Site icon ETHIO12.COM

ከፕሪቶርያው ስምምነት በሁዋላ መንግስት ለትግራይ ክልል ከ37 ቢሊየን ብር በላይ ሰጥቷል

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር፣ ትህነግ ከ60 ቀን በላይ ተሰብስቦ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ መንግስት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በሁዋላ ለክልሉ ያደረሰውን ገንዘብና የዓይነት ደጋፍ ዘርዝሮ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ አቁም እንዳለው አስታወቀ። ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ክልሉ መላኩንም አመለከተ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑንን አመልክቷል። የባለቤትነት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ህገመንግሱ በሚፈቅደው መሰረት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ህዝብ ወሳኔ የሚካሄድባቸውን አግባብ ለመከተል ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ አብሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ትህነግ በትግርኛ ባሰራጨው ድርጅታዊ መግለጫ መንግስትን ወቅሷል። ምዕራብ ይግራይ የሚለውን የወልቃይት መመለስ አጉልቶ የጠየቀው የትህነግ መግለጫ የኤርትራ ወታደሮችም በሃይል ከያዙዋቸው አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ የኤርትራ ህዝብ ጫና እንዲያደርግ ተማጽኗል። ቀደም ሲል ከሻዕቢያ ጋር ስትራቴጂክ አጋር እንደነበሩ አስታውሶ አሁንም ያ አጋርነት ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክቷል። የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር አሳስቧል።

“የፕሪቶርያው ስምምነት ከምንም በላይ ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል” ሲል በምላሹ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጠቁሟል። በአንዳንድ አካባቢዎች “ትክክለኛ” ያላቸው ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቋል። የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናንት ከሚመለከታቸው ከአማራና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል ያንብቡ።


የፕሪቶርያው ስምምነት ከምንም በላይ ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል፡፡


ሕወሐት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው ስምምነት እንዲከበር መጠየቁን የፌዴራል መንግሥት በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን የኢፌድሪ መንግሥት በጽኑ ያምናል።ይሄንንም በተመለከተ የፌዴራሉ መንግሥት ከመነሻው እስካሁን ያለው አቋም ወጥ እና የማይናወጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የፕሪቶርያው ከአቋም ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴም አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ ለሰላም፣ ለፖለቲካዊ መፍትሔና ለትብብር ያለውን አቋም የገለጸው ከፕሪቶርያው ስምምነት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ መቀሌ ከተማ እንዳይገባ የተደረገው ለሰላም ዕድል ለመስጠት ነው፡፡
ከስምምነቱ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ያሉበትን ቡድን ወደ ትግራይ የላከው የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡
የፌዴራል መንግሥት ተቋማትና ክልሎች ለትግራይ ሕዝብ ድጋፋቸውን ያሳዩት ወዲያው ነው፡፡ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በመቀሌ ተገኝተው ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት በማሳየት የሚቻላቸውን ድጋፍ በዓይነትና በገንዘብ አድርገዋል፡፡
በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የገዢው ፓርቲ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ በመተው ሕወሐትና የታጣቂ አመራሮች ጊዜያዊ መንግሥቱን እንዲያቋቁሙ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ከልዩ ልዩ አካላት ተውጣጥተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚካተቱ አመራሮች እስኪተዋወቁና እስኪግባቡ ድረስ የትግራይ ሕዝብ የችግር ወቅት እንዳይራዘም በማሰብ ነው፡፡
በዚህም ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝት ከፕሪቶርያው ስምምነት በላይ በመሄድ አረጋግጧል፡፡
ለትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲቻል የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና የርዳታ ሥራዎችን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች በትግራይ ተገኝተው ከክልሉ ቢሮዎች ጋር እንዲወያዩ የተደረገው የፕሪቶርያ ስምምነት በተፈረመ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች በጀትና ባለሞያዎችን በመመደብ በክልሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አስችለዋል፡፡
በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል ልዩ ልዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የሰው ኃይልና የተቋም ዐቅም ግንባታ፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ሥልጠና፤ የዩኒቨርሲቲዎችን የአመራር ቦርድ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በኩል 165.8 ሚሊየን ብር በዕቅድ ተካትቶ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ለአንደኛና ለሁለተኛ ሩብ ዓመታት ማስፈጸሚያ 517.9 ሚሊየን ብር በገንዘብ ሚ/ር በኩል ለክልሉ ተልኳል፡፡
በትምህርት ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት 1.46 ቢልየን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በ2016/17 በትምህር ቤቶች ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች የ111.08 ሚሊየን ብር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ 441.5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል የ5 ሚሊየን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ የ109 ሚልየን ብር የትምህርት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የክልሉን የማዕድናት ልማት ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ለዘርፉ መሥሪያ ቤት የመገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፤ የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳይ ኤግዚቢሽን በሚልኒየም አዳራሽ በፌዴራል ወጪ ተከናውኗል፡፡ የሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ተመልሷል፡፡ በፋብሪካና በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አካላትን በመደገፍ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ለወርቅ ሥራ የሚያገለግሉ ሁለት ከባድ ተሸከርካሪዎች በእርዳታ ተለግሰዋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክልሉን የዘርፍ መሥሪያ ቤት ለማጠናከር ከተወሰዱ ርምጃዎች ባሻገር ለካፒታል በጀት 4.9 ቢሊየን ብር፤ ለመደበኛ በጀት 11.4 ቢሊየን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 400 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 16.7 ቢሊየን ብር በ2015/16 ለክልሉ ተሰጥቷል፡፡ በክልሉ ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በድምሩ 5.1 ቢሊዮን ብር ተላልፎላቸዋል፡፡ በልማት አጋሮች በኩል ደግሞ የ1.7 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
ከእነዚህም በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በቻናል አንድ 1.7 ቢሊየን እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር በክልሉ ባቋቋመው ጽ/ቤት በኩል፣ በትግራይ ለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ565 ሚልየን ዶላር በላይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክትም 65 ሚሊሊን ብር ለክልሉ ተላልፏል። የሥራና ክሕሎት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በክልሉ የሚገኙ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችንና ተቋማትን ለማብቃት ሥልጠና ሰጥተዋል፤ ቁሳቁስ አሟልተዋል፤ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች የምላሽ አገልግሎት የሚውል ከ7 ሚሊየን ዶላር በላይ ለክልሉ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ለመደገፍም የ28 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማጠናከር ሲባል የቢሮ ዕቃዎችና የተሸርካሪዎች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የክልሉ መሠረተ ልማቶችን ለመሥራትና ለመጠገን እንዲችል ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡ የግንባታና የጥገና ማሽነሪዎች ተሰጥተውታል፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ ድልድዮችን በጊዜያዊነት ለመጠገን እንዲቻል ሁለት ተገጣጣሚ ድልድዮች የተለገሱ ሲሆን አራት ድልድዮችን ለመገንባት ጨረታ ወጥቷል፡፡
በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም በልዩ ፕሮግራም የክልሉ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለዘጠኝ ከተሞች የፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ409 ሚሊየን ብር በላይ እና ከ7 ሚሊየን ዶላር በላይ ለክልሉ ተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ እና ለመንገድ ፕሮጀክት ጥገና ከ418.6 ሚሊየን ብር በላይ ወደ ክልሉ ልኳል፡፡ ለትግራይ ገጠር መንገድ ጥገና ከመንገድ ፈንድ ከብር 107 ሚሊየን ብር በላይ፤ የ2026 በጀት ቅድመ ክፍያ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ተልኳል፡፡ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል ደግሞ በጠቅላላው የ4.2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የትግራይ ክልልን የባህልና ስፖርት እንቅስቃሴ ከተቋረጠበት ለማስጀመር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የሚመለከታቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖች ተገቢውን ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በክልሉ እንዲከናወኑ አድርገዋል፡፡ ለክልሉ የስፖርት ክለቦችም የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡
የክልሉን የጤና ዘርፍ ዐቅም ለመገንባት እንዲቻል 164 ልዩ ልዩ ባለሞያዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት በመደገፍ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ሁሉም ሆስፒታሎች ተኝቶ የማከም አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተችሏል፡፡
ከ830 ሺህ በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት ከማግኘታቸውም ሌላ ከ65 ሺህ በላይ ሕዝብ የኮቪድ ክትባት አግኝቷል፡፡ ከአምቡላንሶች በተጨማሪ ወደ 2 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፎችም ተከናውነዋል፡፡
በ2015/16፣ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከ600.2 ሚሊየን ብር በላይ ለትግራይ ክልል የጤና ዘርፍ የገንዘብና የግብአት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ትግራይ በቱሪዝም ሀብት የታወቀ ክልል ነው፡፡ ይሄንን ሀብት መልሶ ወደ ጥቅም ለማዋል እንዲቻል ቱሪስቶችን የማበረታታት ሥራ ተጀምሯል፡፡
አልነጃሺ መስጅድንና የገርዓልታ ገዳምን ለቱሪስቶች የማስከፈት እንቅስቃሴም ተከናውኗል፡፡ የውኃ ሀብትን ለመጠቀምና ውኃን ለሕዝቡ ለማዳረስ እንዲቻል ለዘርፉ ተቋም ልዩ ልዩ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን፣ የክልሉን ቢሮ የማደራጀትና በቁሳቁስ የማሟላት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለተበላሹ የአገልግሎት ሰጪ ሀብቶችም ጥገና ተከናውኗል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ 217 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል፡፡ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠር በተለያዩ ባዛሮችና ኤክስፖዎች ላይ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ የመሠረታዊ ሸቀጦችን ተደራሽነት ለማስፋት መንግሥት በወሰደው ርምጃ የተለያዩ የምግብና የመጠቀሚያ ሸቀጦች ለትግራይ ክልል ቀርበዋል፡፡
የነዳጅ ማደያዎችን እንዲጠገኑ በማድረግ፣ በክልሉ በቂ ነዳጅ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የትግራይ ክልል ንግድ ፈቃድ ላላቸው 7 ሺህ 240 ነጋዴዎች፣ ከተለመደው አሠራር ወጣ ብሎ ከሐምሌ 1/ 2014 ጀምሮ በአዲስ አበባ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡
51.3 ሚሊየን ብር ለዘር ግዥ ወጪ ተደርጓል፡፡ በ2015/16 13.4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለክልሉ የቀረበ ሲሆን፣ ለ1427 አርሶ አደሮች መጠቀሚያ የሚሆን 1720 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዚሁ የምርት ዘመን ፕሮጀክቶች በኩል ለክልሉ ተገዝቶ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመን ክልሉ 80 ሺ የተለያዩ ማዳበሪያዎች ጠይቆ ሁሉም ቀርቦለታል፡፡ ለ2016/17 ምርት ዘመን ደግሞ ክልሉ ከጠየቀው መካከል የ70 ሺ ቶን ማዳበሪያ ተገዝቷል፡፡ ለግብርና መገልገያ የሚሆኑ የትራክተሮች፣ የውኃ ፓምፖች ድጋፍ ለአርሶ አደሮች ተለግሷል፡፡ በልማታዊ ሴፍቲኔት በኩል 6.2 ሚሊየን ብር የተላለፈ ሲሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የግብርና ሚኒስቴር ባደረጉት ስምነት መሠረት ደግሞ 700 ሺ ኩንታል እህል ተገዝቶ ለክልሉ ቀርቧል፡፡
ለ55 ወረዳዎች በየወረዳው አንዳንድ መኪናና ሞተር ሳይክል፤ እንዲሁም ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮች ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በዘላቂ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም አማካኝነትም 89.2 ሚሊየን ብር ለክልሉ በቁሳቁስ መልክ ተሰጥቷል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ብቻ 11ሺ ኩንታል ምርጥ ዘርና 30 ትራክተሮች ለትግራይ ገበሬዎች ተለግሷል። ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል።
የዊዝሆልዲንግ ታክሶችን ጨምሮ ብር 3.9 ቢሊየን ብር ወደ ክልሉ ትልልፍ ተደርጓል፡፡ ከክልሉ ግብር ከፋዮች የተሰበሰበ ብር 138.06 ሚሊየን ብር ወደ ክልሉ ሂሳብ ተላልፏል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ለተጠቀሱትና ለሌሎችም ወጪዎች ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ከ37 ቢልዮን ብር በላይ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል ድጋፍ አድርጓል፡፡ በተመደበው በጀትና ድጋፍ የክልሉ ዕቅድ ተግባራዊ ተደርጎ ለሕዝብ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣም ይጠብቃል፡፡
ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ መኖሪያቸው ለመመለስ እንዲቻል የፌዴራሉ መንግሥት የሚመለከታቸውን አካላት አቀናጅቶ ሥራ ጀምሯል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ትክክለኛ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናንት ከሚመለከታቸው ከአማራና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በሕወሐት በኩል ታጥቀው ሲዋጉ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ አለባቸው፡፡ ለዚህም የሚረዳ የተሐድሶ ኮሚሽን የፌዴራሉ መንግሥት አቋቁሟል፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል የሚጠበቅበትን የሰው ኃይልና በጀትም መድቧል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ ተገቢውን ርምጃ በእርሱ በኩል ወስዷል፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውንም ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ሌሎች ሥራዎችንም ለማከናወን እንዲቻል የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዐዋጅ ረቂቅ ዝግጅት አጠናቋል፡፡ ይህ ሂደት እንዲሳካም እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ የትግራይ ክልልም ተገቢው ሚና እንዲጫወት ይጠበቃል፡፡
ለትግራይ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት ሲባል የፌዴራሉ መንግሥት እነዚህን ተግባራት ከሚገባው ባሻገር ተጉዞ አከናውኗል፡፡ ለክልሉ ሕዝብ መደረግ ያለባቸው ድጋፎችንም በራሱ ዐቅምም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለማከናወን የፌዴራሉ መንግሥት ምንጊዜም ዝግጁ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ለትግራይና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት ሲባል የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በሚያደርጉ፤ የክልሉን ዕቅዶች ወደ መሬት በሚያወርዱ፤ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች በተጨባጭ ለመፍታት በሚያስችሉ ገቢራዊ ነገሮች ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው ነው ብሎ የፌዴራሉ መንግሥት ያምናል፡፡
እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ተደርገው የትግራይ፣ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የፌዴራል መንግሥቱ ያለውን ቆራጥ አቋም በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ለፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት መፈጸም ሙሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ የፌደራል መንግሥቱ ጥሪውን ያቀርባል።
ጥር 23 ቀን 2016 ዓ ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version