Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላም፣ እርቅና አብሮነት እንዲጎለብት ዜጎች የሚጠበቅባቸውን እንዲያወጡ ጥሪ አቀረበ

በመጪው አዲስ ዓመት ሰላም፣ እርቅና አብሮነት እንዲጎለብት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ብሔራዊ የጸሎት መርሐ ግብር በወዳጅነት አደባባይ አካሂዷል፡፡ የጸሎት መርሐ ግብሩ አዲሱን 2016 ዓመተ ምህረት በይቅርታና በእርቅ መቀበልን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጉባኤው የጳጉሜን ቀናትን የጸሎትና ንስሐ መርሐ ግብር በማውጣት ቤተ እምነቶች ለሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጸልዩ ማውጁ ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም የጸሎት መርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የተካሄደ ሲሆን፤ በስነ-ስርዓቱ ላይ የሃይማኖት አባቶችን፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የጸሎት መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ በጽናት የቆየችው በሕዝቧቿ መካከል ባለው ጠንካራ አንድነትና አብሮነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ አካላት ይህን የሕዝቦች ትስስር ለመሸርሸር የሃሰት ትርክቶች እንደሚያሰራጩም ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በመጪው አዲስ ዓመት ሰላም፣ እርቅና አብሮነት እንዲጎለብት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የኃይማኖት ተቋማት በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ በማፍራት ረገድ የጀመሩትን ሰራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት መፍታት አንደሚገባም እንዲሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም የእርቅና አብሮነት እንዲሆን የኃይማኖት አባቶች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡


Exit mobile version