“በአካል ሳይፈተን በአካል ሳይነካ
የማን ምንነቱ ግብሩ ሳይለካ
እርግጥ በተፈጥሮ በወል ስም ይጠራል
በቁም ነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል”።

፨ ለግጥም የተፈጠሩ ሰው ናቸው ሲሉ ይናገራሉ በስራቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ። እስከዛሬም ዘልቀው የምናደምጣቸው ተወዳጅ ሀገራዊ የዘፈን ግጥሞችን ጽፈዋል ። አራት የግጥም መጽሐፍቶችንም ለህትመት አብቅተዋል ፤ ከዚህም ውጪ ህዝባዊ መዝሙሮችንም በመድረስ ይታወቃሉ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ።

፨ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ከስነ-ጽሑፍ ባለሞያነታቸው ውጪም አርበኛም ጭምር ናቸው ። የቀድሞው የሆለታ ጦር አካዳሚ ምሩቅ እና በሱማሌ ጦርነት ጊዜ በታጠቅ ጦር ሰፈር ስልጠና ይወስድ የነበረውን የሚሊሻ ጦር በፓለቲካ ከማንቃት ጀምሮ እስከ ጦርነቱ ድረስ የተሳታፉ የቀድሞ የኢትዮጺያ ጦር ሰራዊት አባል የነበሩ እንዲሁም በጦርነቱም ጊዜ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው እንደሌሎች ውድ ኢትዮጲያዊያን ጓዶቻቸው ሁሉ ለሀገራቸው መስዋትነትን በመክፈል ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ከጥበብ ውጪ ህይወትን ለመክፈል በመወሰን ጭምር ያሳዩ ድንቅ ኢትዮጲያዊም ናቸው ። የሀገር ፍቅር ፣ ሰላም ፣ ህብረት ፣ አንድነት ፣ መተባበር ፣ ጀግንነት ፣ ሉዓላዊነት ፣ ነጻነት አጠቃላይ ኢትዮጲያና ኢትዮጲያዊነትን የሚያጎሉ አበይት ነጥቦች የግጥሞቻቸው ማዕከላዊ ማጠንጠኛዎች ናቸው ።

፨ ሰኔ 18,1969 ዓ.ም በአብዮት አደባባይ የሱማሌን ሀይል ለመመከት የኢትዮጲያ ሰራዊት ቃል ኪዳን ገብቶ ሽኝት ሲደረግለት በወቅቱ ዘማቹን የሚያበረታ ፣ ከራስ በላይ ሀገርን ማስቀደምን የሚሰብክ ፣ ለሀገር መሞት ክብር እንደሆነ ሰራዊቱን በወኔ እንዲሞላ ያስቻለውን “ይህ ነው ምኞቴ” የሚለውን መዝሙር የጻፉት ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ናቸው ። የዚህን መዝሙር ዜማ ተሾመ ሲሳይ ሰርቶታል ።
ይህ ነው ምኞቴ እኔ በህይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጲያ እናቴ ። ረጅሙን ጉዞ ጥንቱን አውቄ ተነስቻለው ትጥቄን አጥብቄ ፤ መብት ነጻነት እንዲሆን አቻ ተነስቻለው ለድል ዘመቻ ፤ ልሙት ልሰዋ ደስ ብሎኝ ስቄ ለሀገሬ ስል እኔ ወድቄ ...።

፨ “ሀገሬ ካፈራቻቸው ድንቅ ገጣሚያን መካከል ወዳጄ ክፍሌ አቦቸር (ሻለቃ)፣ በቀዳሚነት ከምጠቅሳቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ “ከጣትም ጣት ይበልጣል” እንዲሉ፣ በሀገር ጉዳይ ብዕሩ እያነባ፣ አንዳንዴም እየፈገገ፣ ሲያሻውም እየቆዘመ፣ በቃላት ትንታግ የስሜት ወላፈንን የማቀጣጠል ብርታት ካላቸው ብዕረኞች ውስጥ ገጣሚ ክፍሌ አቦቸርን የሚጋፋ ባለተሰጥዖ፣ በቀዳሚነት መጥቀሱ አይሆንልኝም ይላሉ ዳግላስ ጴጥሮስ የተባሉ ጸሐፊ ፡፡ ለጥቀውም…ሀገሩ ለእርሱ አልፋ ኦሜጋው ነች ፡፡ ሀገሩን ሲያሞግስ አቤት ሲያምርበት፡፡ ውበቷን አድምቆ ሲሞሽራት ደግሞ አቤት ስትዋብለት ፡፡ የሀገሩን ሀዘን ሀዘኔ ብሎ፣ ጉስቁልናዋን ብቻ ሳይሆን ተስፋዋንም ሲያመላክት አቤት ሲዋጣለት፡፡ አብነት ልጥቀስ ይላሉ ጸሐፊው፡-.
ከቀበሌሽ፣ ከአፈርሽ ላይ፣
ከግንድሽ ስር፣ እኔም በቀልኩ፣
ከጅረትሽ-ተራጭቼ፣ በአደግሽበት መንደር-አደኩ፣
በቋንቋሽ፣ አፌን ፈትቼ፣
“ሀ”
ባልሽበት፣ ፊደል-ቆጠርኩ፣
በሮጥሽበት፣ ሜዳ፣ ዳገት፣
እኔም ድኬ፣ ከዚያው ከረምኩ፡፡
ይሄን ይዤ፣ ተሸክሜ፣
እንዳ’መትሽ፣ ዓመት ጨረስኩ፣
በስክነትሽ – ሰከንኩና፣ የኋላዬን – ለፊት፣ አሰብኩ” ። … ይሉናል፡፡

፨ የሻለቃ ክፍሌ አቦቸርን የግጥም ስራዎች አያል የሀገራችን እውቅ ድምጻውያን ተጫውተዋል ። በተለይም የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፊቱ በእንባ እየታጠበ የዘፈነው ፣ በእናት ሀገር ፍቅር፤ በሚያውቀኝ በማውቀው ፣ ለአንድነቱ ለነፃነቱ፣ ውረድ በለው ግፋ በለው (በጦርነቱ ወቅት) ፣ እንኳንስ በሕይወቴ እያለሁ በቁሜ ፣ የወል ስም ሆነና (መግቢያው ላይ ያለው ግጥም) ፣ ለሀገሬ ስታገል ለድንበሯ፣ ከመራራው ትግል ከጀግኖች ደም ጀርባ ፣ እንዳትረሱ ፣ ወዘተ. የሚሉት ግጥሞች፣ የክፍሌ አቦቸር የምንግዜም አይረሴ ሥራዎች ናቸው ።
እንዲሁም
፨ ሂሩት በቀለ ፨ መልካሙ ተበጀ ፨ ጌታቸው አስፋው ፨ መሀሙድ አህመድ ፨ ውብሻው ስለሺ ፨ ነዋይ ደበበ ፨ አረጋኸኝ ወራሽ ፨ ሻምበል በላይነህ ፨ ወጋየው ደግነቱ የክፍሌ አቦቸርን ስራዎች ከተጫወቱት መካከል ናቸው ።

፨ በመጨረሻም ዳግላስ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያየት ላብቃ፦

፨ ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር ይህ ነው፣ ይህም ነበር ። በተለይም የዛሬዎቹ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በሚያባንኑንና በጎ ዕሴቶቻችን ሊዝጉ በወየቡበት በዚህ ወቅት፣እኒህን በመሳሰሉ አነቃቂ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ ሥራዬ ብለን፣ ብዕሮቻችን እንዲያምጡ ግድ ልንል ይገባል ባይ ነኝ፡፡ በደረቅ የፕሮፓጋንዳ ኮቾሮ ሳይሆን በጥበብና በፍቅር ቅመም በማዋዛት፡፡ ሀገርም ስለ ራሷ፣ ትውልድም ስለ ራሱ መስማት የሚገባቸውን ጉዳዮች ሁሉ በግልፅነት ከጥበብ ማዕድ የየድርሻቸውን እንዲያነሱ፣ እንደ ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር፣ ስሜታችንን ልንጨምቅ፣ ብዕራችንም ከሀገራዊ ዕውነታ እንዳይፋታ ማጠየቁ ግዴታ ሳይሆን ይቀራል? ይህ የቆምንበት ዘመን ለሀገር ክብር፣ ለወገን ኩራት፣ ለእናት ዓለም ደስታ፣ ለትውልድ እርካታ በቅንነትና በትጋት እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተግተን ከመሥራትና ከመደጋገፍ ይልቅ የሕይወታችን ሰባቱ ዋነኛ መርሆዎች፡- “ሀ ራስህን አድን!”፣ “ሁ ከራስ በላይ ነፋስ!”፣ “ሂ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ!”፣ “ሃ ሲሾም ያልበላ . . .!”፣ “ሄ ቀድሞ መገኘት”፣ “ህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል .. .!”፣ “ሆ ማን ምን ያመጣል!” የሚል የነፍስና የሥጋ ጩኸት ብቻ ከሆነ፣ ታሪክም፣ ሰንሰለቱ ሊቋረጥ የማይችለው የትውልድ ሰልፈኛም መታዘቡና መፋረዱ አይቀርም ሲሉ ያስጠነቅቁናል ።

፨ እውነት ነው! ዛሬም ልክ እንደ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር አይነት ያሉ ሀገር ወዳዶች በብዛት ያስፈልጉናል ፤ ትውልድን በጥበብ የሚያነቁ ፣ የሚያንጹ ፣ የሚገስጹ ፣ የሚያስተምሩ የጥበብ አርበኞችን ያብዛልን ።

፨ የሰሩትን እያከበርን ፣ አዲስ ሰሪዎችን እንፍጠር ።
ክብር ለጥበበኞቻችን ይሁን!

Book for all page

Leave a Reply