Site icon ETHIO12.COM

ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴቶች የተጣሉት ፊልሞች

ሰው በባሕሪው ቤተሰቡን፣ አካባቢውን፣ ማኅበረሰቡን ይመስላል፡፡ ባለንበት የዲጂታል ዘመን ደግሞ ሰው የሚያየውንና የሚሰማውን ይመስላል፡፡ በተለይ ህጻናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸውና አካባቢያቸው ይልቅ ባህሪያቸው ከዲጂታል ሚዲያው የሚቀዳ ሆኗል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ከኢትዮጵውያን ባህልና ወግ ውጪ የሆኑ መልዕክቶች፣ ቀልዶችና ፊልሞች ማኅበረሰቡን ከነባር ባህልና እሴቱ እያፋቱ ለአዳዲስ ልማዶች እያጋቡት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የዛሬው ትውልድ ከትናንቱ ጋር ያለው ልዩነት በእጅጉ የሰፋ፤ ለባህልና እሴቱ ያለው ዋጋም እይወረደ መጥቷል።

አቶ አየለ ቲሳው የ70 አመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ በእሳቸው በልጆቻቸው በልጅ ልጆቻቸው አስተዳደግ መካከል ያለው ልዩነት ያስገርማቸዋል፡፡ የአሁን ዘመን ልጆች በመልካቸው እንጂ በባህሪያቸው ወላጆቻቸውን አይመስሉም ይላሉ፡፡

የአሁን ልጆች ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍና አብሮ ለመጫወት ጉጉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከስልክና ቴሌቪዥን ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ይበልጥባቸዋል፡፡ ስማቸው ሲጠራ እንኳ አቤት ማለት በማይችሉበት ሁኔታ ከቴክኖሎጂዎች ጋር ተጣብቀው ይቀመጣሉ ሲሉ ትዝብታቸውን አጋርተዋል።

የበለጠ የሚያስደነግጠኝ ግን፣ ልጆቹ ጊዜያቸውን በሰጡት ቲቪና ስልክ የሚያዩት አብዛኛው ነገር ፍጹም ከማኅበረሰባችን ባህልና ወግ የወጣ መሆኑ ነው የሚሉት አቶ አየለ፤ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡ ጉዳዮችን ከማኅበረሰባችን ወግና ባህል ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ ብሎ የሚጠይቅና የሚቆጠጣር አካል ሊኖር ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ዛሬም ለወላጆቻቸው የሚታዘዙ፣ ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩ፣ ለሰው ልጅ ዋጋ የሚሰጡ፣ ባህላቸውን የሚረዱና የሚያከብሩ ታዳጊዎችና ወጣቶች የመኖራቸውን ያህል ከዚህ በተቃራኒ ከኢትዮጵያዊ ወግ የተፋታ፣ ነውርን ከክብር ለይቶ የማያውቅ ትውልድ እየተበራከተ መጥቷል ያሉን ደግሞ የሶስት ወጣቶች እናት የሆኑት ወይዘሮ ፍቅርተ ኃ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡

ትውልዱ የራሱ ባልሆነ ባህልና ልማድ ተጋላጭ መሆኑ ችግር ፈጥሯል። በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉለት በተለይም ከውጭ ሀገራት ተተርጉመው ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡ ፊልሞች ትውልዱን አጉል አድርገው እየቀረጹት ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ትውልዱ የባሰ እንዳይጠፋ ሃይ ባይ አካል ሊኖር ይገባል ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዋ ኢየሩሳሌም ዳኜ በበኩሏ፤ በተለይም ከውጪ ሀገር ቋንቋ ተተርጉመው የሚቀርቡ ፊልሞች ትውልዱን ከራሱ ባህል ከማራቃቸውም ባለፈ፣ አዳዲስ ወንጀሎችን እያስተዋወቁ መሆኑን ትናገራለች፡፡

ፊልሞቹን በተመለከተ የጠለቀ ማብራሪያ ለመስጠት የፊልሞቹ ተከታታይ መሆንና ጥናትን የሚፈልግ ቢሆንም፣ ሲኒማ በትውልድ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አለመሆኑ ግልጽ ነው ትላለች፡፡ በአንድ ወቅት በሞተር ሳይክል የስርቆት ወንጀል እንደተፈጸመባት ያስታወሰችው ወጣቷ፣ የደረሰባትን ያጫወተቻቸው ጓደኞቿ ይህ የወንጀል አይነት በቀጥታ ከውጪ ተተርጎሞ ለኢትዮጵያውያን በቀረበ ፊልም ላይ የተዋወቀ መሆኑን እንዳጫወቷት ታስታውሳለች።

የሌላውን ባህል ማወቁ፤ ከዓለም ህዝቦች ጋር የባህል ሽግግር መኖሩ መልካም ቢሆንም፣ እንደ ማኅበረሰብ የሚጠቅመንን ከሚጎዳን ለይተን፣ የቀረበልንን አላምጠን የምንውጥ ባለመሆናችን የሚቀርቡ ፊልሞችና ድራማዎችን የሚቆጣጠርና ኃላፊነትም የሚወስድ አካል ሊኖረን ይገባል ስትል ሃሳቧን ሰጥታለች።

ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡ ነገሮች ከገቢ አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ የሚያመጡት ተጽዕኖ ምንድነው? ምንስ ጠቀሜታ አላቸው የሚለው መታየት እንዳለበት ነው ያመላከተችው። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ የፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲ፣ ደግሞ፤ የፊልም ፖሊሲም እንደ ሀገር ከወጣ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ ፖሊሲው ሲወጣ ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችል የራሱ ስትራቴጂ ሊኖረው ስለሚገባ ስትራቴጂው በቅርቡ ወጥቷል፡፡ ይህንን ስትራቴጂም ወደ መሬት ለማውረድ እቅድ ተይዞ ይገኛል ይላሉ፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ግን የጥበብ ነጻነት ጉዳይ ስላለ፣ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞከረው በአብዛኛው ከባለድርሻ አካላት ጋር የሂስ መልክ ያላቸው የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ነው የሚሉት ወይዘሮ ነፊሳ፤ እየቀረቡ ያሉ ፊልሞች ከሀገራችን ባህል ጋር ምን ያህል ይመጋገባሉ የሚለው ሲታይ ችግሮች መኖራቸውን አመኖራቸውን አልሸሸጉም

“አሁን ያለው ትውልድ ሰው አክባሪ ነወ? ታላቅ ታናሹን ያከብራ? ወጉንስ ያውቃል ወይ? የራሱን ባህል ጠንቅቆ ያውቃል? የሚለውን ስናይ መልሱ ጥሩ አይሆንም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ መስጠትና መከታተል እንዲሁም ሥርዓት ይዘው እንዲያድጉ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ነው ያመላከቱት።

ልጆች ጊዜያቸውን እያሳለፉ ያሉት የሀገራቸውን ባህልና እሴት እንዲጠብቁ ፣ ማኅበረሰባቸውንና ታሪካቸውን እንዲያውቁ ዕድል በማይሰጡ ፊልሞች ነው። ስለዚህም ልጆችን መቆጣጠር የወላጅ ኃላፊነት ነው፤ ቤታችንንም ልጆቻንንም የምናለማውም ሆነ የምናጠፋው ራሳችን ነን፣ ልጆቻችንን እየቀማን ያለው በገንዘባችን የምናመጣው ነገር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ተቋማት በበኩላቸው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል የሚለው ትክክል ቢሆንም፣ ህብረተሰቡ በራሱ የሚያየው ነገር ከባህልና ወጉ ያፈነገጠ ከሆነ ራሱን መቆጠብ፤ ባህልና ወጉን ያልጠበቁ ጣቢያዎችን አለመጠቀምና የራሳችንን ባህልና ወግ በሚያስተላልፉት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ወላጅ ልጁን ከመቆጣቱ በፊት ለራሱም የሚያያቸውን ነገሮች መርጦ በማየት ለልጆቹ አርዓያ መሆን እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ቁጥጥርን በተመለከተ ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሙያና የብቃት ማረጋገጫ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ብቃት ከሚያረጋግጡ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ሲሆን፣ ተቋማቱ የብቃት ማረጋገጫውን አጽድቀው ሲልኩ በቀጣይ ፊልሞችን በዝርዝር መቆጣጠር የሚያስችለውን መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ቁጥጥር ሥርዓት የሚገባ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥር  14/2016

Exit mobile version