Site icon ETHIO12.COM

“በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቤተክርስቲያንም እንከን የለሽ አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መሥራት ይኖርብናል” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱሥ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱሥ አቡነ ማቲያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሥ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት ጉባኤውን በጸሎት አስጀምረውታል።

በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቤተክርስቲያንም እንከን የለሽ አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል ቅዱስ ፓትርያርኩ፡፡

በጥቅምት ወር የሚደረገው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መካሄድ ጀምሯል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ በመክፈቻ መልእክታቸው ቤተክርስቲያን በእሾህ የተከበበች አበባ ናት የተሰጣትን የመንፈሥ ቅዱስ ኀይል በአግባቡ መጠቀም ይኖርባታል ብለዋል። ታዲያ ከመጽናት በቀር ከኛ ሌላ ምን ይጠበቃል? ብለዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳሉት እኛ ያለንበት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ዓለም እኛን ለመጥቀም ሳይኾን ለራሱ ሲል የሚቀራመተው አካባቢ ነው፡፡ ለዚያ ሲባል የደረሰብንም ጫና ምን ያህል እንደኾነ የምንስተው አይደለም ብለዋል:: እኛም አንድነታችንን እና ወንድማማችነታችንን አጽንተን መቆም ባለመቻላችን ለአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ ኾነናል ብለዋል ፡፡

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ሕዝብ ተጐዳ ማለት ቤተክርስቲያን ተጐዳች ማለት እንደኾነ አንርሳው ነዉ ያሉት ፤ ቤተክርስቲያን ማለት በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያን ነውና፡፡ ያለንበት አካባቢ ለልዩ ልዩ ጥቃት የተጋለጠ ኾኖ ሳለ ቤተክርስቲያናችን ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ብቻ ለብቻ ኾና በሃይማኖተ ክርስትና መዝለቋ እጅግ የሚያስደንቅ መኾኑን እናስታውስ ብለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የቀደምት አባቶቻችን ጽንዐ ሃይማኖትና ጥንካሬ ስለኾነ ሳናመሥግናቸው ብናልፍ ትልቅ ኃጢአት ይሆንብናል፤ እነሱን ማመሥገንም በቃላት ብቻ አይኾንም ብለዋል፡፡ እነሱ የሠሩትን በመጠበቅና በመድገም እንጂ ለዚህ ተልዕኮ ይህ ጉባኤ ኀላፊነት አለበት፤ ኀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል በማለት አሳስበዋል ፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክታቸውን ከኹኔታዎች በትክክል መገንዘብ እንደሚቻለው ቤተክርስቲያን ከሚተቻት ይልቅ የሚወዳት ይበልጣል። በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ያሉ ፈላጊዎቿ ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ የሚኾኑን በሀገር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፣ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሕዝቦች ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ግብረ መልስ ከዚህ ጉባኤ ይጠበቃል ብለዋል። ይህ በቀጣዮቹ ዓመታት በመሪ ዕቅዱ መሠረት በሥፋት የሚሠራ ሥራ ይኾናል በማለት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ቤተክርስቲያን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር ያሏት በመኾኗ የሀብት እጥረት ያጋጥማታል ተብሎ አይጠረጠርም ብለዋል በመልእክታቸው፡፡

ትልቁ ሀብት ሰው ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ሰውን በቅዱስ ወንጌል በሚገባ ከገነባች ፣ የሀብት አያያዟ በትክክልና በሃቅ ጠብቃ ለሚገባው የሃይማኖት ተልእኮ ለማዋል የሚያስችል አሠራር ከዘረጋች፣ ይህንንም በምእመናን አእምሮና ዓይን ከተረጋገጠ እንኳን ለገንዘቡ ለሕይወቱ የማይሳሳ ምእመን እንዳላት ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ታድያ ሀብት ማለት ይህ አይደለምን? አኹን መሥራት ያለብንስ ይህ ሀብት በትክክል መጠበቁ ላይ አይደለምን? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህም በቀጣዩ ዓመት በሥፋት የሚሠራበት ይኾናል ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በቀጣይ መሠራት አለባቸው ያሏቸው የዕቅበተ ንዋይ፣ የዕቅበተ ሃይማኖት፣ የሥልጠናና ትምህርት፣ የገዳማትና ቱሪዝም፣ የምርትና የደን ሀብት፣ የፋይናንሱ ሴክተርና የስብከተ ወንጌሉ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው የአመራርና የአሠራር ጥበብና ሥልት እየታገዝን፣ ሕዝባችንንም ከጎናችን እያሠለፍን የምንሠራበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ሰላምና የሀገር አንድነት ላይ ባተኮረው መልዕክታቸው እንዳሥገነዘቡት ለተጀመሩና ወደፊት ለሚጀመሩ የመልካም አሥተዳደርና የልማት ሥራዎች ዋስትና እንደሚያሥፈልጋቸው እሙን ነው ብለዋል፡፡ የሥራዎቻችን ዋሥትናም በሀገርና በቤተክርስቲያን ፍጹም የኾነ ሰላምና አንድነት መኖር ነው ብለዋል፡፡

ሰላምና አንድነት መልሶ ለማምጣት የቤተክርስቲያን ኀይል የአንበሣውን ድርሻ እንደሚወስድ ሳይታለም የተፈታ ነው ብለዋል፡፡ ኾኖም የቤተክርስቲያን የሰላም ጉዞ ከማንኛውም ወገንተኝነት በጸዳ ፣ ማእከሉና ዓላማው የሀገርና የቤተክርስቲያንን አንድነት ብቻ መሠረት ያደረገ መኾን ይገባዋል ብለዋል::

ከዚህ አንጻር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሠፍን፣ በቤተክርስቲያናችንም እንከን የለሽ አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መሥራት ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡ አኩርፈው የተለዩትን በጠባይ ወደ እኛ እናምጣቸው ፤ እኛም ኩርፊያን ከሚያስከትል ድርጊት እንራቅ ፤ በአንድነት፣ በእኩልነትና በጋራ ኾነን ታላቋን ቤተክርስቲያን እንሰብሰብ፣ እናገልግል፣ እንምራ፣ እንጠብቅ ብለዋል ቅዱሥነታቸው በንግግራቸው፡

የዕለት ተዕለት ሥራችን የቤተክርስቲያንን ጭንቀት የሚያቃልል ይሁን ፤ ይህ ከኾነ ቤተክርስቲያንን ያለ ምንም ጥርጥር በዕድገት ጐዳና ወደ ፊት እናሻግራለን ብለዋል።

የታላቋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መርምሮ ገምግሞና አጥንቶ ችግር ፈቺ ውሳኔን የመሥጠት ኀላፊነት ያለበት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በይፋ መጀመሩንም አብሥረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ታድመውበታል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ – (አሚኮ)


Exit mobile version