Site icon ETHIO12.COM

ለሻምበል በላይነህ አዘንኩለት፤ በዘረኞች መዳፍ …

ዛሬም አልረፈደምና አዳነች አቤቤ ሻወርና ሽንት ቤት የሌለው ኮንዶሚኒየም በነፃ ሸልማ በአማራነቱ ልታዋርደው ነው ባላችሁበት አፋችሁ ለተወዳጁ ድምፃዊ ማረፊያ የሚሆን ለአማራነት ክብሩ የሚመጥን ቆንጆ ቤት አሜሪካ ላይ በመግዛት “ውርደቱን ” ተበቀሉ።

የድምፃዊ ሻምበል በላይነህ አድናቂ ነኝ። ታሪክህ ይፍረደኝ ፣ ዕውነቱ ይፍረደኝ ፣ ጊዜ ይፍረደኝ የምትለው ዘፈኑ ወያኔ ከሀገር ሲያበረኝ የስደት መተከዢያዬ ነበረች ።

በአካል ያገኘሁት አንድ ጊዜ ነው። በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጀርመን ውስጥ። እዚያ ቦታ በአካል ሳገኘው የተደሰትኩትን ያህል በሥፍራው የራሱን ሲዲዎች ለመሸጥ ወጪ ወራጁ ላይ አይኑ ሲያማትር ስላገኘሁት ተሸማቅቄ ነበር።

ሻምበል በላይነህን ያህል ከሁለት ዓሥርት ዐመታት በላይ ባካሄድነው ፀረ ወያኔ ትግል ከፊት ተሰልፎ በሙያው ከማንም በላይ ብርቱ አስተዋፅዖ ያደረገው ሻምበል በላይነህ የራሱን ሲዲ ቆሞ ሲሸጥ ሳየው አዘንኩ ። ጠጋ ብዬ አድናቆቴን ገለፅኩለት ። ሲዲው ጥሩ እየተሸጠ ነው ወይ ስለው በቅሬታ ማን የኛን ሲዲ ይገዛል ብለህ ነው የሚል ቅሬታ አሰማ። ( ያው የፍቅር የሞትኩልሽ ሞትኩልህ ዘፈን ካልሆነ ማን የትግል ዘፈን በሲዲ ይገዘል ማለቱ ነው) የሲዲው ዋጋ ውድ ስላልነበር የተወሰኑ ሲዲዎች ገዝቸ እዛው ለወዳጆቼ ስጦታ አበረከትኩት።

ሻምበል የሚዘፍናቸው አብዛኛው ዘፈኖች የትግል ዘፈኖች በመሆናቸው እንደሌሎች ዘፋኞች በሙያው ተጠቅሞ ብዙ ገንዘብ ያገኘ አይመስለኝም ። እኛም ለሀገር በጮኸው ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሰብሰብ ብለን ለአስተዋፅዖው የሚመጥን ምሰጋናና ድጋፍ አላደረግንለትም ።

በቅርቡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ለሻምበል በላይነህና ለጌታቸው ካሳ ኮንዶሚንየም ሸለማቸው ሲባል እንደገና ደስታና ሀዘን ተደባልቆ ተሰማኝ ። የተደሰትኩት ቤት በመሸለሙ ሲሆን ያዘንኩት ደግሞ ይሄን ያህል ዓመት አገልግሎ የራሱ ቤት መግዛት የሚችልበት አቅም አጥቶ የመንግሥት ድጋፍ ተቀባይ በመሆኑ ነበር።

ብዙም የዘፈንና የዘፋኝ አድናቂ አደለሁም ሻምበል በላይነህ ግን የትግላችን ድምፅ ነውና አክብሮቴ ነው እንዲያ እንዲሰማኝ ያደረገው።

ሰሞኑን የሱ ሥምና ምሥል በብዛት ፌስ ቡክ ላይ ሲዘዋወር ምን እንደተፈጠረ ሳጣራ የ360 ቲቪ ላይ ቀርቦ በተዋንያንነት በምናውቀው ሽመልስ አበራ ጆሮ ጠያቂነት ኢንተርቪው ሲያደርግ አደመጥኩት።

ጠያቂው ” እነ አዳነች አቤቤ ሻወርና ሽንት ቤት የሌለው ኮንዶሚኒየም የሸለሙህ በአማራነትህ ሊያዋርዱህ ፈልገው ነው” ሲለው ዛዲያሳ ይላል ሻምበል

ማለፊያ ወግ ነው ጃል

እኔ የማከብረው ሻምበል በላይነህ በዘር ውርዴ በተጠቁ የ360 ዘረኞች ዕጅ ገብቶ በተናገረው ነገር ለሱ የነበረኝ ክብር አልቀነሰም። ዛረም ለትላንት አስተዋፅዖው አመሰግናለሁ።

ሻምበል በላይነህን የዘር መርዝ ለመርጨት መሳሪያ ለማድረግ የሞከራችሁ ዕኩያን ሻምበል ከነ አዳነች ዕጅ ዕርዳታ እስከመቀበል ኑሮ ሲፈታተነው የት ነበራቹ?

ዛሬም አልረፈደምና አዳነች አቤቤ ሻወርና ሽንት ቤት የሌለው ኮንዶሚኒየም በነፃ ሸልማ በአማራነቱ ልታዋርደው ነው ባላችሁበት አፋችሁ ለተወዳጁ ድምፃዊ ማረፊያ የሚሆን ለአማራነት ክብሩ የሚመጥን ቆንጆ ቤት አሜሪካ ላይ በመግዛት “ውርደቱን ” ተበቀሉ።

ለሻምበል አዝናለሁ በዘረኞች አዝናለሁ

አብነት ጎሚስታ

Exit mobile version