የ34 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ከአውሮፕላኑ ሲወርድ እግሮቹ ቆስለው መራመድም ሆነ መቆም አቅተውታል። ብርክ ይዞት ይንገዳገዳል፡፡ ይህ ሰው የተሻለ ህይወት ይኖረናል ብለው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ በባህር ላይ ተጉዘው ለእንግልት ከተዳረጉ ዜጎች መካከል አንዱ ነው፡፡
አብዱረሃማን ከማል ይባላል፡፡ ምስራቅ ሀረርጌ ባበሌ የትውልድ ሥፍራው ናት፡፡ በሱማሊያና በየመን አድርገን ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ ለመግባት ሲሞክር አሲር በሚባል የሳኡዲ ቦርደር በኩል ዛራን አልጀኑ በምትባል ከተማ ለእስር ተዳርጓል፡፡
አብዱረሃማንና ጓደኞቹ በባህር አቋርጠው ወደ ሳኡዲ ሲጓዙ ነበር የተያዙት። በእስር ቤቱ ያለ ብርድ ልብስና ያለ ሕክምና፤ ንጽህናቸውም ሳይጠበቅላቸው ከፍተኛ በሆነ የምግብ እጥረት፤ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ከሁለት ጉርሻ የማታልፍ ቂጣ እየበሉ በስቃይና በእንግልት 14 ወራትን ማሳለፋቸውን ይናገራል፡፡
የሳኡዲው የስደት ጉዞ ስቃይና መከራ የበዛበት መሆኑን የሚናገረው አብዱረሃማን፤ በእስር ቤት እርስ በእርስ የሚጣሉ እንዳሉ፤ ዝርፊያም መኖሩን፤ ሰብዓዊ መብት የሚባል ነገር ይናፍቃቸው እንደነበር ይገልጻል፡፡ “የዓለም ስቃይ ያለበት ቦታ ነው” ይላል የነበረበትን የእስር ቤት ህይወት “ከገሀነም እሳት” ጋር እያመሳሰለ፡፡
አብዱረሃማን እንደሚለው፤ የባህር ላይ ወንበዴዎች ስደተኞችን በጫካ ውስጥ ስቃይ ያደርሱባቸዋል፡፡
ይህም በርካቶችን ለስነልቦና ጉዳት ዳርጓል፡፡ በሀገሪቷ ከፍተኛ ሙቀት አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለቅጣት ሲባል ከመጠን ያለፈ ቅዝቃዜ ውስጥ ያስቀምጧቸዋል፡፡ ሴቶች የንጽሕና አገልግሎት አያገኙም፡፡ ልብስ ለመቀየር ይቸገራሉ፡፡ ጉልበቱ ሻል ያለው መሳሪያ ይገዛና ከወንበዴዎች ጋር ተሻርኮ ጫካ ይገባል፡፡ ዜጎችን ያገቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ በየዕለቱ ከሚደረገው ቅሚያ ባሻገር የሚፈጸም ድርጊት ነው ይላል፡፡
“በባህር ላይ ወንበዴዎች የተቀጠቀጥኩበት ዱላ ከአንድ ወር በላይ አሳምሞኛል” የሚለው አብዱረሃማን፤ በታሰረበት ወቅት ጀርባው ላይ ቃጠሎ እንደደረሰበት ይናገራል፡፡ አሁን ላይ እግሮቹ እንደ ልቡ እንደማይራመዱለትና በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት እስከ አዕምሮ ጤና ምርመራ እንደሚያስፈልገው ይገልጻል፡፡
“ልክ እንደ አካል ጤና ጉዳት ብዙዎች የአዕምሮ ጤና እክል ገጥሟቸዋል፡፡ ሥራ ከመፈለጉና እንጀራ ከማግኘቱ ይልቅ ጤንነት ይቀድማል፡፡ ሁሉም ነገር የሚገኘው ጤና ሲኖር ነው” በማለት፤ ለተመላሽ ስደተኞች ቅድሚያ ሕክምና እንዲሰጣቸው ይጠይቃል፡፡
“በዚህ መንገድ ለስድስት ጊዜ ያህል ተመላልሻለሁ፡፡ ከሰርኩ እንጂ የተጠቀምኩት ነገር የለም” ሲል አብዱረሃማን ይናገራል፡፡ ዜጎችን ባልተገባ መንገድ የሚያመላልሱ አካላት የባንክ ቁጥራቸው ጭምር ስለሚታወቅ መንግሥት ይህንን አፋላልጎ ደላሎች ላይ ክትትል ማድረግ እንዳለበትም ይመክራል፡፡
አብዱረሃማን እንደሚገልጸው፤ ወጣቱ ወደ ስደት ሄዶ የተሻለ ሥራ እንደሚሰራ ተነግሮት እየተታለለ ለአንድ ጊዜ ጉዞ እስከ 150 ሺህ ብር ለደላላ እያወጣ ነው፡፡ በዚህ ሀገር ውስጥ መስራት ሲቻል የሀገር ሀብትና የወጣት ጉልበት እየባከነ ነው፡፡
ፈጣሪ ለሀገሩ ስላበቀው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው፤ መንግሥት በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች መድረሱ ትልቅ ሥራ መሆኑንና ዳግም ከዚህ ሀገር ለመውጣት እንደማያስብ ይናገራል።
“ከሚደርሰው ስቃይና እንግልት አኳያ እንጀራ ፍለጋ ሕጋዊነትን የተከተለ መሆን እንዳለበት እመክራለሁ፡፡ ማህበራዊ ኑሮ እንዲጎብትም መላው ሕዝብ ትብብር ማድረግ አለበት፡፡ ሕገ ወጥ ደላሎች የሂሳብ እንቅስቃሴያቸውን ተከትሎ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ይላል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት መካሻ አረጋ፤ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈትኖ ውጤት አልመጣ ሲለው ስደትን እንደመረጠ ይናገራል፡፡ ከ200 ሺህ ብር በላይ ለሕገ ወጥ ደላላ በመክፈል በባህር ላይ አድርጎ ሳኡዲ ገብቶ ለመሥራት ቢሞክርም ሳይሆንለት ቀረ፡፡ እሱም እንደ ሌሎች ስደተኞች የእንግልትን ጽዋ ሳይጎነጭ አልቀረም፡፡ በሳኡዲ እስር ቤት ከዓመት በላይ ታስሯል፡፡
ለዚህ ሁኔታ ያበቃው የጓደኛ ግፊት መሆኑን የሚናገረው መካሻ፤ “የስደትን ጉዳት ባለማየት የወሰነው ውሳኔ ትልቅ ዋጋን እንዳስከፈለው ይጠቅሳል፡፡ “በስደት የገጠመን ከሚወራው ነገር ፍጹም የራቀ ነው፡፡ ስቃይና እንግልት የበዛበት ነው፡፡ ከብዙ ወንበዴዎች ሽሽት ብዙ መከራ ደርሶብኛል፡፡ ድንበር ላይ የሞቱ ብዙዎችን አይቻለሁ፡፡ አብሬያቸው ከሄድኩት ዘጠና ወጣቶች ነን የተረፈነው በጣም ጥቂቶች ነን ይላል፡፡
“ስደት አስከፊ ነው ለጠላቴም አልመክርም፤ ለችግሩ የሚዳርገው ደግሞ አለማስተዋል ነው”በማለት፤ ወጣቶች ከስደት ይልቅ በሀገራቸው ተፍጨርጭረው ሰርተው መለወጥ እንዳለባቸው ይመክራል፡፡
“በእሬሳ ላይ እየተራመድን ነው የምንሄደው፡፡ እስር ቤቱም ቢሆን ብዙ በሰቀቀን የተሞላ ነው፡፡ በአንድ ልብስ ዓመት ሙሉ እንቆያለን፡፡ በሽታ ይዞን የሚለቀን ታክምን ሳይሆን በራሱ ጊዜ ነው” ይላል የስደትን አስከፊነት ሲገልጽ፡፡ ከዚህ በኋላ ማንኛውንም አይነት ሥራ ቢሆን ሳይንቅ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም ነው የሚናገረው፡፡
መንግሥት በጠንካራ የክትትል ሥራዎች በርካቶችን ከአስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ እያደረገ ላለው በጎ ተግባርም መካሻ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
የሦስት ዓመት ልጅ እና የሰባት ወር ልጅ ይዛ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ወይዘሮ ነሂማ አህመድ በበኩላቸው፤ ሰርቼ እለወጣለሁ በማለት ልጅ ይዘው ወደ ስደት ቢሄዱም እንዳልተሳካላቸው ይገልጻሉ፡፡
እንጀራ ፍለጋ ወጥተው ገንዘባቸው ለባህር ላይ ወንበዴዎች ሲሳይ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ለ10 ወራት ያህል ከልጆቻቸው ጋር የእስር ቤትን ስቃይ ቀምሰዋል፡፡ በስደት ቆይታቸው ልጅ ይዞ እስር ቤት መግባት አስቸጋሪው የህይወት ፈተና እንደነበር ጠቅሰው፤ ሁሉም ሰው በእንዲህ መንገድ ለስደት መዳረግን ምርጫው ማድረግ እንደሌለበትም ይመክራሉ፡፡
ምንም እንኳን አስቸጋሪው የህይወት ውጣ ወረድ ትልቅ ጠባሳ ጥሎባቸው ቢያልፍም ከነ ሙሉ አካላቸውና ከነ ልጆቻቸው ለሀገራቸው ለመብቃታቸው ለመንግሥት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም