Site icon ETHIO12.COM

በጎብኝዎች የተወደዱ ምርጥ ሀገራት

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም መረጃዎችን ይፋ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ቱሪዝም ላይ ወቅታዊ ትንታኔዎችን ይሰጣል፡፡ በዓመት አራት ጊዜ የሚታተም የቱሪስት ፍሰት መረጃን ያወጣል፡፡ ተቋሙ በያዝነው የፈረንጆች 2023፤ ከጥር እስከ ሐምሌ ያለውን የሀገራትን የቱሪዝም ፍሰት እ.ኤ.አ.ከ 2019 ጋር በማነጻጸር ይፋ አድርጓል፡፡ ቀዳሚዎቹ ሀገራት የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ኳታር

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ኳታር በርካታ ጎብኝዎችን በመሳብ 1ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ሃገሪቱ ቱሪስቶችን በመሳብ 95 በመቶ እድገት ማስመዝገቧንም ይፋ አድርጓል፡፡ ሀገሪቱ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ በጣም ተመራጭ የቱሪስት እና የንግድ መዳረሻ ስትሆን፤ የበረሃ ባሕረ ገብ መሬትንም የታደለች ሀገር ነች፡፡

2. ሳዑዲ አረቢያ

ተቋሙ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሰቀመጣት ሳዑዲ አረቢያን ነው፡፡ ሃገሪቱ 58 በመቶ የቱሪስት ፍሰት ዕድገት ያስመዘገበች ስትሆን፤ ሀገሪቱ በሃይማኖታዊ እና በታሪካዊ ቅርሶቿ በስፋት የምትታወቅ ሀገር ነች፡፡

3. አልባንያ

አልባንያ እ.አ.አ ከ2019 አንጻር 56 በመቶ የቱሪስት ፍሰት ዕድገት በማስመዝገብ ከ1 እስከ 3 ዝርዝር ውስጥ ተካታለች፡፡ በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ የምትገኛው አልባንያ ጥንታዊ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን የያዘች ሀገር ናት፡፡

4 ኤልሳቫዶር

ኤልሳቫዶር አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሀገር ናት፡፡ የቱሪስት ፍሰት ዕድገቷም 32 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በመካከለኛው አሜሪካ የምትገኛው ኤልሳቫዶር “የእሳተ ገሞራ ምድር” በመባልም ትታወቃለች። በየጊዜው የሚከሰተውን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ትዕይንት ለመታደም በርካታ ቱሪስቶች ወደ ሃገሪቱ ያቀናሉ፡፡

5 አንዶራ

ከዓለም በ5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው አንዶራ በቱሪዝም ዘርፉ 31 በመቶ እድገት አስመዝግባለች፡፡ አንዶራ በፒሬኒስ ተራሮች ተከባ በፈረንሳይ እና በስፔን መካከል የምትገኝ ትንሽ ራስ ገዝ አስተዳደር ስትሆን፤ ብዙ የበረዶ መንሸራተቻ ቦታዎች የሚገኙባትም ነች፡

6 አርሜንያ

ከዓለም ምርጥ የቱዝም መዳረሻዎች ውስጥ አንዷ የሆነችው አርሜንያ 30 በመቶ የቱሪስት ፍሰት እድገት አስመዝግባለች፡፡ አገሪቷ በተራራማ መልክዓ ምድሮቿ ትታወቃለች። ሀገሪቱ በዓለም ላይ እጅግ ጥንታዊ የሆኑትን ጨምሮ ከ4ሺህ በላይ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አሏት፡፡ በዚህ አማካኝነትም “የአብያተ ክርስቲያናት ምድር” ተብላም ትጠራለች።

7. ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2019 አንጻር በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በመጀመሪያዎቹ 7 ወራት የዓለም ቱሪዝምን በመሳብ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የዓለም አቀፉ ቱሪዝም ተቋም አስታውቋል፡፡ በተቋሙ መረጃ መሠረት ሀገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 2019 አንጻር 28 በመቶ የቱሪዝም ፍሰት ዕድገት በማስመዝገብ ከዓለም 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶች የሚገኙባት ሀገር ናት፡፡

በቅርቡም የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር በዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት የእውቅና ሽልማት ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የሌጲስ መንደር አስደናቂ መልክዓ ምድሮችን፣ ፏፏቴ፣ አእዋፋት እና የተለያዩ የዱር እንስሳት በውስጡ የያዘ እና በጎብኝዎች ዘንድም ተመራጭ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በዓለም ድንቅ መንደርነት የጮቄ ተራራ እና የወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መንደርን ያስመዘገበች ሲሆን፤ የሌጲስ መንደር ሶስተኛ ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

ከታሪካዊ ቅርሶችና ሃብቶች በተጨማሪም እንደ ወንጪ፣ ኮይሻ ፣ጎርጎራ ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚሰሩ ፓርኮች ለኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት እድገት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ይፋ ባደረገው ዝርዝር ውስጥ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ብቻ ተካተዋል፡፡ አፍሪካዊቷ ሃገር ታንዛንያ በቱሪስት ፍሰት እድገት 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አፍሪካ እንደ አህጉር በዚህ የሰባት ወር ጊዜ ውስጥ 92 በመቶው የቱሪስት ፍሰት እድገት አሳይቷል፡፡

በጊዜው አማረ Addis zena


Exit mobile version