Site icon ETHIO12.COM

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

240 ሺህ ሚደርሱ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ይወስዳሉ

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ንቅናቄ ሊካሄድ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸው ትምህርት ቤቶችን በማሻሻል የመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የማስተካከል ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
በመሆኑም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ አገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 47 ሺህ አጠቃላይ ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው ያሉበትን ደረጃ በሚመለከት ቀደም ብሎ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶች የሚጠበቀውን ደረጃ የማያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ያሉት ሚኒስትሩ በተባበረ አቅም የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ማሻሻል ያስፈልጋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሟላት ሕብረተሰቡን በማስተባበር በተሰበሰው 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር 8 ሺህ 702 ትምህርት ቤቶች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል።

ዘንድሮ 240 ሺህ ሚደርሱ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ይወስዳሉ ፡- ትምህርት ሚኒስቴር

240 ሺህ ለሚደርሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በበይነ-መረብ የመውጫ ፈተና ለመሥጠት መዘጋጀቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት ÷ በ2015 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ኘሮግራም ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ለመሥጠት ብሉ -ኘሪንት ተዘጋጅቷል፡፡

የመውጫ ፈተና የክፍያ ተመን ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱንም ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት አብራርተዋል፡፡

የመውጫ ፈተና ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ መመሪያ እና የድርጊት መርሐ-ግብር ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡

በመውጫ ፈተና የሚካተቱ የትምህርት ዓይነቶች ተለይተው በቅድመ-ምረቃ በሚሰጡ በሁሉም የትምህርት መስኮች የፈተና ንድፍ ማሳያ መዘጋጀቱን ማስረዳታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

OBN

Exit mobile version