Site icon ETHIO12.COM

የፕሮስቴት እጢ ምልክቶችና ህክምናው

ፕሮስቴት እጢ በወንዶች ፊኛ በታች የሚገኝ ተፈጥሯዊ የሰውነት አካል ነው ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ዩሮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር መሀመድ አብዱልሀዚዝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷የፕሮስቴት እጢ ዋነኛ ተግባር የዘር ፈሳሽ በማመንጨት ወደ ፊት ለፊት እንዲወጣ በማገዝ ለመራቢያነት ማገልገል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የበሽታው መንስኤ ብለን የምንጠራቸው ምክንያቶች አብዛኛዎቹ ተፈጥሯዊ መሆናቸውንም ነው በቆይታቸው የገለጹት፡፡

እጢው በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ እንደመሆኑ መንስኤው በጾታ ወንድ መሆን ሲሆን÷ እጢው ሊያድግ የሚችልባቸው ጊዚያቶችም አንደኛው ምክንያት አንድ ወንድ ለአቅመ አዳም ሲደርስ መሆኑን እና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እድሜው በ50ቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲገባ ነው ይላሉ፡፡

ሌላኛው መንስኤ ቤተሰብ ውስጥ በፕሮስቴት እጢ ምክንያት የጤና ችግር ያጋጠመው የቤተሰብ አባል ሲኖርም በዘር ምክንያት የመጋለጥ እድል እንደሚኖረውም ያነሳሉ፡፡

በተጨማሪም÷ አንድ በጾታ ወንድ የሆነ ሰው የስኳር ፣የደም ግፊት፣የኮሌስትሮል መብዛትና የክብደት ከመጠን በላይ መጨመር ካለ ተጋላጭነቱ ሊሰፋ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የእጢው እድገት ችግር ላያመጣ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጤና ችግር በሚፈጥር መልኩ የሚያስቸግርበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ይጠቅሳሉ፡፡

የጤና ችግር የሚፈጠርበት ምክንያት የእጢው መገኛ የሽንት ፊኛ አንገት ላይ በመሆኑ የእጢው ማደግ ቀጥታ ከመሽናት ችግር ጋር ሊያያዝ ስለሚችል እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

የፕሮስቴት እጢ ምክንያት የሚመጣው የጤና ችግር የሚከተሉትን ምልክቶች እንዳሉት የሚገልጹት ዶ/ር መሀመድ ሽንት ለማጠራቀም መቸገር (ቶሎ ቶሎ መሽናት)፣ሲሸኑ የማቃጠል ስሜት መሰማት፣ለመሽናት መቸገር ፣ሽንት በደምብ ያለመፍሰስ፣ የሽንት መቆራረጥ የመሳሰሉት በዋነኝነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡

የፕሮስቴት እጢ ቀላልና ከባድ ህመሞች የሚያስከትል ሲሆን÷ እንደ ችግሩ ሁኔታ መፍትሔውም የሚለያይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቀለል ያሉ የፕሮስቴት እጢ ችግሮች በምክርና በክትትል ሊሻሻሉ የሚችሉ እንደሆኑ የሚገልጹት ዶ/ር መሀመድ ከበድ ያሉት ደግሞ የህክምና እገዛ የሚፈልጉ ማለትም በመድሃኒትና በቀዶ ጥገና ጭምር የሚታገዙ እንደሆኑ ያነሳሉ፡፡

እጢው ከበድ ያለ ህመም ወደ ማስከተል ደረጃ ደርሶ የህክምና ክትትል ካልተደረገ ግን እንደ የኩላሊት ስራ ማቆምና ወደ ሌሎች ውስብስብ ችግሮች ሊያመራ ስለሚችል ከላይ የተጠቀሱትን የህመሙ ምልክቶች የሚያሳይና በተለይ ደግሞ እድሜው በ50ቹ የእድሜ ደረጃ ላይ ያለ ወንድ የጤና ባለሙያ ሊያየው እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

FBC


Exit mobile version