አንፃር ፤ ውስጣዊ አንድነቱን ማፅናት የቸገረው ብልፅግና ስልታዊ አንድነት ( Tactical alliance ) በመመስረት
የ” ጊዜ መግዣ ዕድሎችን በማማተር ” ጨዋታ በመጫወት ላይ ይገኛል ። የብልፅግና ሰልፍ በሁለት ጎራ መከፈሉ ለወያኔ ( ለትህነግ ) መሪዎች ፍንትው ብሎ ተገልጾ ታይቷቸዋል ።

ወያኔ ( ትህነግ ) –

የውስጥ አንድነቱን መፍጠር ያልቻለው ብልፅግና ፤ የሒሳብ ስሌት ሲያጣፋ ወደ ቆየው ጠ/ ሚኒስትር ቀርቦ ሲሸረሽረው መሠንበቱ ብዙም ሊገርመን አይገባም ።
በአማራ ክልል የተሳው ህዝባዊ እንቢተኝነት ለኢትዮጵያ መንግስት እንቅልፍ የሚሰጥ አልሆነም ። በተራዘመ ሂደት የኢትዮጵያ ጠ/ሚንስትሩን ሊያዳክመው እንደሚችል ይገመታል ። ነገርየው እንጨት ሲፈልጥ የዋለ አባወራ ሺህ ፍልጦችን በአንዲት ልጥ ሊያስር እንደሚሞክር ማለት ነው ። ልጧ ብጥስ ያለች ጊዜ ፍልጦቹ ተበትነው ወደ መሬታቸው እንደማለት ነው ።

ደምረን ስናየው….

ሀ ) የኢዮጵያ መንግስት
ለጭፍራ ማሌሌት ( ትህነግ) ይቅርታ ያደረገላት ፤ ከሰራችው ወንጀል ነፃ ሆና እንድትኖር ሲሆን የከበሮ ድለቃው ግን ከነፃነት አልፋ ሥልጣን ለመካፈል የተስማማች ይመስላል ። ይህ ምንን ይወልዳል ? በጊዜ ሂደት በዝግታ የሚመለስ ይሆናል ።

ለ ) ጭፍራ ወያኔ ( ትህነግ ) ” የፕሪቶሪያ ስምምነት በጥምር ኃይሉ ፣ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግስታት ጥርጣሬ (ስንጥቃት ) ይፈጥራል ” የሚል እምነት ይዛ እንደገባችበት ቁልጭ ብሎ በገሃድ ግልፅ ሆኗል ። ስልታዊ ወዳጅነታቸውንም በሚገባ እየተገበሩ ነው ማለትም ይቻላል ።

ሐ ) የፕሪቶሪያ ስምምነት ፤ ብዙዎች በጥርጣሬ አይን የጎሪጥ እያዩት መሆኑ አገር ያወቀው ነው ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ በያዘው አካሄድ ለመሄድ ከመረጠ ፤ ጥንቃቄ ማድረግም አስፈላጊያችን ነው ፤ ምክንያቱም እያንዳንዷ እርምጃ እራሷን የቻለች ትርጓሜ ስለሚኖራት ።

መደምደሚያ– የኢትዮጵያን ኩነቶች በአፅንኦት እና በትኩረት መከታተል የምንገደድበት ጊዜ መጥቷል ። በአጠቃላይ ሁኔታው ፡ ለሰው ብለህ በላከው እጅህ ድንጋይ የመዝገን አይነት ነው የሚመስለው ፤ በእርግጥም ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው ።

ዋናውን ጽሑፉ ከእነ ባለቤቱ ከሚከተለው አድራሻ ያገኙታል

ይህ የዋናው ጽሃፊ የፌስቡክ መለያ ምልክት ነው

ጽሁፉን ያሰራጨው ውብሸት ሙላት በቴሌግራም ገጹ ነው።

Exit mobile version