Site icon ETHIO12.COM

በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የፋይናንስ ሥርዓት ሥር ነቀል ለውጥ ጥያቄ

በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የመሳሰሉ ተቋማት ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ይሞግታሉ። የዕዳ ጫና፣ የከባቢ አየር ለውጥን ዳፋ ለመቋቋም የሚመደበው ገንዘብ ዋንኛ መከራከሪያ ናቸው። በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት መሪዎች የተቋማቱ አወቃቀር አካታች እና ፍትኃዊ እንዲሆን ይሻሉ።

ለሁለት ቀናት የተካሔደው የፓሪስ ጉባኤ ባለፈው አርብ ሲጠናቀቅ በውጤቱ የየተደሰተ ካለ ፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቺሌማ አንዱ መሆን አለባቸው። አገራቸው ዛምቢያ ሁለት ዓመታት ያዘገመ የዕዳ አከፋፈል ድርድሯን ያጠናቀቀችው ሒቺሌማ ራሳቸው በተገኙበት የፓሪስ ጉባኤ ላይ ነበር።

የሒቺሌማ መንግሥት ከአበዳሪዎቹ በደረሰው ሥምምነት መሠረት ቻይናን ጨምሮ ዛምቢያ ከተለያዩ አገራት የተበደረችውን 6.3 ቢሊዮን ዶላር የምትከፍልበት ጊዜ ከ20 ዓመታት በላይ እንዲሆን ተራዝሞላታል። ሥምምነቱ ለፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቺሌማ መንግሥት የሦስት ዓመታት እፎይታ ሰጥቷል።

ሥምምነቱ የፓሪሱ ጉባኤ “ጉባኤ አንድ ስኬት ነው” ያሉት ሒቺሌማ እንዲሳካ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን ቻይና፣ ፈረንሳይ እና ደቡብ አፍሪካ በሥም እየጠሩ አመስግነው “ዛምቢያ ከሞላ ጎደል መሞከሪያ ሆናለች። ከዚህ የተቀሰመው ልምድ በትክክል እንደ ትምህርት ተወስዶ ከዚህ ጉባኤ በኋላ በሚጀመሩ ሌሎች ሒደቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል ተስፋ አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

በጉባኤው መዝጊያ ከፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቺሌማ በቅርብ ርቀት ተቀምጠው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እንደ ዛምቢያ ሁሉ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ማድረግ የሚያስችለውን ድርድር ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ሒቼሊማን ለምስጋና ያበቃቸውን ዕድል ግን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አላገኙትም።

ባለፈው ዓመት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የከፈለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት አዝጋሚው ድርድር በመጪዎቹ ወራት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ ሰንቋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የፋይናንስ አማካሪያቸው ተክለወልድ አጥናፉን አስከትለው ወደ ፓሪስ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት የገጠሟቸውን አንገብጋቢ ችግሮች ዘርዝረዋል።

ዐቢይ ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል መንግሥታቸውን ሰንጎ የያዘው ዕዳ እና የዋጋ ንረት ይገኙበታል። “የግል እና የመንግሥት ዕዳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያሉት ዐቢይ “ዛሬ በአብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የመንግሥታት የራስ ምታት እንዴት ዕዳን እንቆጣጠራለን የሚለው እንጂ ስለ ልማት ማሰብ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ልማት ላይ ከማተኮር ይልቅ ጥረታችን ሁሉ ዕዳን መቆጣጠር ሆኗል። እነዚህን ሁሉ ቀውሶች መጋፈጥ አልበቃ ብሎ አስከፊ የከባቢ አየር ለውጥ ተጽዕኖ አጋጥሞናል” ያሉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ችግሮቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

ዐቢይ እና በፓሪስ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ጉባኤ የተሳተፉ የአፍሪካ መሪዎች ለገጠሟቸው ብርቱ ቀውሶች የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ማድረግ ብቻ እንደማይበቃ ያውቁታል። አብዛኞቹ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ዓለም ባንክን ጨምሮ ብድር እና እርዳታ የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት ተልዕኮ፣ አደረጃጀት እና አሠራር መቀየር አለበት የሚል ቆፍጠን ያለ አቋም አላቸው። ከምድር ወገብ በታች የሚገኙ አገራት ከዕዳ ባሻገር የከባቢ አየር ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጠቀም ያለ ገንዘብ ፍትኃዊ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡላቸው ይሻሉ።

ይኸን በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ለውጥ እንዲደረግ የሚወተውተውን እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ከሚመሩት መካከል የፓሪሱ ጉባኤ ተባባሪ አዘጋጅ የነበሩት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ አንዷ ናቸው። አገራቸው ባርባዶስ የከባቢ አየር ለውጥ ዳፋ በኃይል ከሚፈታተናቸው አንዷ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትሯ “የሚያስፈልገው የተጠናከረ የፖለቲካ ፍላጎት፤ ተሐድሶ ሳይሆን ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንዳለበት” ተናግረዋል።

“አገራትን በማይመለከት፣ ስሜታቸውን በማይረዳ፣ በማያዳምጣቸው፣ በጣም ሲከፋ ሕዝብን በማይመለከት፣ ስሜቱን በማይረዳ እና በማያዳምጥ ኢምፔሪያል ሥርዓት ጥላ ሥር ዓለም መቀጠል እንደማይችል የመንግሥታት እና የአገራት መሪዎች እንድንገነዘብ እጠይቃለሁ” ሲሉ ሞትሌይ በፓሪሱ ጉባኤ ለታደሙ አሳስበዋል።

የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ለውጥ ሊደረግ ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም ካላቸው መሪዎች መካከል ናቸው። ከፓሪሱ ጉባኤ ቀደም ብለው ግፊት ሲያደርጉ የቆዩት ሞትሌይ በተቋማቱ “ተሐድሶ ሳይሆን ሥር ነቀል ለውጥ” ያስፈልጋቸዋል ባይ ናቸው።

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ለውጥ እንዲደረግ የሚወተውተው ንቅናቄ በማደግ ላይ ባሉ አገራት መሪዎች ከፍ ብሎ ይሰማ እንጂ በበርካታ ባለሙያዎች ዘንድ ሰሚ አግኝቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዲያውም “ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ጊዜው ያለፈበት” እንደሆነ ይነቅፋሉ። ዋና ጸሐፊው በፓሪስ ደሐ አገሮች የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማትን ደጅ የሚያስጠናውን ሥርዓት “የማይሰራ እና ኢ-ፍትኃዊ” ብለውታል።

ይኸን ሐሳብ በዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የምትከፍለው የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሥርዓት “ሰባራ”፣ “የተጭበረበረ” እና “ኢ-ፍትኃዊ” እንደሆነ ይሞግታሉ። “ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ተቋማትን ማሻሻል አለብን” ያሉት የኬንያው ፕሬዝደንት “ስምንት እጥፍ ወለድ እየከፈልን ነው። ዕዳ ውስጥ የተዘፈቅንው በሥርዓቱ ወጥመድ እንጂ ቀድሞም ባለዕዳ ሆነን አይደለም። ከሌላው በተለየ ስምንት እጥፍ ወለድ የምትከፍል ከሆነ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ የመቅረት ዕድልህ ከሚቀጥለው ሰው ስምንት እጥፍ ይልቃል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሥርዓት የሚያብጠለጥሉት በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ችግሩን ነቅሶ ከማውጣት ባለፈ መፍትሔ የሚሉት ሐሳብ አላቸው። የኬንያው ዊሊያም ሩቶ የዕዳ መክፈያ ጊዜን ማራዘም እና እፎይታ መስጠት በፓሪሱ ጉባኤ ካቀረቧቸው አማራጮች አንዱ ነው።

በዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የምትከፍለው የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሥርዓት “ኢ-ፍትኃዊ” ሲሉ ተችተዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፖሳ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሥር ነቀል ለውጥ ካልተደረገ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማበጀት የወጠኑት ዕቅድ ይከሽፋል የሚል ሥጋት አላቸው።  ራማፖሳ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ቁልፍ ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን ያላቸው ኃላፊዎች አሿሿም እንዲቀየር ይፈልጋሉ። ለናጠጡት አገሮች የሚያደላው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት “ልዩ የመበደር መብት (SDR) አመዳደብ” ጭምር መቀየር እንዳለበት ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ አሁን ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ባለፉት አስርት ዓመታት “እጅግ ጠቃሚ” እና ውጤታማ” እንደነበር ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማትን የሚጨምረው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም አንገብጋቢ ችግሮቿን ለመፍታት ካላት ፍላጎት ጋር ሊጣጣም እንደሚገባ ይስማማሉ።

ይሁንና ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ተቋማትን የሚዘውሩት የናጠጡ አገሮች ለሥር ነቀል ለውጥ የሚደረገውን ግፊት ምን ያክል ይቀበላሉ የሚለው ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ነው። ቢያንስ በፓሪሱ ጉባኤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትን ያጎበጠው ዕዳ የተጠበቀውን ያክል ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል። የከባቢ አየር ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ለደሐ አገሮች ሊሰጥ ቃል የተገባው 100 ቢሊዮን ዶላር በመጨረሻ መሳካቱን ይፋ ያደረጉት ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ “ምንም እያደረግን አይደለም ማለት አንችልም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ለውጥ ፈላጊዎቹ ግን የብሪቶን ውድስ ሥምምነት ላይ አይናቸው ያረፈ ይመስላል። የብሪቲቶን ውድስ ሥምምነት ቀልጣፋ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለማበጀት፣ የመገበያያ ገንዘቦች ተመንን በውድድር ማዳከምን ለመከላከል እና ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማበረታታት ከ79 ዓመታት በፊት የተፈረመ ነው። የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ያቋቋመውም ይኸው ሥምምነት ነበር። ሥምምነቱ በ1970ዎቹ ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት ቢፈርስም ያቋቋማቸው ሁለቱ ተቋማት ግን አሁንም በዓለም ፖለቲካል ኤኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Exit mobile version