Site icon ETHIO12.COM

“ጩኸቱ ግን የማነው? መነሻውስ ከየት ነው?ፍላጎቱስ ምንድን ነው?”

“አማራጭ ሀሳብ የሚያቀርቡ ደፋር ሰወች ቢኖሩ እንኳ ይዋከባሉ፣ ይወገሩ ይገደሉ ይባላሉ፣ ዲቃሎች/half cast/ ይባላሉ፣ በባንዳነት ይወነጀላሉ፣ ከአካላዊ ሞታቸውም አስቀድሞ የስብዕና ግድያ ተደጋግሞ ይፈጸምባቸዋል ….” ይላሉ የአብን ሊቀመንበርና የኢኖቬሽን ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ። ሲቀጥሉም “ጩኸቱ ግን የማነው? መነሻውስ ከየት ነው?ፍላጎቱስ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

የዘረዘሩትን ፍረጃና ማስፈራራት ዘርዝረው “ይህን ሁሉ እንባላለን” የሚለው ፍርሃቻ መንገሱን ያወሳሉ። “ጩኸቱና ነውር የለሽነቱ ደግሞ የታጋይነት መገለጫ ተብሏል” ሲሉ ግርምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህን ካሉ በሁዋላ አቶ በለጠ ” ህዝባችን አማራጭ ሀሳቦችን እንዳያዳምጥ በአስጨናቂ echo-chamber ውስጥ ታፍኖ ያለ ህዝብ ይመስላል ሆኗልም” ሲሉ ድምዳሜያቸውን ያስቀምጣሉ። ሙሉ አሳባቸውን ከፌስ ቡክ ገጻቸው በመውሰድ ከስር እንዳለ አትመነዋል። ይህን በመጻፋቸው የዘነበባቸው ስድብ በአሳብ ልዕልና ለሚያምኑ አንባቢያን ስለማይመጥን አላካተትነውም።

Echo-chamber!

ብዙ ግዜ ህመሜን እምብዛም የማዳምጥ ሰው አይደለሁም። በዚህ ረገድ ሰፊ ክፍተት ያለብኝ ሰው አይነት ነኝ።
ዛሬ ግን አንድ ሰሞናዊ ህመሜን የግድ ለመታየት ወሰንኩና ጦር ሀይሎች ሆስፒታል ሄድኩኝ። ሀኪሙም ህመሜ ያለበትን አካባቢ በMRI ማሽን እንድታይ አዞልኝ ስለነበር ወደዚሁ ማሽን ውስጥ ገባሁ። ከማሽኑ ውስጥ በቆየሁባቸው 20-25 ደቂቃወች ውስጥ እስክወጣ ድረስ የምሰማው ድምጽ እጅግ ሰቅጣጭ፣ እያረፈ የሚጀምር፣ ከግራና ከቀኝ እያፈራረቀ የሚወጣ፣ የተለያየ አይነት ድምጸት ያለው በሀይል እየጦዘ የሚጨምር አስጨናቂ ድምጽ ነው። ሰውነቴ ላይ የትኩረት/የእይታ ነጥቡን ለመቀየር አንዱ አይነት የማሽኑ ድምጽ ሲቆምና ሌላኛው ሊጀምር ሲል ባለው አጭር የሽግግር ክፍተት ሌላ ደስ የሚል ሀገራዊ የክላሲካል ሙዚቃ ድምጽ ድንግት መሰማት ይጀምራል። ማሽኑ በሙሉ አቅሙ ሰቅጣጭ ድምጹን ማውጣት ሲጀምር ደግሞ የሙዚቃው ድምጽ ሙሉ በሙሉ በማሽኑ ድምጽ ስለሚዋጥ ለጆሮ መራቅ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ይዋጣል ይጠፋል። በማሽኑ ውስጥ የሚኖርህ ቆይታ እንዲያጥር ትወዳለህ ግን ደግሞ ህክምና ነው…

ይህ የecho-chamber ለወቅታዊ ሁኔታችን ሁነኛ ምሳሌ ሆኖ አገኘሁት። በተለይ ህዝባችን (የአማራ ክልል) ያለበትን ሰሞናዊ ሁኔታ ይህ ምሳሌ አውድ ይሰጠዋል። ህዝባችን አማራጭ ሀሳቦችን እንዳያዳምጥ በአስጨናቂ echo-chamber ውስጥ ታፍኖ ያለ ህዝብ ይመስላል ሆኗልም። አማራጭ ሀሳቦች እንደሌሉ ሁሉ ህዛባችን በማህበራዊ ሚዲያው ሰቅጣጭ ጩኸት ተውጧል። አማራጭ ሀሳብ የሚያቀርቡ ደፋር ሰወች ቢኖሩ እንኳ ይዋከባሉ፣ ይወገሩ ይገደሉ ይባላሉ፣ ዲቃሎች/half cast/ ይባላሉ፣ በባንዳነት ይወነጀላሉ፣ ከአካላዊ ሞታቸውም አስቀድሞ የስብዕና ግድያ ተደጋግሞ ይፈጸምባቸዋል …. ይህን ሁሉ እንባላለን ! ጩኸቱና ነውር የለሽነቱ ደግሞ የታጋይነት መገለጫ ተብሏል።

ህዝባችንን ከዚህ አይነት አፋኝ ድምጽ ነጻ ማውጣት አለብን!

ይገርማል። ሁሉ በእጁ ያለን ሕዝብ ሰከን ብሎ ምን እንዳለው እንኳን እንዳያገናዝብ በጩኸት አፍነውታል። ጩኸቱ ግን የማነው? መነሻውስ ከየት ነው?
ፍላጎቱስ ምንድን ነው? በርግጥ “አማራ” በሚለው ቃል ተሸፈነ እንጅ ምንነቱን አጥተነው አይደለም!

በጩኸት የተዋጡ አማራጭ ድምጾችንና ሀሳቦችን ለማጉላትና ለማዳመጥ፣ በርግጥ ህዝባችንን ከየትም የሚነሳ ጩኸቱ አፍኖ መተንፈሻ እንዳያሳጣው ለማድረግ፣ ብዥታ ለማጥራት፣ ሰላምና መረጋጋቱን ለመመለስ ህዝቡን ወደ መድረክ ማምጣትና ማወያየት ለነገ የማይባል አስቸኳይ ጉዳይ ነው ብለን እናምናለን! ስለሆነም አብን እንወያይ እናወያይ ሲል ይፋ ጥሪ ለክልሉና ለፌዴራሉ መንግስት አቅርቧል። ግን ደግሞ ጓደኛችን Gashaw Mersha ዛሬ እንደገለጸው ነው!

በተለይ በጦርነት የተጎዳው ህዝባችን ከምንም ነገር በላይ ሰላምና መረጋጋቱን ለመልሶ ግንባታ አበክሮ ይፈልገዋል። በ”አማራ” ስም የሚደረግን ሰርጎ ገብነትንም ይሁን አድፋጭ ንዑስ ፍላጎትን ለማስፈጸም ድርብርብ አጀንዳና ጩኸትን ለመሸከም የህዝባችን ፍላጎት አይደለም! ህዝባችን ገና ከጦርነት እየወጣ ነው። ሰላምና መረጋጋት ይፈልጋል፣ መልሶ ግንባታ ይፈልጋል።

ስለሆነም ህዝባችንን አናፍነው!
ቢያንስ እኛ ሰላሙን አንንፈገው!

ሰከን ማለት ጥሩ ነው!

Exit mobile version