Site icon ETHIO12.COM

ዛሬ ደግሞ መንግስትን በገባን ልክ እንነቁራለን!

Oluma M. Wodajo እንደጻፈው…!

የብልፅግና መንግስት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ከነበሯት መንግስታት ሁሉ ከሚለዩት ነገሮች አንዱ አንድም ብዙም መሆኑ ነው። Cohesive አይደለም። ሁሉም ባይሆኑ ከፊል ሹመኞቹ በሁለት እና በሶስት ቢላ የሚበሉ፣ የጎንዮሽ የሚጣለዙ፣ ህዝበኝነት እና ታይታ (populism and cheap popularity) ያነሆለላቸው አድር-ባዮች ናቸው። ከ22 ካቢኔት ሚኒስትሮች የተሾሙበትን ዘርፍ አጥርተው እና አድምተው የሚሰሩት ግማሽ አይሆኑም። በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ከሚመሩ ፕሮጀክቶች ውጪ ያሉት ስራዎች ፍጥነትም ጥራትም አጠያያቂ ነው።

የውስጥ ሰላም እና ደህንነት ጉዳይ በተመለከተ የሰሜኑ ጦርነት መቆሙ ትልቅ እመርታ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በየቦታው ያለው መፈናቀል፣ ግድያ እና የወንጀል መበራከት ከአምስት አመታት በኋላም መቀጠሉ አሳዛኝ እና አነጋጋሪ ነው። የፀጥታው ዘርፍ የፈለገ ዝግጁነት እና ብቃት ቢኖረው፤ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ካልታገዘ ተአምር ሊፈጥር አይችልም። መንግስት በተለይ የፖለቲካ ጉዳዮችን በፍጥነት እና በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ባለመቻሉ የሰላም እና የደህንነት ተቋማትን ስራ firefighting አድርጎታል። ዛሬም ድረስ የዜጎች መፈናቀል፣ ሞት እና ስቃይም ሊቆም አልቻለም። በዚህም ምክንያት ተቋማቱ ሊኖራቸው የሚገባው ህዝባዊ አመኔታ፣ ቅቡልነት እና ድጋፍ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ከጠ/ሚው ጀምሮ የመንግስት communication strategy ያለ እስከማይመስል ድረስ የአገላለፅ/የገለፃ ግድፈት፣ የመረጃ ክፍተት፣ የግልፅነት እጦት እና ከፊት ሆኖ የመምራት ችግር ተንሰራፍቷል። በዚህ በ”post-truth era” የራስን ዕውነት proactively በአግባቡ አቅዶ፣ መጥኖ እና ከሽኖ በማቅረብ ፋንታ በreactive engagement ላይ ተጠምዷል። ጠ/ሚ አብይም monologue ጥሩ የPR ስትራቴጂ ነው ብሎ አምኖ ይሁን ወይ በሌላ በመደበኛነት ጋዜጠኞችን (ሌላው ቢቀር የሚያዝባቸውን የመንግስት ሚዲየ ጋዜጠኞችን) ጠርቶ press briefing ለመስጠት እንኳን ዳተኛ ሆኖ መቀጠሉ ሁሌም እንዳስገረመኝ አለ።

የመልካም አስተዳደር ችግር በተለይ ሙስና/ሌብነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና የህግ የበላይነት ጉዳዮች ከመሻሻል ይልቅ ብሶባቸዋል። ጠ/ሚሩ ሌቦችን ስለመታገል እና ስለ “political market place” ደጋግሞ ቢናገርም የዚህ market place ሸማችም፣ ሻጭም፣ ደላላም በዋናነት በራሱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ነው ያሉት። እነዚህን ይዞ ምን አይነት ብልፅግና እንደሚመጣ ለማየት በጉጉት እየጠበቅን ነው።

ኢኮኖሚውን ሁሉም የሚያውቀው እና የሚኖረው ነውን አልዘረዝረውም። ሁሌም የሚመጣብኝ ጥያቄ ግን መንግስት አሁን ያለውን የኢኮኖሚው ሁኔታ ለመቀየር በተጨባጭ የሚያደርጋቸው ነገሮች በቂ ናቸው ወይ የሚል ነው። ኢኮኖሚስት አይደለሁምና መልስ የለኝም።

ከስትራቴጂክ እና ታክቲካል አጋርነት አንፃር መንግስት ጠላቱን ወዳጅ (ለምሳሌ ህወሐትን፣ አሜሪካኖቹን…ወዘተ) ለማድረግ የሄደበት ርቀት መልካም ቢሆንም፤ አጋሮቹን አጋር አድርጎ ለማቆየት እያደረገ ያለው ጥረት አናሳ መሆኑ ግን ግራ አጋቢ ነው። በተለይ በሁለቱ አመታት ጦርነት ወቅት አብረውት ለቆሙት ግለሰቦች እና ቡድኖች out of courtesy ስለ ሰላም ሂደቱ እና ዕቅዱ የውይይት መድረክ አለማዘጋጀቱ ነጥብ አስጥሎታል። ጠላትን ወዳጅ ማድረግ ማለት ወዳጅን for granted መውሰድ ማለት አይደለም። አንድ መንግስት ጠላቶቹን ቀንሶ አጋሮቹን ለማብዛት መስራት ትቶ እንደ ጎረምሳ ወዳጆቹን መቀያየር ካበዛ የመረጋጋት ዕድሉ አነስተኛ ነው።

ከሁሉ በላይ የብልፅግና መንግስት ከአምስት አመታት በኋላም በመሰረታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ (በህገ-መንግስት፣ በተቋማት ግንባታ፣ በዕርቀ-ሰላም፣ ወዘተ) mixed signal እያሳየ መቀጠሉ ተራ ብልጣብልጥነት መስሎበታል። ወይ አቋሙን በግልፅ አልገለፀ ወይ public debate and dialogue እንዲደረገ በቂ ርቀት አልሄደ፤ ሁሉንም በእንጥልጥል ትቶታል። ይህን ያሳልጣል የተባለው የምክክር ኮሚሽንም እንቅስቃሴው አመርቂ አይደለም።

እናም መንግስት ሆይ…አንዳንዶቻችን ይህንን ሁሉ እያወቅን ጠብሰቅ እና ሞቅ አድርገን 24/7 የማንተችህ ሃገራችን በቋፍ መሆኗን ስለምንረዳ፤ የፀጥታ መዋቅሩም ሃገሪቱን ለማረጋጋት አቅሙ የፈቀደውን ያህል እየሞከረ መሆኑን ስለምናውቅ ነው። እንጂማ በውስጥህ እንደተሰገሰጉት የፖለቲካ አመራሮች ደካማ አፈፃፀም ቢሆን ኖሮ ተቃውሞ ሲያንስህ ነው።

Exit mobile version