Site icon ETHIO12.COM

“መንግስት ይሰረኝና ልጀግን፣ ታዋቂም ልሁን”ቀረጥ የማይከፍለበት የገቢ ምንጭ

አንድ መስማሚያ እውነት አለ። ኢትዮጵያ በሚዲያ ቫይረስ ተመታለች። የሚዲያ ቫይረስ ወሯታል። ሌላ መጠሪያ እስኪበጅለት “ሚዲያ” እንለዋለን እንጂ ኢትዮጵያ ላይ እየዘነበ ያለው የጥፋት አረር የተከለከል መሳሪያና ኬሚካል ከሚያደርሱት ጥፋት በላይ ነው። መንግስትን መተቸት፣ ማውገዝ፣ መቃወምና ለማረቅ መስራት እሰይ የሚያስኝ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ከቅርብና ከሩቅ የሚረጨው መንዝ መጨረሻው ምን እንዲሆን ተፈልጎ እንደሆነ ማሰብ ያዳግታል። ያማል። ይዘገንናል።

ይህን የሚዲያ ቫይረስ እንዲያከሽፉ በሚሊዮን የሚፈስባቸው ተከፋዮች ከሚታወቁት የመንግስት ሚዲያዎች ውጭ ማለቴ ነው፣ እንኳን መርዙን ሊያከሽፉ ራሳቸው ለሚያበላቸው መንግስት መርዙ ናቸው። አገርን ከሚዲያ የፕሮፓጋንዳ መጠበቅ ሳይሆን አላማቸው በቤተሰብና በጓደኛ ተቧድነው አገርን መጋጥ እንደሆነ በመረጃ መነጋገር ይቻላል። ከውስጣቸው ያሉ ጥቂት መልካሞችና ምንም ሳይከፈላቸው ለአገራቸው ህልውና ዘብ የቆሙ ቢኖሩም ትብትቡ እነዚህን ወገኖች የሚያርቅና የሚበላ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” የሚሰሩትን ማግለልና ማሸማቀቅ” መንገሱን በገለጹበት አግባብ ሲያዋቸው ትልቅ የሚመስሉ ሌቦች ከለየላቸው የጥፋት ሃይሎች ባልተናነሰ አገር እየጎዱ ነው። ከዋናዎች አፍራሾች ባለመታሰር ብቻ የሚለዩት ቂበኞች ሊተቿቸው የሚምክሩትን እንደሚያስፈራሩና በኔትዎርካቸው …. ወደ ዋናው ጉዳይ ላምራ።

ማንንም ዝቅ የማድረግ ወይም ከፍ የማድረግ ፍላጎት የለኝም። ይህ የግል ምልከታዬና አንዳንድ ለልቦናቸው የቀረቡ የሰጡትን ምስክረነት ያካተተ አሳብ ነው። ርዕሱን የመርጥኩት መታሰር የገቢ ምንጭ፣ የዝና መከናነቢያ፣ በምርጥ የውዳሴ ጋጋታ የሚያሰክር፣ በማያቋርጥ ጭብጨባ አናትን አሳብጦ አቅል የሚያሳጣና ” ሳያውቁ አዋቂ” የማድረግ ክብር የሚያላብስ መንደር ውስጥ የሚከት ሆኖ ስላገኘሁት ነው። ይህ ሁሉ ሲዳመር ኪሳ ማደለብ ነው ውጤቱ። ኢንዘስትመንቱ በኢትዮጵያ ባንዲራ የሚንቆጠቆጥ፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ የሚገነዝ ነገር ግን መደምደሚያ ” የትም ፍጪው …” ነው!!

እዚሁ ገጽ ላይ ኢትዮጵያን እያመሳት ያለው የ”ገፊና ጎታች ሤራ” (Pull and Push Conspiracy) ሲገለጥ የቀረበው አስገራሚ ድራማ እንዳለ ሆኖ፣ መንግስት እንዲያስራቸው የሚመኙ መነሻቸው ትህነግ ነው። ትህነግ “ቆፍጣና መንግስት ነኝ” ለማለት ኮሽ ባለበት ሁሉ እየተንደረደረ ሲቀፈድድ በአንድ ጊዜ “ኢትዮጵያ ዝነኛ ታሳሪዎችን አፈራች” ስም መዘርዘሩ ባያስፈልግም በታሪኳ አንድ ብቻ የሚጠቀስ ጽሁፍ የጻፈች እህት አስሮ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ አደረጋት። እሷም ታዋቂነቷን አምና ተቀብላ በልዕልት የአቀባበል ስነስርዓት ዳያስፖራውን አስደግድጋ ተንታኝ ሆነች። ክብር ለትህነግ/ ኢህአዴግ። የሚገርመው ይህች እህት “ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ አገር መምራት እችላለሁ” ስትል የኔታ መስፍን ታወሱኝ። አባታችንን ነብሳቸውን ይማርና ” ጭብጨባ አናት ያሳብጣል” ብለው ነበር። ይሰማል?

ሌላው 1987 ምርጫ ተከትሎ ሁሉም ሚዲያዎች ሲዘጉ ብቻውን እንዲሰራ የተፈቀደለት አውራ አምባ ሚዲያ ነበር። እርግጠኛ አይደለሁም ስሙ እንደሚመጥን ግን ” ጋዜጠኞች” የተባሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሲታሰሩ እሱም ታስሮ ነበር። “አምበሳው” በአቶ በረከት አማካይነት የተመለመሉ አማካሪዎቹና ባቀረቡት ጥቆማ መሰረት የሲፒጄ ተሸላሚ ሆኖ አሜሪካ ሲገባ ልክ እንደ ልጅቷ ዲያስፖራው በንብርክኩ ዳኸለት። ኪሱን አራግፎ ሸለመው። ማማ ላይ አውጥተው ሰቀሉት። ክንር፣ ዝና፣ ሙገሳ ከአበባና እጅ መንሻ ጋር አዘነቡለት። ከስካራቸው ሲነቁ አዲስ አበባ ሆኖ ምሲጢራቸውን በድምጽ ቅጂ ሳይቀር ሲረጭ አገኙት። ዝም ብሎ ነበር አሁን ትህነግ ያገኘውን ምህረት ተንተርሶ የዩቲዩብ አድማቂ ሆኗል። አበሻ ይሰማል። በሱፐር ቻት ኪሱን ያራግፋል።

ሰሞኑን ስዩም ተሾመ አምቆ እንደያዘው የገለጸው ጉዳይ የአንድ ተሸላሚ ” ጋዜጠኛ ግን …” ስም ጠቅሶ ” መዓዛ እኔም እንዳንተ በትሳረኩ አለችኝ” አለ። ስዩሜን በነጻ ውይይት ወቅት ቁጭ ብሎ የሚያዳምጠውና ለመሳቅ የሚከፍለው አጋሩ ማብራሪያ እንዲያክል ባያደርገውም፣ ስዩም ሃቁን አፍርጦታል። ስዩም ” ለምን” ብሎ ሲጠይቃት ነው ” ታዋቂ ዝነኛ እንደሆን” ያለችው። ብልጽግና ምስጋና ይግባውና ምኞቷን አሳክቶላት ተሸለመች። ልብ በሉ በመታሰሯ ብቻ አዋቂ፣ ተንታኝ፣ ተሸላሚ፣ ብር፣ …. ሁሉም ተግተልትለው ቤቷ ገቡ።

ሃብታሙ አያሌው የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሰብሳቢ፣ መልማይና አደረጅ ነበር። ታሰረ። እስር ቤት ሆኖ ልብ የሚሰብሩ ምስሎችን በተነ። ጉሉኮስ ተሰክቶለት የሚያሳይ ፎቶ እጅግ በስቃይ ላይ እንዳለ በሚያሳይ ምስል እያከታተለ በመለተፍ አየሩን ያዘው። በትክክል ምክንያቱ ባይታወቅም መቅመጫው መጎዳቱ በተደጋጋሚ ሲነገር፣ ሚዲያዎች ይህን ሲያስታውቁ፣ ኦባንግ ሜቶ መድሃኒት ሲልኩ አውቃለሁ። ሃብትሽ አሜሪካ በገባ በሳምንት ጊዜው ውስጥ የተጸነሰ ልጅ አገኘ። በከፍተኛ ደረጃ ስለት ገባለት። ጀግና የራበውና ጀግና የማያውቀው ዲያስፖራ እየረገደ ኪሱን አወለቀለት። ኢንዘስትመንቱ የሚጠይቀውን ሁሉ በማድረግ ኢሳትን ተሰናብቶ የአማራ ንቅናቄ መሪ ሆነ። ተከታዩና መንጋው ሲበዛ አናቱ አበጠ። አጥንትና ዘር እየቆጠረ የሰባት ልጆች አባት ላይ ዘመቻ አስከፈተ። አሁንም ሳያቋርጥ ትርምስና አመጽ የሚረጭ …. ኤርሚያስ የታጠፈበት ሰዓትና አሁን ያለው ግጥምጥም ልብ ለሚሉ ብዙ ይናገራል።

ዛሬ ጎበዜ ተያዘ ተባለ። ከጅቡቲ ተላልፎ ሲሰጥ ታየ። ጎበዜ ቆቦ ሆኖ በቅርቡ ለአንድ ዩቲዩብ በስልክ የጦርነት ትንተና ሲሰጥ ሰምቻለሁ። በተደጋጋሚ ጦርነት ወይም ግጭት ካለባቸው ቦታዎች ሆኖ በማህበራዊ ገጽና በዩቲዩብ መረጃ ሲያሰራጭ አውቀዋለሁ። ልክ ነው አይደለም የሚለውን ለሚፈርዱ ሰጥቼ ስለ አያያዙ ግራሞቴን ልግለጽ።

ጎበዜ በአውሮፕላን፣ ከዛ በላንድ ክሪዘር፣ በሚኒብሳ፣ በልዩ ሁኔታ ታጅቦ ወደ ማረፊያ ሲያመራ ኢቲቪ አሳይቷል። የፍርዱና የክሱን ጉዳይ አሁንም ለሚመለከታቸው ትቼ ” ይህን ያህልክ ማግነን ግን ለምን አስፈለገ?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ፈለኩ። በፌስ ቡክ ዜና ማስታወቁ አይበቃም? ጅቡቲ እንደሆነ የትህነግን ጀነራሎች ሳይቀር አሳልፋ ሰጥታለችና ዜናው እንዴት በዚህ ደረጃ ሊደምቅ እንደተፍለገ አልገባኝም። ይልቁኑ ጎበዜን መንጋው ” ጀግና” የሚለውን ስም በማከል ” ጀግና ጋዜጠኛ” እንዲሉት አድርጓል። እንደ እሱ በአውሮፕላን ታጅበው ወደ እስር ቤት ሲገቡ በኢቲቪ ለመታየት የሚጓጉ በርካቶች በምኞት እንዲተጉ ማነሳሻ ….

በቅርቡ የጀርመኑ የመረጃ ቲቪ ተዋናይ በአሜሪካ የተደረገላቸውን መስተንግዶ በራሳቸው ብዕር፣ በራሳቸው ቃላት፣ በራሳቸው ስሜት በተከናነቡት ክብር ውስጥ ሆነው ሲያሰራጩ የነበረውን ለማንበብ እድል ያገናቹህ አናት ሲያብጥ እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ምርጥ ማሳያ ይሆንላችኋል። የሚገርመው፣ (እነሱን አይገርማቸውም) መነጥርና ኮት እየቀያየሩ የሚያሰራጩት ግለ ዜናቸው ” ግፋ በለው እያሉት” የሚነዱት ሃይል እየሞተ ነው። የሚማግዱትና፣ እየማገዱት ዜና በሚያደርጉት ምስኪን የሚሰበስቡት ሃብት ሳያንስ፣ በዚሁ የዕርም ገንዘብ እየዝነጡ ሬሳ ለታቀፉ ወገኖች የቅንጦት ዜና ይልኩላቸዋል። አይ ዘመን?!

አቶ ግርማ የሺ ጥላ ” ዲቃላ ናቸው” ተብለው ከተገደሉ በሁዋላ እሳቸውን የሚገልጹ ንግግሮቻቸው በይፋ ተሰራጭተዋል። እሳቸው እንዳሉት አንድ በሞትና ህይወት መካከል ያለ ሰው እንዴት ራሱን ፎቶ አንስቶ ለማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች ይልካል? ሲሉ የገፊና ጎታች ፖለቲካን ብልት ነክተው ነበር። ይህ የገፊና ጎታች ፖለቲካን ለሚተውኑ እንጥላቸው ላይ የሚቆም፣ በገቢያቸው ላይ ቅርቃር የሚከት ምልከታ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

“… ማንም ይሙት የሚገደለው ሁሉ አማራ፣ ገዳዩ ደግሞ ሸኔ ብቻ እንዲባል ለምን ተፈለገ? የሸኔ የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ምንድነው? ሸኔን በፋይናንስ የሚደጉመው ማነው? ሸኔ ወለጋ ላይ በተለይ ያተኮረው ለምንድነው? ሸኔ ሲገድል የአማራ ተቆርቋሪዎች በምን ግንኙነትና ፍጥነት እየተቀበሉ ነው የፎቶና የቪዲዮ መረጃ የሚለቅቁት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በወለጋና ዙሪያው ስለ ተፈጸመውና እየተፈጸመ ስላለው መረጃ እንዲሰጡ ጎልጉል የጠየቃቸው የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሰጡት ምላሽ “እነሱ አብረው ላለመሥራታቸው ምን ማስረጃ አለ?” ብሎ መልሶ በመጠየቅ ነበር “ ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡት አሳቤን ስለሚያጠንክርልኝ።

የሚዲያ በተለይም የዩቲዩብ አብዮት ልክ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመከፋፈል ሁሉም የየግል መስኮት የመረጡበት ዋና ምክንያት ገቢ ነው። ገቢው ደግሞ በገፊና ጎታች ስልት ቅብብሎሽን ማዕከል ያደረገ ነው። አንዱ ለሌላው አጀንዳያ እያበጀ፣ በመመጋገብ አብረው የሚሰሩበት ይህ አውድ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አንዳችም በጎ ነገር አያይም። ማንም ይፈጽመው ማን፣ በጎ ነርን ለአፍታ አያቀርብም። የህዳሴ ግድብ ላይ ሆነው እንዳልተንደቀደቁ፣ አየር ሃይል ግቢ ገብተው ብቃቱን እንዳልንበለበሉ ዛሬ መርዶ አርጂነትን ብቻ መርጠዋል። በመንግስት ደጆች ሲርመጠመጡ የነበሩ ዛሬ “ጋዜጠኛ” በሚለው ካባ እልቂት እየወዘወዙ ወለው ያመሻሉ። ሲነኩ ” ጋዜጣኛ ተያዘ” እያሉ የከለላ ሪፖርት አቅራቢና ገቢ አሰባሳቢ ይሆናሉ። ዶክተር ዳንኤል የሚመሩት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ህግ ስለ ጋዜጠኛነት ምን የሚል ህግና የህግ ትርጓሜ እንዳለው ባይታወቅም አብሮ ሲያለቅስ ይሰማል። በነጋርችን ላይ የአቶ ግርማ የሺ ጥላ ህይወትና ሰባት ልጆቻቸው ጉዳት ለአቶ ዳንኤል ዜናም፣ መረጃም፣ ቁብም አይድለም። ለሰብአዊነት ሚዛንም አይበቃም። ገፊና ጎታች ይሏል ይህ ነወ።

ሚዲያ ክፉውን ከደጉ እያነጻጸረ በማቅርብ ቀና ሚና መጫወት ሲገባው፣ ውጭ ተቀምጠው ምድሪቱን የመርዶና የደም ምድር አድርገዋታል። መልካም ዜና ለእውቅና ስለማያበቃ፣ ለግነዘብ ማስገኚያ ስለማይሆን፣ ላይክና ሰብስክራይብ ስለማያስገኝ፣ ስለማያሳስር፣…. እልቂትን በመፍጠርና እልቂትን ዜና በማድረግ በገፊና ጎታች ስልት ኪስ ያወልቃሉ። ለዚሁ ገቢያቸው ሲሉ ድሆችን እሳት ውስጥ እየገፉ ልጆቻቸውን ያንቆጠቁጣሉ። ዜጎችን በተራ የዘረኛ መርዝ እያሰከሩ ያስጨርሳሉ፣ እነሱ በዚህ የእልቂት ዜና በሚየገኙት ገንዘብ ክራባት እየቀያየሩ ቢች ይዛናናሉ። “ተው እባካችሁ” በሚል የወላድ እንጀት ከማይመክሯቸው ሚስቶቻቸው ጋር ይመነሸነሻሉ። ከላይ እንደተባለው ስራው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነው። የዲያስፖራው ኪስ በቀላሉ የሚያውልቅበት፣ እንዲሁም በሳይበር ማጅራቱን የሚመታበት ነውና ይቀጥላል። ድሃውም ያልቃል!!

እናቶቻችን ” ማነሽ ባለሳምንት” ብለው ጽዋ እንደሚረካከቡት ሁሉ “መንግስት ይሰረኝና ልጀግን፣ ታዋቂም ልሁን” በሚል አዲስ ብቅ ለሚሉት ዝናና ገቢ ናፋቂዎች እንኳን “ቀረጥ የማይከፍለበት የገቢ ምንጭ” ኢንዘስትመንት መጣችሁ ከማለት ውጪ የሚባል ነገር የለም። ግን ዲያስፖራው እስከመቼ ነው የሚታለበው? መረጃ ቲቪና ባለቤቶቹስ ምን ይሆን ፍላጎታቸው? እመለስበታለሁ።

ሰብለ ወንጌል ሃይሉ ኦሎምፒያ


Exit mobile version