Site icon ETHIO12.COM

‘ድንገቴ የልብ ምጥ’ በሽታ ምንድነው?

ኸዲጃ አወል የአራት ልጆች እናት ናት። ከአራት ዓመት በፊት ሠርግ ተጠራች። አምራና ደምቃ ታደመች። ሙሽሮች እየተጠበቁ ሳለ ያልተጠበቀው ሆነ። በድግስ መሀል ድንገት ‘የልብ ምጥ’ ውስጥ ገባች። እጇ በላብ ተጠመቀ። ሰወራት። ተዝለፍልፋ የምትወድቅ ይመስላታል፤ ግን አትወድቅም። የምትሞት ይመስላታል፤ ግን አትሞትም። መሬት የከዳቻት መሰላት። ምን ጉድ ነው?

ሠርገኛው ታወከ። የአምቡላንስ ያለህ ተባለ። ሰዎች ተረባርበው ሆስፒታል ወሰዷት። ብዙዎች በልብ ድካም የምትሞት መስሏቸው ነበር። ይህ ሁሉ ሰቀቀን የቆየው ግን ለግማሽ ሰዓት ብቻ ነበር። ኸዲጃ የልብ ችግር አልነበራባትም፤ ጤነኛ ናት። ታዲያ ኸዲጃ ምንድነው ነበር የሆነችው?

‘ድንገቴ የልብ ምጥ’፣ የልብ ድካም አይደለም

ኸዲጃ ምን እንደሆነች ያወቀችው ሙሉ የልብ ምርመራ ከተደረገላት በኋላ ነበር። ልቧ አንዳችም እክል የለበትም። ሐኪሞች እንደገመቱት ከሆነ ኸዲጃ ላይ የተከሰተባት ‘ፓኒክ አታክ’ (Panic Attack) ነው። ምንድነው እሱ? 30 ዓመት በአእምሮ ሕክምና ዙርያ የሠሩት ጎምቱው የአእምሮ ስፔሻሊስት ዶ/ር ግንባሩ ገብረማሪያም ይህን እክል በአማርኛ “ወራሪ ጭንቀት እክል” የሚል አቻ ስም ይሰጡታል።

ለምንድነው ወራሪ ጭንቀት ያሉት ስንላቸው ችግሩ ድንገት እንደ አውሎ ንፋስ፣ እንደ ማዕበል ስለሚከሰት ነው ሲሉ ያስረዳሉ። እኛ ለዚህ ጽሑፍ ቅለት ስንል ግን “ድንገቴ የልብ ምጥ” እንለዋለን። “ብዙ ሰዎች ‘ፓኒክ አታክ’ የሚባል ነገር ስለማያውቁ በልብ ሕክምና ጊዜያቸውን ያጠፋሉ” ይላሉ ዶ/ር ግንባሩ። ይህም የሚሆነው የ‘ፓኒክ አታክ’ ምልክቶቹ ከልብ ሕመም ጋር በጣም ተቀራራቢ ስለሆኑ ነው።

የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ግንባሩ ገብረማሪያም

ድንገቴ የልብ ምጥ ምንድነው?

አንጋፋው የአእምሮ ጤና ስፔሻሊስት ሐኪም ለሦስት አሥርታት በሙያው ላይ ቆይተዋል። በእነዚህ ረዥም ዓመታት በዚህ ችግር እየተሰቃዩ ያሉ አያሌ ኢትዮጵያዊያንን አክመዋል።

ብዙዎቹ ታካሚዎቻቸው የሚያሳዩት ምልክት ይነስም ይብዛ ኸዲጃ በሠርግ ቤት ካጋጠማት ምልክት ጋር ተመሳሳይ ነው።

በማይቆጣጠሩት ምክንያት፣ ባልተገመተ ሁኔታ እና ባልጠበቁት ጊዜ የልብ መፍረክረክ፣ የእግር መብረክረክ፣ የሰውነት መራድ ይከሰታል።

ድንገተኛ ፍርሃት እና ጭንቅ፣ ጥብ ድንገት ደርሶ ይሰፍርብናል።

ያለምንም በቂ ምክንያት መሬት ትከዳለች። አንዳንዶች እንደማዞር ያደርጋቸዋል። አንዳንዶች ያቅለሸልሻቸዋል፤ መሬት እንደ እንዝርት ትሾርባቸዋለች።

ብቻ በሚደንቅ ቅጽበት ታማሚው በሰከንዶች ውስጥ በድንገት በፍርሃት ማዕበል ይናወጣል። በላብ ይጠመቃል፣ በስጋት ይንቀጠቀጣል። አሁን ጤና – አሁን ሞት አፋፍ ደርሶ መመለስ ምን ይሉታል?

“ማምለጫ በሌለው ወጥመድ ውስጥ እንደመግባት ያለ ነው” ይላሉ ዶ/ር ግንባሩ ስሜቱን ሲያስረዱ። እነዚህ ምልክቶች ተደማምረው ሲመጡ ታዲያ የልብ ምት ይጨምራል። ልብ ምት ሲጨምር ትንፋሽ ያጥራል። ትንፋሽ ሲያጥር በፍርሃት መንዘፍዘፍ ይከተላል።

“የሚገርምህ ይህ ሁሉ ነገር በድንገት ይመጣና ታማሚዎችን በድን ያደርጋቸዋል። በእኔ ተሞክሮ ቢበዛ ለ10 ደቂቃ ነው ፍርሃቱ የሚቆይባቸው” ይላሉ ዶ/ር ግንባሩ። ነገር ግን እንዲህ በጭንቀት የወረረ ‘የልብ ምጥ’ ከ10 ደቂቃ በኋላ ቢጠፋም የጭንቀቱ ድባብ ግን ለሚቀጥለው አንድ ሰዓት ያህል ሊጸና ይችላል።

ድጋሚ ይከሰታል የሚል ሌላ ጭንቅ

ዶ/ር ግንባሩ እንደሚሉት አንድ ጊዜ በዚህ በሽታ የተጠቃ ሰው መፍራት እና መጨነቅ ዕለታዊ ሕይወቱ ነው። የቤት ሥራው። ባለሙያዎች ይህን የ“ይሆናል ጭንቀት” ወይም ‘Anticipatory Anxiety’ ይሉታል። ዶ/ር ግንባሩ ደግሞ “ፍርሃትን የመፍራት አባዜ” ብለው ቅልብጭ ባለ ቋንቋ ያስቀምጡታል። ምን ማለት ነው? ፍርሃትን መፍራት ሁለት ሞትን የመሰለ ነገር ነው።

የመጀመሪያው ‘ወራሪ ጭንቀት’ ወይም ‘የልብ ምጥ’ ወይም ‘ፓኒክ አታክ’ ከፍተኛ የስሜት መሸበርን ያስከትላል። ታማሚዎች ነገሩ ከዚያ በኋላ መቼ በድጋሚ ሊከሰትብኝ ይችላል ብለው ጭንቅ ጥብብ ይላቸዋል። ሌላው ሲከሰት ደግሞ ሦስተኛውስ ብለው ይጨነቃሉ። የጭንቀት አዙሪት። ፍርሃትን የመፍራት እሽክርክሪት። ይህ ነው ፍርሃትን የመፍራት አባዜ የሚባለው።

በየስንት ጊዜው ይከሰታል ይችላል?

ኸዲጃ የመጀመሪያው የልብ ምጥ ከተከሰተ በኋላ ነገሩ የበለጠ እያስጨነቃት መጣ። ሰው ማግኘት ፈራች። ማኅበራዊ ሕይወቷ ተጎዳ። ሠርግ ጠላች።አሁን የሚያስፈራት ሌላ ነው። መኪና እየነዳች ‘ድንገቴ የልብ ምጥ’ ቢከሰትስ? ነገሩ ምልክት አይሰጥማ። ፋታም የለው። ልክ እንደ ነፍሰ ጡር ምጥ ነው። ጊዜው ሲደርስ በአንድ ጊዜ ይፋፋማል።

የነፍሰ ጡር ምጥ እንዲያውም ቀን ተቆጥሮ መዘጋጀትም አለው። ይህ የልብ ምጥ ግን እሱን ዕድል እንኳ አይሰጥም። በዚህ ፍርሃቴ የተነሳ “መኪና የግድ ካልሆነብኝ መንዳት ከናካቴው ትቻለሁ” ትላለች ኸዲጃ። ዶ/ር ግንባሩ ይህ ችግር በእኔ ተሞክሮ እንዳየሁት ደጋግሞ መከሰቱ ያለ ነው ይላሉ። “ድግግሞሽ የሕመሙ አንድ ባሕሪው ነው”

ብዙውን ጊዜ እንዲያውም መጀመሪያ በተከሰተ በሦስት ሳምንቱ ተመልሶ የመምጣት ዕድል አለው። የአእምሮ ስፔሻሊስቱ ትልቁ ችግር መቼ እና በምን ሁኔታ እንደሚከሰት ማንም አለማወቁ ነው ይላሉ። በዚህ የተነሳ የችግሩ ሰለባ አለመጨነቅ አይችልም። ወይ ማታ ተኝቶ በላብ ተዘፍቆ ትንፋሽ አጥሮት ሊሞት ሲል የሚነቃ ይኖራል።ውይ ደግሞ አስተማሪ በሰላም ክፍል ውስጥ ሲያስተምር ድንገት ‘የልብ ምጥ’ ሊፋፋምበት ይችላል።

እርኩስ መንፈስ ይሆን?

ኸዲጃ መጀመሪያ በሽታዋ ምንነቱ ሊገባት ባልቻለበት ወራት ሰዎችን ስታማክር “ሸይጣን ነው፤ ጂኒ ነው” ሲሏት ነበር። ሼኾች ጋር ጎራ እንድትል ተመክራም ነበር። ዶ/ር ግንባሩ ይህ በሽታ ከሚጥል በሽታ እኩል ሰዎች ከእርኩስ መንፈስ ጋር እንደሚያስተሳስሩት በ30 ዓመት የሥራ ዘመናቸው የታዘቡት ነው። “እንኳንስ እንዲህ ዓይነት የሚያሸብር በሽታ ይቅርና ሌላም በሽታ ሕዝባችን ከእርኩስ መንፈስ ጋር ያያይዛል እኮ፤ የታወቀ ነው” ይላሉ።

ዶ/ር እንደሚሉት ብዙ ታማሚዎች እርሳቸው ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት “ስህር ነው፤ መተት ነው” በሚል ብዙ የባሕል አዋቂ ጋር ተንከራተው የዛሉ ናቸው። ማንቀጥቀጥ፣ ልብ መምታት፣ ማዞር ዋንኛ ምልክቶቹ ስለሆኑ ደግሞ ሰዎች ከእርኩስ መንፈስ ጋር ሊያስተሳስሩት በቂ ምክንያት ያገኙ ይመስላቸዋል። ሌላው ደግሞ ለበሽታው ቀጥተኛ እና አፋጣኝ ፈውስ በዘመናዊ ሕክምና ስለማያገኙ ወደ ባሕል አዋቂዎች የመሄድ አዝማሚያ ይታያል።

ለምን ሲባሉ፣ “ሐኪም ቤት ሄጄም ያው የእንቅልፍ ኪኒን ነው የሰጡኝ፤ ለውጥ አላየሁበትም” ይላሉ። እርግጥ ነው የ‘ልብ ምጥ’ ለምን እንደሚከሰት የልብ የሚያደርስ ማብራሪያ ዘመናዊው ሕክምና የለውም። ስለዚህ ታማሚዎች ወደ ሌላ ቢያማትሩ አይደንቅም።

ሴቶች ላይ ለምን ይበረታል?

የልብ ምጥ ወይም ፓኒክ አታክ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ ይከሰታል። ለምን ለሚለው ሳይንስ በቂ ማብራሪያ የለውም። ብዙውን ጊዜ ‘በለጋ ጎልማሳነት’ ዕድሜ የመከሰት ዕድልም አለው። ለምን ግን ይህ በሽታ በሴቶች ላይ በረታ? የሚመጣውስ በምን ምክንያት ነው? ይህ ወደ ጥልቅ እና ውስብስብ ሳይንስ የሚወስደን ጥያቄ ነው።

ማኅበራዊ፣ ሥነ ፍጥረታዊ እና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዎች ይህ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱን ታማሚ በዚህ ምክንያት ነው ለዚህ በሽታ የተጋለጠው ማለት ከባድ ነው።

ይሁንና የአንዳንድ ሰዎች የኋላ ታሪክ አንዳች ነገር ሊጠቁም ይችላል። ለምሳሌ በልጅነቱ አስከፊ ሰቆቃ ያሳለፈ ሰው በጎልማሳነቱ ‘የልብ ምጥ’ ሊቀሰቅስበት የሚችልበት ዕድል አለው።

“አስከፊ ገጠመኞችን አእምሯችን አይጥልም፤ ሸሽጎ ያስቀምጠዋል እንጂ” ይላሉ ዶ/ር ግንባሩ። ለምሳሌ አንዲት የሚያክሟት ልጅ ነበረች። ዕድሜዋ ትንሽ እያለ ሊፍት ውስጥ የመደፈር ሙከራ ደርሶባት ነበር። አሁን ትልቅ ሰው ሆና ወደ ማንኛውም ሊፍት በተጠጋች ቁጥር ልቧ በከፍተኛ ሁኔታ ይመታል። ‘ወራሪ ጭንቀት’ ይከሰትባታል።

“ይቺን ልጅ አስታማሚዎቿ ሲያመጧት ግን እርኩስ መንፈስ ሊፍት ውስጥ ለከፋት ብለው ነው” ሲሉ ሕዝባችን እንዴት ነገሮችን ከመንፈስ ጋር እንደሚያገናኝ አስረድተውናል።

ሌሎች ታካሚዎቻቸውም “በቃ እብድ ልሆን ነው፤ እየጀማመረኝ ነው፤ ያንቀጠቅጠኛል፤ የሆነ መንፈስ ተጸናውቶኛል” በማለት በጭንቀት ይሰቃያሉ ሲሉም ያብራራሉ።

ፈውስ ይኖረው ይሆን?

ድንገቴ የልብ ምጥ በራሱ የአእምሮ በሽታ ቢሆንም ተደርቦ ደግሞ በማንም ላይ ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ አወሮፕላን መሳፈር የልብ ምጥ የሚያመጣባቸው ሰዎች አሉ።

ሕዝብ በተሰበሰበበት መድረክ ላይ መውጣት ራሳቸውን የሚያስታቸው አሉ።

ሰቀቀን እና ከፍተኛ ፍርሃት ያለበት ሁሉ የልብ ምጥ ሊከሰትበት ይችላል።

ነገር ግን “ድንገቴ የልብ ምጥ” ወይም ‘ፓኒክ አታክ’ በተከታታይነት የሚከሰትባቸው ሰዎች የአእምሮ ሐኪም ክትትል መሻታቸው የምርጫ ጉዳይ አይሆንም።

ሕክምናው ጥምር ሕክምና ይባላል። ከሥነ ልቦና ምክር ጋር መድኃኒቶችም ይኖራሉ።

በአንድ ጊዜ እንደ ሆድ ቁርጠት ቀጥ እንዲል ማድረግ አይቻልም። በረዥም ጊዜ ክትትል ለውጥ ማግኘት ይቻላል።

በምህጻሩ ሲቢዲ (Cognitive Behavioural Therapy) የሚባለው ነው፤ ለዚህ ችግር ውጤታማው ሕክምና።

የታማሚው የዓለም አረዳድ እየተቃኘ፣ ለበሽታው የነበረው የተንሸዋረረ አመለካከት እየተቃና እንዲሄድ የሚያደርግ ሕክምና ነው።

ድንገቴ የልብ ምጥ ከ360 በላይ ከሚቆጠሩ የአእምሮ እክሎች አንዱ ነው። ከጭንቀት ጋር የተያያዙት ደግሞ 17 ይሆናሉ።

የአእምሮ እክል ደግሞ በአንድ ጀንበር የሚፈወስ አይደለም።

“ታካሚዎች በትዕግስት ራሳቸው ላይ እየሠሩ ሕክምናን በጽናት መከታተል እንዳለባቸው ከወዲሁ ሊያውቁ ይገባል” ይላሉ ዶ/ር ግንባሩ።

“እኔ ታማሚዎችን የምመክረው አንድ ነገር ነው፤ ማኅበረሰቡ ብዙ መገለል ሊያደርስባቸው ይችላል። ቀላል አይደለም። ራሳቸውን ላይ ማተኮርን ይለማመዱ። የአእምሮ ሕክምና በችኮላ የሚሆን አይደለም።”

ከቢቢሲ አማርኛ የተወሰደ

Exit mobile version