“የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለን” እንዲል መፅሐፍ

ኢትዮጵያዊነትን በደብዳቤ የሰጠነው እኛ ነን ያሉ ሊያፈርሷት ሲነሱና የእነሱ የግብር ልጆች ደግሞ “ጦርነቱ እኛን አይመለከተንም”ብለው ተቀናጅተው አጀንዳ እየተመጋገቡ እስከደብረ ሲና ሲገሰግሱ ኦሮሞ አገር አፍራሽና አገር ገንጣይ ቢሆን ኖሮ ያኔ ሁሉም ነገር ተመቻችቶለት ሳለ ምኞታቸው እውን ሆኖ በታየ ነበር። በተግባር ሆኖ ያየነው ግን ኦሮሞ ስለኢትዮጵያ ሕልውና ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥና ሲያፈርስ ነው።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያን በኦሮሞ አሳበው ለማፍረስ ለቋመጡ ሃይሎች ኦሮሞ ምቹ ሆኖ አልተገኘም። እንዳሰቡትና እንደፈለጉት አልሆነላቸውም። ለኢትዮጵያ ሕልውና ሉዓላዊነትና ልዕልና ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ኦሮሞ ራሱ ለማፍረስ ተሽቀዳደመባቸው። ራሱ ወድቆ የኢትዮጵያ ሕልውና ይቀጥል ዘንድ፣ልክ እንደትናንቱ ኢትዮጵያ በጦርነት የገጠማትን ፈተና በድል አድራጊነት ትሻገር ዘንድ ቁርጠኛ ስለመሆኑ በወሬ ያይደለ በጦር ግንባሮች በነቂስ ዘምቶ አስመስክሯል።ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ትሻገር ዘንድ ካደረጉ ሌሎች ወንድሞቹ ጋር ስሙን በታሪክ አፅፏል።

በኢትዮጵያዊያን የተቀናጀ አኩሪ ተጋድሎና አሸናፊነት ጦርነቱ ስለተጠናቀቀ ለተሸናፊዎች ምህረት የወንድ በር ዕድል ስለተሰጠ ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ እንዳልነበረባት አያሳይም። ለተሸናፊዎች ምህረት ማድረግ የነበረ ያለና የሚቀጥል ነው።
መታወቅ ያለበት ለ27 ዓመት መንግስት መር በሆነ ደረጃ የተሰበከልን ወያኔያዊ ኦሮሞ የሆኑ በግለሰብ ደረጃ የሚታዩ የለም ማለት ግን አይደለም። ከንፍሮ ጥሬ የሆኑ በጥላቻ ፖለቲካ እንሰራለን የሚሉ የሚጮሁ በየትኛውም በኩል አለ። የሚታየው ብዙሃኑ ነው።በስልጣን ላይ የማድረግ አቅም ያለው ነው። ወደስልጣን የወጣው ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ ስለኢትዮጵያ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ዶ/ር አብይ በዚህ አያያዙ ከቀጠለ ኢትዮጵያዊነትን በፅኑ አለት ላይ ይገነባዋል። በየትኛውም ጠላት በቀላሉ የማትደፈር በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰላም ወጥተው የሚገቡባት በእኩልነት በፍትሃዊነት የሚኖሩባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆናለች።
በኦሮሞ አሳበው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ ለኦሮሞ ከፍተኛ ንቀትና ጥላቻ ያላቸው የጥፋት ሃይሎችና በኦሮሞ ስም በጥላቻ የሚንቀሳቀስ ወያኔያዊ ኦሮሞ ምኞት ደግሞ የሚፈልጉትን ርቀት ሳይሳመድ በቀላሉ የሚከስም ይሆናል።
አሁንም ደጋግመን ማሰብ የሚገባን ኦሮሞ መገንጠል የሚፈልግ አገር አፍራሽ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያዊነትን ለሌሎች ብሔሮች በደብዳቤ የሰጠነው እኛ ነን እስከማለት የደረሱ እብሪተኞች ደብረ ሲና ሲደርሱ ኢትዮጵያን አፍርሶ ኦሮሚያ የተባለች ነፃ ሐገር ወደመፍጠር እንዳይሸጋገር የሚያግደው ወይም እንቅፋት የሚሆነው አንዳችም ሃይል አለመኖሩን ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው የማይስተው ጉዳይ ነው። እየፈረሰች የነበረችን ኢትዮጵያ ወደማፍረስ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሲል ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ራሱን ሊፈርስ ወደጦር ግንባር ዘምቷል። ኢትዮጵያም በድል አድራጊነት እንድትሻገር ሆኗል።
በኢትዮጵያ ላይ የጠላቶች ምኞት ኢትዮጵያዊያን የድል አድራጊነት የከፍታ ጉዞው ሁሉም አይኑ እያየ ይቀጥላል!

ሰላም ለሐገራችን!
ከፍ በይ እናት ኢትዮጵያችን!

Tomas jajaw telegram page

Leave a Reply